የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያገረሸው ጦርነት ቀጣናውን እንዳያበጣብጥ መከላከል ይገባል አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty image/ Kaari/ Michigan university
በኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ ጥሰቶችን የሚያጣራውና በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የተቋቋመው፣ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት መርማሪ ኮሚሽን ያገረሸው ጦርነት ቀጣናውን እንዳያበጣብጥ የመከላከል እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ሲል አሳሰበ።
ኮሚሽኑ የዜጎችን ደኅንነት ለማረጋገጥና እንዲሁም ግጭቱ የበለጠ ተስፋፍቶ ቀጣናውን እንዳያበጣብጥ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
ኮሚሽኑ በትናንት ረቡዕ ጳጉሜ 02/2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ምክር ቤቱ የዜጎችን የደኅንነት ለማረጋገጥና እና ጦርነቱም ተዛምቶ ቀጣናውን የበለጠ ሊያናጉ የሚችሉ ግጭቶችን ለመከላከል በወጣው ቻርተር መሰረት እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
ጦርነቱ ወደ ሌሎች አገራት የመዛመት ስጋት እንዳጫረበትም ገልጿል።
ጦርነቱ በቀጣናው ሰላምና ፀጥታ ላይ ከደቀነው ስጋት አንጻር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በአስቸኳይ በኢትዮጵያ ላይ ለመምከር መወሰኑን ኮሚሽኑ በበጎ እንደሚያየው ገልጿል።
የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ምክር ቤቱ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ሁኔታዎችን ዋነኛ አጀንዳ አድርጎ እንዲያስቀጥላቸው ኮሚሽኑ አሳስቧል።
በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ግጭቱ ማገርሸቱ እንዳሳሰበው የገለጸው የኮሚሽኑ መግለጫ የኤርትራ ወታደሮችም በዚህ ጦርነት ተሳታፊ ናቸው ብሏል።
ኮሚሽኑ ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ጦርነቱን እንዲያቆሙ፣ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ የሚጠበቅባቸውን ግዴታ እንዲያከብሩ እና ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት ወደ ውይይት ሂደቱ እንዲመለሱ ጥሪውን በድጋሚ አቅርቧል።
የተኩስ አቁም አዋጁን ተከትሎ ለአምስት ወራት ጋብ ብሎ የነበረው የርስ በርስ ጦርነት ነሐሴ 18/2014 እንደገና ተቅስቅሶ በተለያዩ ግንባሮች ጦርነት መፋፋሙ ሪፖርት እየተደረገ ነው።
በትናንትናው ዕለት የኤርትራ ጦር በራማ፣ ጾረና፣ ዛላምበሳ እና ዳሎል ግንባሮች ጥቃት እየሰነዘረ ነው ሲሉ የህወሓት ቃለ አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል።
አክለውም የአዲግራት ዙሪያንም የኤርትራ ጦር በከባድ መሳሪያ ቀኑን ሙሉ ደብድቧል ብለዋል።
ከሳምንት በፊት በኤርትራና እና በኢትዮጵያ ጦር በምዕራብ ትግራይ በኩል በአራት አቅጣጫዎች ጥቃት ተከፍቶብናል ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ለሁለት ሳምንታትም ያህል በዚሁ ግንባር ውጊያው እንደቀጠለ በትናንትናው ዕለት በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።
ይህንን አስመልክቶ ከኤርትራ በኩል ምንም የተባለ ነገር ባይኖርም የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሱዳን ጋር በምትዋሰንበት ምዕራባዊ አካባቢን ጨምሮ የትግራይ ኃይሎች ጦርነቱን ወደ ተለያዩ ግንባሮች እያስፋፉ ነው ሲል መክሰሱ ይታወሳል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ከሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ ላይ የትግራይ ኃይሎች አዳዲስ የጦርነት ግንባሮች በምዕራብ በኩል የከፈቱት በምሥራቅ በኩል በቆቦ አካባቢ የከፈቱት ጥቃት እንዳቀዱት ስላልተሳካ ነው ብሏል።
ግጭቱን በመጀመር አንደኛው ወገን ሌላኛውን እየከሰሰ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና መንግሥታት የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ኃይሎች ግጭቱን አቁመው ለድርድር እንዲቀመጡ ጥሪ እያቀረቡ ነው።
ሁለት ሳምንታት ቀናትን ባስቆጠረው ባገረሸው ጦርነት የሰሜን ወሎ ከተማዋ ቆቦ በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የምትገኝ ሲሆን፣ በሌሎች ግንባሮችም ጦርነቶች እየተደረጉ መሆኑ ይነገራል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት የአስር ሺዎችን ሕይወት በመቅጠፍ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብአዊ ቀውስ አድርሷል።
በሁለቱም ወገኖች በኩል የሰብአዊ ተኩስ አቁም አዋጅ ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ጦርነቱ ጋብ ቢልም በትግራይ ያለው የምግብና ነዳጅ ዕጥረት እንዲሁም ስልክ፣ ውሃ፣ መብራት፣ ባንክ የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶች ተቋርጠው መቀጠላቸው ሕዝቡን ለፈተና እንዳረጉት ነዋሪዎችና የረድዔት ድርጅቶች ይገልጻሉ።
ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን የርስ በርስ ጦርነት በድርድር ለመቋጨት የአፍሪካ ኅብረት፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና የተለያዩ አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጥረት እያደረጉ የነበረ መሆኑ የሚታወስ ነው።
ሁለቱም ወገኖች ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውና ተደራዳሪ ኮሚቴም ማዋቀራቸውን ቢገልጹም በአሁኑ ወቅት የርስ በርስ ጦርነቱ ማገርሸቱ የተባለውን የሰላም ሂደት አደጋ ላይ ጥሎታል።












