ቤት ሊዘርፍ የገባው ጣሊያናዊ ሌባ ቁጭ ብሎ መፅሐፍ ሲያነብ ተያዘ

አንድ ግለሰብ ቁጭ ብሎ መፅሐፍ ሲያነብ የሚያሳይ የፋይል ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Kriangsak Koopattanakij

ቤት ሊዘርፍ የገባው ጣሊያናዊ ዘራፊ ስለ ግሪክ ሚቶሎጂ [አፈ-ታሪክ] የሚተርክ መፅሐፍ ቁጭ ብሎ ሲያነብ መያዙ ተሰምቷል።

የጣሊያን መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የ38 ዓመቱ ዘራፊ በጣሊያኗ መዲና ወደሚገኝ አንድ አፓርትማ በበረንዳ ተንጠልጥሎ ነው የገባው።

ግለሰቡ ሊዘርፍ ወዳሰብው ቤት ከገባ በኋላ ከአልጋው አጠገብ ስለ ሆሜር ኢሊያድ የሚተርክ መፅሐፍ ሲያገኝ ቁጭ ብሎ ማንበብ ይጀምራል።

የ71 ዓመቱ የቤቱ ባለቤት ከእንቅልፋቸው ነቅተው ሲመለከቱ ሌባው በመፅሐፉ ተመስጦ ሲያነብ ያገኙታል።

የሌባው በቁጥጥር ሥር መዋል በመገናኛ ብዙኃን ከተነገረ በኋላ የመፅሐፉ ፀሐፊ ሌባው “አንብቦ እንዲጨርስ” አንድ ዕትም እንደሚልክለት ለሚድያ ተናግሯል።

መፅሐፍ ሲያነብ በቤቱ ባለቤት ዕይታ ውስጥ የገባው ሌባ ደንግጦ በገባበት በረንዳ በኩል ለማምለጥ ሲሞክር ነው በቁጥጥር ሥር የዋለው።

በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ በበረንዳ ተንጥልጥሎ የገባው የሚያውቀውን ሰው ለማገኘት እንደሆነ ለፖሊስ ተናግሯል።

“እኔ የማውቀው የእንግዳ ማረፊያ ቤት [ቤድ ኤንድ ብሬክፋስት] ውስጥ የገባሁ መስሎኝ ነው። መፅሐፉን ሳገኘው ጊዜ ማንበብ ጀመርኩ” ሲል ለፖሊስ ቃሉን ሰጥቷል

‘ዘ ጋድስ አት ሲክስ ኦክሎክ’ የተባለው መፅሐፍ ፀሐፊ የሆነው ጂዮቫኒ ኑቺ፤ ኢል ሜሳጌሮ ለተሰኘው ጣቢያ “የሚግርም ነው” ሲል ተናግሯል።

“እጅ ከፍንጅ የተያዘውን ሰው አግኝቼ አንድ ዕትም ልሰጠው እፈልጋለሁ። ምክንያቱም በቁጥጥር ስር የዋለው እያነበበ ስለሆነ ንባቡን እንዲያጠናቅቅ እፈልጋለሁ” ብሏል።

“በጣም የሚገርም ነው። ሰብዓዊነትንም የሚያሳይ ነው” ብሏል ፀሐፊው።

ሌባው በቁጥጥር ሥር ከመዋሉ በፊት ከሌላ ቤት የዘረፈው ነው የተባለ በጣም ውድ የሚባሉ ልብሶችን የያዘ ቦርሳ አዝሎ ነበር።

ፀሐፊው ኑቺ በሰጠው ቃለ-ምልልስ ከግሪክ አማልክት መካከል በጣም የሚያደንቀው ሄርሜስ የተባለው የሌቦች አምላክን እንደሆነ ተናግሯል።

ሄርሜስ ከግሪክ 12 የኦሊምፒያን አማላክት አንዱ ሲሆን የንግድ፣ ሀብት፣ ዕድል፣ እንቅልፍ፣ ቋንቋ እና ሌብነት አምላክ ነው ይባልለታል።

“[ሄርሜስ] የሥነ-ፅሑፍም አምላክ ነው። ግልፅ እኮ ነው። ሁሉም ምልክት ግለፅ ነው” ሲል ፀሐፊው በቀልድ መልክ ሁኔታውን ገልፆታል።