የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰንደቅ ዓላማችንን ለሁከት አሳልፈን አንሰጥም አሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ብሪታኒያ ሰንደቅ ዓላማዋን ለሁከት፣ ፍርሃት እና ልዩነት ምልክት አድርገው መጠቀም ለሚፈልጉት አሳልፋ አትሰጥም አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰንደቅ ዓላማው "ብዝኃነት ያላትን አገራችንን" ይወክላል ያሉ ሲሆን፤ ሰዎች በቆዳ ቀለማቸው እና በማንነታቸው ምክንያት ፍርሃት እንዲሰማቸው እንደማያደርጉ ገልፀዋል።
የኪር ስታርመር ንግግር የተሰማው በመሀል ለንደን ስደተኞችን የሚቃወሙ 150 ሺህ የሚሆኑ ሰልፈኞች 'ዩናይት ዘ ኪንግደም' በሚል ሕዝበ ትዕይንት ካደረጉ በኋላ ነው።
ሰልፉ ቶሚ ሮቢንሰን በተባሉ የቀኝ ዘመም የፖለቲካ ተሟጋች የተዘጋጀ ሲሆን ይህን ሰልፍ የሚቃወም እና ስደተኞችን የሚደግፍ በዛው በለንደን ተካሂዷል።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አስቀድሞ የንግድ ሚኒስቴር የሆኑት ፒተር ካይል ሰልፉ የመሰብሰብ እና የመናገር መብትን ያሳየ ነው ብለው ነበር።
እሁድ ከሰዓት ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር "ሰዎች ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት አላቸው። የአገራችን አንኳር እሴት ነው።
"ነገር ግን በመንገዶች በቆዳ ቀለማቸው ምክንያት ስጋት ያደረባቸውን ሰዎች የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ያሉ የፖሊስ መኮንኖችን ማጥቃትን አንታገስም" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም "ብሪታኒያ በመቻቻል፣ በብዝኃነት እና በክብር ላይ የተገነባች አገር ናት። ሰንደቅ አላማችን ብዝኃነት ያላትን አገራችንን የሚወክል ነው። ለሁከት፣ ፍርሃት እና ልዩነት ምልክት አድርገው ለመጠቀም ለሚፈልጉት አሳልፈን አንሰጥም" ብለዋል።
ስደተኞች በመቃወም በተካሄደው ሰልፍ አራት ክፉኛ የቆሰሉትን ጨምሮ 26 የፖሊስ መኮንኖች መጎዳታቸውን ፖሊስ አስታውቋል።
በፖሊሶች ላይ ጥቃት በማድረስ 24 ሰዎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለዋል።
እሁድ ከሰዓት ሙሉ መሀል ለንደን የዩናይትድ ኪንግደምን ሰንደቅ አላማ እና የቅዱስ ጊዮርጊስን መለያ ጨምሮ የተለያዩ አርማዎችን የያዙ በሺህዎች በሚቆጠሩ ሰልፈኞች ተጥለቅልቆ ነበር።
ፖለቲከኞች ሰልፉን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች በስደተኞች ዙሪያ የሕዝቡን ጥያቄ እና ስጋት ለመፍታት ጥረታቸውን እንዲያሳድጉ ብርቱ ጥሪ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ቢሊየነሩ ኢሎን መስክ በተቃውሞ ሰልፉ ላይ በቪዲዮ መልዕክት ያስተላለፈ ሲሆን፤ ለሰልፈኞቹን 'ተዋጉ አሊያም ሙቱ' ብሏል።
ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የስደተኞች ፍልሰትን የጠቀሰው ቢሊየነሩ፤ በዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት እንዲለወጥም ጥሪ አቅርቧል።















