የብራዚሉ ዝነኛ ተጫዎች ፔሌ ሆስፒታል መግባቱ ተሰማ

የቀድሞው አጥቂ ፔሌ በ92 ጨዋታዎች 77 ጎሎችን አስቆጥሯል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቀድሞው አጥቂ ፔሌ በ92 ጨዋታዎች 77 ጎሎችን አስቆጥሯል

የቀድሞ የብራዚል ብሄራዊ ቡድን ዝነኛ ተጫዋች ፔሌ ሆስፒታል ገብቷል።

ሆኖም የቀድሞው አጥቂ ወደ ሆስፒታል የሄደበት ጉዳይ ድንገተኛ ህክምና ያደረሰው እንዳልሆነ ልጁ ገልጻለች።

ትላንት ኢኤስፒኤን ብራዚል ፔሌ ሰውነቱ ላይ ባጋጠመው እብጠት ምክንያት ወደ ሳኦ ፖሎ ሆስፒታል ለህክምና መግባቱን ዘግቧል።

ሆኖም የፔሌ ልጅ ኬሊ ናሲሜንቶ በኢንስታግራም ገጿ ከፔሌ ህመም ጋር በተያያዘ “ምንም የሚያስከፋ ዜና የለም” ብላለች።

ፔሌ በፈረንጆቹ 2021 ሆስፒታል ገብቶ የአንጀት እጢ ተወግዶለት መደበኛ ህክምናውን ሲከታተል ነበር።

“የአባቴን ጤንነት በተመለከተ ዛሬ ብዙ ብለዋል” ያለችው ናሲሜንቶ “በሆስፒታል ውስጥ ህክምና እያገኘ ነው። ድንገተኛ ወይም አዲስ ከጤናው ጋር የተያያዘ የሚያስከፋ ዜና የለም። [በፈረንጆቹ] አዲስ ዓመት እዛ እገኛለሁ። ፎቶዎቹንም አጋራቸሁሃለሁ” ብላለች።

ኢኤስፒኤን ብራዚል ጨምሮ የ82 ዓመቱ ፔሌ ከልብ ጋር የተገናኘ ችግር እንደገጠመው እና እየወሰደ ያለው ህክምና የሚጠበቀውን ውጤት ባለማምጣቱ ስጋት ፈጥሯል ሲል ዘግቧል።