የወንጀል ታሪኮች ሱሰኛዋ ኮሪያዊት ሰው መግደል የሚፈጥረውን ስሜት ለማወቅ በፈጸመችው ግድያ ተፈረደባት

ጁንግ ዮ-ጁንግ

የፎቶው ባለመብት, Busan Police

የምስሉ መግለጫ, ጁንግ ዮ-ጁንግ

ሰውን መግደል የሚፈጥረውን ስሜት ለማወቅ ካላት ጥልቅ ፍላጎት የተነሳ የማታውቀውን ሰው የገደለችው ደቡብ ኮሪያዊት ወጣት በዕድሜ ልክ እስራት ተቀጣች።

ጁንግ ዮ-ጁንግ የተባለችው የ23 ዓመት ወጣት በእውነተኛ ታሪክ ላይ በተመሠረቱ እና ልብ ወለድ በሆኑ የወንጀል የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ከፍተኛ አባዜ የተጠናወታት ናት ተብሏል።

ፖሊስ ወጣቷ “ሰውን ለመግደል ሙከራ ለማድረግ” አስባ የማታውቃትን የእንግሊዘኛ ቋንቋ መምህርት በሰለት ደጋግማ ወግታ ገድላለች ብሏል።

ይህ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ የተፈጸመው ግድያ መላ ኮሪያውያንን በእጅጉ ያስደነገጠ ክስተት ነበር።

ዐቃቤ ሕግ በደቡብ ኮሪያ ከፍተኛ ጥፋት በፈጸሙ ላይ ብቻ የሚሰጠውን የሞት ቅጣት እንዲወሰንባት ጠይቆ ነበር።

ዐቃቤ ሕግ የወንጀሉን ድርጊት ለፍርድ ቤት ሲያስረዳ፤ ሥራ አጥ እና ብቸኛ የሆነችው ጁንግ የምትገድለውን ሰው ለመለየት ለወራት ያክል ስታስስ ቆይታለች።

ለዚህም ወጣቷ የቋንቋ መማሪያ መተግበሪያን በመጠቀም እንግሊዘኛ ቋንቋ በቤታቸው ያስተምሩ እንደሆነ ከ50 በላይ ሰዎችን ለማነጋገር ሞክራለች።

ግንቦት ወር ላይ እንግሊዘኛ ቋንቋ መማር የምትፈልግ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እና እናት መስላ አንዲት ሴት መምህርትን ማነጋገር ጀምራለች።

ጁንግ ወንጀሉን የፈጸመችው በደቡብ ምሥራቅ ደቡብ ኮሪያ ውስጥ ቡሳን ከተማ ነዋሪ ወደሆነች እና በስም ወዳልተጠቀሰች የ26 ዓመት ሴት መምህርት ቤት ካመራች በኋላ ነው።

ጁንግ ከኢንተርኔት ላይ የገዛችውን የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ ለብሳ ከመምህሯ ቤት ተገኝታለች።

መምህርቷ ወደ ቤቷ ዘልቃ እንድትገባ ከፈቀደች በኋላ ከ100 ጊዜ በላይ በስለት ወግታ እንደገደለቻት ዐቃቤ ሕግ አመልክቷል።

ወንጀለኛዋ ጁንግ የተጎጂዋ ሕይወት ካለፈ በኋላ እንኳ የመምህርቷን አካል በስለት መውጋት ቀጥላ ነበርም ተብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በመቀጠል የተወሰነውን የመምህርቷን አስክሬን በመቆራጠር በታክሲ ተሳፍራ ሰሜናዊ ቡሳን በሚገኝ ወንዝ አቅራቢያ ጥላለች።

ጁንግ ብዙም ሳይቆይ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለች ሲሆን፣ ዐቃቤ ሕግ እንዳለው ወጣቷ በቁጥጥር ስር የዋለችው ተሳፍራበት የነበረው የታክሲ ሹፌር በደም የተጨማለቀ ሻንጣ ጫካ ውስጥ የጣለች ተሳፋሪ ማሳፈሩን ለፖሊስ ከጠቆመ በኋላ ነው።

ፖሊስ እንዳለው ጁንግ እንዴት ሰውን መግደል እና አስክሬን እንዳይገኝ አድርጎ ማስወገድ እንደሚቻል ለማወቅ ለወራት ጥናት ስታደርግ እንደነበረ ከኢንተርኔት አጠቃቀም ታሪኳ መረዳት እንደቻለ ጠቅሷል።

ፖሊስ ጨምሮም ጁንግ ግድያ ለመፈጸም ረዘም ያለ ዝግጅት ብታደርግም እራሷን ከደኅንነት ካሜራዎች ዕይታ ውጪ ማድረግን ዘንግታ ነበር ብላል።

ወጣቷ ወደ መምህርቷ ቤት ስትገባ እና ስትወጣ በተደጋጋሚ ታይታለች።

ባለፈው ሳምንት የቡሳን ወረዳ ፍርድ ቤት በወጣቷ ላይ የዕድሜ ልክ እስራት ብይኑን ሲያስተላልፍ ዳኛው “የትኛውም ሰው ያለ ምንም ምክንያት በማያውቀው ሰው ሊገደል እንደሚችል ወንጀሉ ስላሳየ ግድያው በማኅብረሰብ ውስጥ ከፍተኛ ፍርሃት ፈጥሯል” ብለዋል።

ወንጀሉን መፈጸሟን ያመነችው ጁንግ ወንጀሉን በፈጸመችበት ወቅት የአእምሮ ጤና እክል ገጥሟት ስለነበረ ቅጣቱ እንዲቀልላት ጠይቃለች።

ፍርድ ቤቱ ግን ተከሳሿ ወንጀሉን የፈጸመችው “ከፍተኛ ዝግጅት አድርጋ እና አቅዳ በመሆኑ” የአእምሮ ጤና እክልን ወንጀሉን ለመፈጸሟ እንደምክንያት አድርጋ ልታቀርብ አትችልም ብሏል።

ጁንግ ምርመራ ሲደረግባት እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ የእምነት ክህደት ቃለ መስጠቷን ፖሊስ ተናግሯል።

ጁንግ መጀመሪያ ላይ ግድያው በሌላ ሰው መፈጸሙን እና የእርሷ ተሳትፎ አስክሬኑን ወደ ሌላ ቦታ መውሰድ ብቻ መሆኑን ተናግራ ነበር። ከዚያ ደግሞ መምህርቷን የገደለችው በመካከላቸው አለመግባባት ከተፈጠረ በኋላ ነውም ብላለች።

በመጨረሻም በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረቱ የወንጀል የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን አብዝታ ከመመልከቷ የተነሳ ሰው የመግደል ፍላጎት እንደተጠናወታት አምናለች።