የዓለም ዋንጫ፡ አርጀንቲና ወደ ቀጣዩ ዙርፍ ስታልፍ ያሸነፈቻት ሳዑዲ በጊዜ ተሰናብታለች

ሊዮኔል ሜሲ

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport

አርጀንቲና በኳታር የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታ የደረሰባትን ሽንፈት በመቀልበስ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ችላለች።

የሊዮኔል ሜሲ ሃገር ምድቡን በአንደኝነት በመምራት ጭምር ነው ለማለፍ የቻለችው።

አርንጀንቲና ትላንት ምሽት ፖላንድን 2 ለ 0 በማሸነፍ ነው ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈችው።

አርጀንቲና አወዛጋቢ በሆነ ሁኔታ ያገኘችውን ፍጹም ቅጣት ምት አምበሉ ሊዮኔል ሜሲ ሳይጠቀምብት ቀርቷል።

ማክ አሊስተር አርጀንቲናን ቀዳሚ የምታድርገውን ጎል በ46ኛው ደቂቃ አስቆጠረ።

አልቫሬዝ ደግሞ ሁለተኛዋን ኳስ ከመረብ አሳርፏል።

በሌላ የምድቡ ጨዋታ አርጀንቲናን በማሸነፍ ድንቅ አጀማመር ያደረገችው ሳዑዲ አረቢያ ፍጻሜዋ አላማረላትም።

በሜክሲኮ 2 ለ 1 ተሰንፋለች።

ከመጀመሪያው ደቂቃ ጀምሮ ተጭና የተጫወተችው ሜክሲኮ የበላይ ለመሆን ችላለች።

ሄነሪ ማርቲን የመጀሪያዋን ጎል በ47ኛው ደቂቃ አስቆጠረ። ሊዊስ ቻቬዝ ደግሞ ሌላኛዋን ጎል ለሜክሲኮ አስቆጥሯል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጨዋታው በዚሁ ውጤት ተጠናቀቀ ሲባል ሳዑዲ ባለቀ ሰዓት በሳሌም አል ዳውሳሪ አንድ ጎል አስቆጥራለች።

አርጀንቲና ምድቡን በስድስት ነጥብ አንደኛ በመሆን አጠናቃለች።

ፖላንድ እና ሜክሲኮ አራት አራት ነጥብ ቢይዙም በጎል ክፍያ ፖላንድ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፏን አረጋግጣለች።

ሳዑዲ አርጀንቲናን በማሸነፍ ባገኘችው ሦስት ነጥብ ምድቡን በአራተኝነት አጠናቃለች።

በምድብ አራት ደግሞ ቱኒዝያ ፈረንሳይን 1 ለ 0 ማሸነፍ ችላለች።

በርካታ የመጀመሪያ ተሰላፊ ተጫዋቾቿን ቀይራ ወደ ሜዳ የገባችው ፈረንሳይ በቱኒዝያ ተሸንፋለች።

ዋህቢ ካዚ ብቸኛዋን ጎል ከመረብ ያሳረፈ ተጫዋች ሆኗል።

ፈረንሳይ ቋሚ ተጫዋቾቿን ቀይራ ውጤቱን ለመቀልበስ ብትሞክርም አልተሳካላትም።

አንቶኒ ግሪዝማን ባለቀ ሰዓት ያስቆጠራት ጎል ከጨዋታ ውጭ በመሆኑ ተሽራለች።

ድሉ በርካታ በፈረንሳይ የተወለዱ ተጫዋቾችን ላሰለፈችው ቱኒዝያ ጣፋጭ ሆኖ አምሽቷል።

በሌላ የምድቡ ጨዋታ አውስትራሊያ እና ዴንማርክ ተገናኝተዋል።

አውስትራሊያ በ60ኛው ደቂቃ በማቲው ሌኪ ብቸኛ ጎል ለማሸነፍ ችላለች።

ከምድቡ ቀድማ ማለፏን ያረጋገጠቸው ፈረንሳይ በስድስት ነጥብ አንደኛ ለመሆን በቅታለች።

ትላንት ያሸነፈችው አውስትራሊያ በተመሳሳይ ስድስት ነጥብ ሁለተኛ ሆና ጥሎ ማለፉን መቀላቀሏን አረጋግጣለች።

ቱኒዝያ በአራት ነጥብ ሦስተኛ ስትሆን ዴንማርክ በአንድ ነጥብ የምድቡ ግርጌ ላይ ሆነው ጨርሰዋል።

በጥሎ ማለፉ የምድብ ሦስት እና አራት ቡድኖች የሚገናኙ ይሆናል።

አርጀንቲና ከአውስትራሊያ ቅዳሜ ምሽት ትጫወታለች።

ፈረንሳይ ደግሞ ፖላንድን እሑድ ታስተናግዳለች።

የምድብ አምስት እና ስድስት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይከናወናሉ።

12፡00 ሰዓት ላይ ክሮሽያ እና ቤልጂየም እንዲሁም ካናዳ እና ሞሮኮ ይገናኛሉ።

ምድብ ስድስትን ክሮሺያ በአራት ነጥብ ትመራለች። ሞሮኮ በተመሳሳይ አራት ነጥብ ሁለተኛ ናት።

ቤልጂየም ሦስት ነጥብ ሲኖራት ካናዳ ያለምንም ነጥብ በምድቡ ግርጌ ላይ ትገኛለች።

ክሮሺያ፣ ሞሮኮ እና ቤልጂየም ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ተስፋ አላቸው።

ምሽት 4፡00 ሰዓት ደግሞ ጃፓን ከስፔን እንዲሁም ኮስታሪካ ከጀርመን ይጫወታሉ።

ምድብ አምስትን ስፔን በአራት ነጥብ ትመራለች። ጃፓን እና ኮስታሪካ አራት አራት ነጥብ አላቸው።

ጀርመን በአንድ ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዛለች።

የዚህ ምድብ አራቱም ቡድኖች ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ተስፋ አላቸው።