ገበሬውን ያሰጋው፣ ሹፌሩን ከቤት ያዋለው፣ ቱሪስቶችን ያራቀው የአማራ ክልል አለመረጋጋት

የፎቶው ባለመብት, Gettyimage
በአማራ ክልል የተከሰተው አለመረጋጋት ከሦስት ወራት በላይ ሆኖታል።
ክልሉ ካለፈው ዓመት ማብቂያ አንስቶ በመንግሥት ኃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል ከባድ ውጊያን በተለያዩ ጊዜያት እያስተናገደ ይገኛል።
በዚህም ምክንያት በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች መሠረታዊ አገልግሎቶች ተስተጓጉለዋል። በዚህም ሳቢያ ነዋሪዎች ከመደበኛ የሥራ እንቅስቃሴ ውጪ ሆነው ሕይወታቸውን ለመምራት ተቸግረዋል።
ከክልሉ ወደ አዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ወደ ክልሉ የተለያዩ ከተሞች የሚደረጉ ጉዞዎች የተገደቡ በመሆናቸው መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች፣ መድኃኒቶች እና ነዳጅ በበቂ ሁኔታ ማግኘት ፈተና ሆኗል ይላሉ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች።
በክልሉ በተለይ በግብርና እና በቱሪዝም ዘርፎች የተሻለ ምርት እና ገቢ የነበረ ቢሆንም የተፈጠረው አለመረጋጋት ሰብል ከሚዘራበት አስከሚሰበሰብበት ወቅት ድረስ የቀጠለ በመሆኑ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የክልሉ አርሶ አደሮች ላይ ጉዳት አድርሷል፣ ተጨማሪ ስጋትም ተደቅኗል።
በሌላ በኩል በአገሪቱ ካሉ የጎብኚዎች መዳረሻዎች መካከል በርከት ያሉት የሚገኙበት የአማራ ክልል የቱሪዝም እንቅስቃሴ ክፉኛ በመደናቀፉ ኑሯቸው በዘርፉ ላይ የተመሠረተ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በችግር ላይ እንዳሉ ይናገራሉ።
ግብርና. . .
የአማራ ክልል ከፍተኛ የሰብል ምርት ከሚሰበሰብባቸው የአገሪቱ ክፍሎች አንዱ ቢሆንም፣ በክልሉ የተከሰተው አለመረጋገት በግብርናው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል።
በተለይ በመንግሥት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተጀመረው ግጭት ማሳ በሰብል በሚሸፈንበት እና የማዳበሪያ ግብዓት በሚሰራጭበት ወቅት ስለነበረ ተጽዕኖው የከፋ መሆኑን ቢቢሲ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች ከዚህ ቀደም መግለጻቸው ይታወሳል።
በክልሉ ትርፍ አምራች ከሆኑ አካባቢዎች መካከል ምዕራብ ጎጃም ዞን አንዱ ነው። በዞኑ ጃቢ ጠህናን ወረዳ የሚኖሩት አርሶ አደር መስፍን ቻላቸው በጦርነቱ ምክንያት በመቶ ሺዎች ብር የሚገመት ንብረት ሊያጡ እንደሚችሉ ይናገራሉ።
አቶ መስፍን በዘንድሮው የምርት ዘመን ከመደበኛ ሰብሎች በተጨማሪ አንድ ሄክታር ተኩል ማሳ ላይ ሸንኮራ አገዳ አልምተዋል። ሸንኮራ አገዳው አሁን ለመሰብሰብ የደረሰ ቢሆንም ባለው የፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ነጋዴዎች ስጋት ስላደረባቸው ሸንኮራ አገዳውን የሚገዛ ጠፍቷል። በመሆኑም አቶ መስፍን ሌላ አማራጭ እስካላገኙ ድረስ የለፉበትን የሸንኮራ አገዳ ቆርጠው ለመጣል እንደሚገደዱ ይናገራሉ።
ሰላም ሰፍኖ መደበኛ እንቅስቃሴ ቢጀመር ኖሮ ያለሙት የሸንኮራ አገዳ ልማት ከ600 ሺህ ብር በላይ ሊያወጣላቸው እንደሚችል ይገምታሉ።
አቶ መስፍን ከዚህም በተጨማሪ እርሳቸው እና ሌሎች ጎርቤት አርሶ አደሮች የብርቱካን እና የአቮካዶ ፍራፍሬዎችን አልምተዋል። ነገር ግን የሰላሙ ሁኔታ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ የፍራፍሬ ምርቱ ጉዳይም ገበያ የማያገኝ በመሆኑ አሳሳቢ ሆኖባቸዋል።
የክልሉ የግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ድረስ ሳህሉ በክልሉ ያለው ግጭት በአርሶ አደሩ ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደሩን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ምንም እንኳ በባለሙያ የተጠና መረጃ ባይኖርም ለአርሶ አደሩ ድጋፍ ሰጪ የሆኑ ሙያተኞች ወደ ሥራ የሚሰማሩበት ሁኔታ ባለመፈጠሩ፣ አርሶ አደሮች በግጭት ምክንያት ሥራ በማቆማቸው እና ተያያዥ ምክንያቶች ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድር ኃላፊው ገልጸዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸመ ዘረፋ ምክንያት ለአርሶ አደሮች መድረስ የነበረበት የግብርና ግብዓት ሳይደርስ መቅረቱንም ዶ/ር ድረስ ተናግረዋል። “እስካሁን ከ30 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ተዘርፏል” ያሉት የቢሮ ኃላፊው፣ “በወቅቱም በጦርነቱ ምክንያት ዘግይቶ የደረሰውን ግብዓት ማሰራጨት አልቻልንም” ብለዋል።
በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች አሁንም ግጭቱ እንደቀጠለ ነው። አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ተሰብስቦ በተከመረ ሰብል ላይ የሚጣል ከባድ መሣሪያ ቃጠሎ ያስነሳል የሚል ስጋት መኖሩን አርሶ አደሮች ይናገራሉ።
በሌላ በኩል በግጭቱ ምክንያት በአንዳንድ አካባቢዎች አርሶ አደሮች ሰብል በፍጥነት መሰብሰብ ባለመቻላቸው ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ሌሎች ደግሞ ያመረቱትን ሰብል ወደ ቤታቸውም ሆነ ወደ ገበያ ቦታ ለማጓጓዝ ያለው የፀጥታ ሁኔታ አልፈቀደላቸውም።
ከዚህም በተጨማሪም አርሶ አደሮቹ ባለፈው ዓመት ያጋጠማቸው የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት ዘንድሮም ተባብሶ ሊቀጥል ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።
የቢሮ ኃላፊው ዶ/ር ድረስ ግን ማዳበሪያውን ቀድሞ መግዛት መቻሉን ተናግረዋል። ያም ሆኖ ግን ለሚቀጥለው ዓመት የሚሆነውን ማዳበሪያ ለማሰራጨት አሁንም የፀጥታው ሁኔታ አስተማማኝ ባለመሆኑ ስጋቱ መኖሩን ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትራንስፖርት. . .
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመንግሥት ኃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ተስተጓጉሏል።
ከጎንደር፣ ባሕር ዳር እና ከሌሎች የምዕራብ አማራ ከተሞች የሚነሱ ተሽከርካሪዎች ወደ አዲስ አበባ እና ደርሶ መልስ የሚያደርጉትን ጉዞ ካቋረጡ ወራት መቆጠራቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
በተለይ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ በእነዚህ አካባቢዎች እንቅስቃሴ አቁመዋል። በዚህም ምክንያት የሰዎች እና የንግድ እንቅስቃሴ ክፉኛ በመስተጓጎሉ አሽከርካሪዎችን ጨምሮ ነዋሪዎች ለከባድ ችግር መጋለጣቸውን ያነሳሉ።
መለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ በማሽከርከር ሕይወቱን የሚመራው አቶ ዮሴፍ አበበ፣ ነዋሪነቱ በምዕራብ ጎጃም ፍኖተ ሰላም ከተማ ነው።
ዮሴፍ እንደሚለው ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ጉዞ ከመቆሙም በላይ በክልሉ ውስጥ ለመንቀሳቀስም ያለው የፀጥታ ችግር እና የነዳጅ አቅርቦት አለመኖር ከፍተኛ ጫና አሳድሮባቸዋል።
“ከፍተኛ የሆነ መጉላላት እና የታሪፍ ጭማሪ ተደርጓል። ከነበረው ክፍያ ጋር ሲነጻጸር ታሪፉ በእጥፍ ጨምሯል” የሚለው ዮሴፍ፣ ይህ የሆነውም የነዳጅ አቅርቦት ባለመኖሩ እና ሌሎች የንግድ እንቅስቃሴዎች በመቆማቸው ምክንያት ነው።
የአንድ ሊትር ነዳጅ ዋጋ እርሱ በሚኖርበት ፍኖተ ሰላም ከተማ እስከ 150 ብር ድረስ እንደሚሸጥ በመጥቀስ፣ ይህም ሆኖ ነዳጅ በማደያዎች ሳይሆን በደላሎች እየተፈለገ በጥቁር ገበያ እንደሚሸጥ አመልክቷል።
በክልሉ ውስጥ ጦርነቱ እዚህም እዚያም ቢቀሰቀስም ተሽከርካሪዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ሆነው ለመንቀሳቀስ ይሞክራሉ። ነገር ግን ጉዟቸው በሰቀቀን የተሞላ መሆኑን ዮሴፍ ይናገራል።
“አንድ ኬላ ላይ መከላከያ ይፈትሻል። ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ ፋኖ ኬላ ዘርግቶ ይጠብቀነናል” የሚለው አቶ ዮሴፍ፣ በሰላሙ ጊዜ በቀን ውስጥ ከፍኖተ ሰላም ባሕር ዳር እስከ 3 ጊዜ ደርሶ መልስ ይሰራ የነበረ ተሽከርካሪ በአሁኑ ወቅት አንድ ጊዜ ደርሶ ለመመለስ እንኳን በጣም አስቸጋሪ ነው ይላል።
“በስጋት ነው የምንጓዘው፣ አንድን ከተማ ሰላም ቢታለፍ ሌላኛው ከተማ ላይ ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል” በማለት ያለው ሁኔታ ለሥራ ብቻ ሳይሆን ለሕይወትም አስጊ መሆኑን ያብራራል።
ከጦርነቱ በፊት ከፍኖተ ሰላም ባሕር ዳር ለመጓዝ 3 ሰዓት ይፈጅ የነበረው ጉዞ፣ አሁን ግን በየመንገዱ በሚደረገው ፍተሻ እና የሰላም መደፍረስ ምክንያት እስከ 6 ሰዓት ይወስዳል። በዚህ ምክንያትም አሽከርካሪዎች ያለውን የነዳጅ ዋጋ መናር እና የጉዞ መጉላላት ለማካካስ ዋጋውን በእጥፍ ጨምረውታል።
ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ ከሚደረገው እንቅስቃሴ በተጨማሪ በአንድ ከተማ ውስጥም ሕሙማንን እና በምጥ የተያዙ ወላዶችን ወደ ሆስፒታል ለመውሰድ የተሽከርካሪ እጥረት በጣም አሳሳቢ መሆኑንም ገልጿል።
የመንግሥት ተሽከርካሪዎችን እና አምቡላንሶችን ሙሉ በሙሉ የሚጠቀምባቸው መከላከያ ሠራዊት በመሆኑ ከተቋማት የተሽከርካሪ እገዛ መጠየቅም አስቸጋሪ መሆኑን ይናገራል።
ከዚህ በተጨማሪም በከተሞች የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ የተፈቀደው እስከ ምሽቱ 12፡00 በመሆኑ ከዚያ በኋላ የሚያጋጥምን ድንገተኛ ሕመም ለመታከም ተሽከርካሪ መጠቀም የማይቻል በመሆኑ ነዋሪው ላይ ከፍተኛ ችግር እየተፈጠረ መሆኑን አቶ ይሴፍ ተናግሯል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቱሪዝም. . .
በኢትዮጵያ የውጭ አገር ጎብኚዎችን በመሳብ ከሚታወቁ መዳረሻዎች አብዛኛዎቹ የሚገኙት በአማራ ክልል ነው።
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የጎንደር የፋሲል ቤተ መንግሥት፣ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እና የጭስ አባይ ፏፏቴ በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው።
ነገር ግን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋት እና የሰሜኑ ጦርነት መቀስቀሱ የቱሪስት ፍሰቱን በእጅጉ ጎድቶት ቆይቶ ነበር። ከሦስት ወራት በፊት በክልሉ የተፈጠረው የፀጥታ መደፍረስ ደግሞ ሁኔታውን አባብሶታል።
አቶ አሰግድ ተስፋዬ በአስጎብኚነት ሙያ ለ15 ዓመታት ሠርቷል። በአብዛኛው የማስጎብኘት ሥራውን የሚያከናውነው በጎንደር እና በሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ነው።
አሰግድ እንደሚለው በኢትዮጵያ የቱሪስት ፍሰት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚደርሰው ከሰኔ እስከ ጥር ባሉት ወራት ነው። ነገር ግን በእነዚህ ወራት በተለይ በአማራ ክልል ግጭት በመቀስቀሱ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መቆሙን ይናገራል።
የየብስ ትራንስፖርት በመቆሙ ከውጭ ጎብኚዎች በተጨማሪ የአገር ውስጥ ጎብኚዎችም እንደ መስቀል እና ጥምቀትን የመሳሰሉ የአደባባይ በዓላትን ምክንያት በማድረግ ያደርጉት የነበረው ጉዞ መቋረጡንም ይገልጻል።
የዓመቱ 60 በመቶ የሚሆነው ጎብኚ ከሰኔ እስከ ጥር ባሉት ወራት የሚገባ ነው የሚለው አቶ አሰግድ፣ በጎንደር ብቻ በሰላሙ ጊዜ በዓመት 150 ሺህ የአገር ውስጥ እና 30 ሺህ የውጭ አገር ጎብኝዎችን ይቀበሉ እንደነበር ያስታውሳል።
አሁን ባለው ሁኔታ ግን የአገር ውስጥ እንግዳ ወደ ጎንደር የሚሄደው በወር በአማካይ ከ50 እስከ 60 የሚደርስ ብቻ መሆኑን በመግለጽ፣ ከአገር ውጭ ደግሞ በቀን በአማካይ አንድ ጎብኚ ብቻ እንደሚመጣ ተናግሯል።
ችግሮቹ ከመደራረባቸው በፊት ለጥምቀት ብቻ ወደ ጎንደር ከ3000 እስከ 5000 የውጭ ቱሪስቶች ይመጡ ነበር። አሰግድ እንደሚለው ይህ ቁጥር አሁን በእጅጉ ቀንሷል። ለአብነት ባለፈው ዓመት ለጥምቀት በዓል ጎንደር የተገኙት የውጭ አገር ጎብኚዎች 15 ብቻ ናቸው ይላል።
በሰሜን ፓርክ እና በጎንደር ከተማ ብቻ 200 የአካባቢ አስጎብኚዎች እና 25 አስጎብኚ ድርጅቶች አሉ። ከእነዚህ በተጨማሪ ሆቴሎች፣ በቅሎ አከራዮች፣ ስካውቶች፣ ምግብ አብሳዮች፣ መንገድ መሪዎች እና ድንኳን የሚተክሉ ግለሰቦች በቀጥታ ሕይወታቸው ከጎብኚዎች ጋር የተያያዘ ነው።
በክልሉ ውስጥ የሚካሄደው ግጭት ተባብሶ መቀጠሉ ግን ጎብኚዎቹን በማስቀረቱ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወት ላይ የከፋ ጫና አሳድሯል።
የሁለት ልጆች አባት የሆነው አሰግድ አሁን ሥራ በመቆሙ በሰላሙ ጊዜ ሰርቶ በቆጠበው ገንዘብ ሕይወቱን እየመራ ነው።
ለጎብኚዎች የሚሸጡ በተለያዩ ቋንቋዎች የተጻፉ ሦስት መጻሕፍትን አዘጋጅቷል። ነገር ግን ማሳተሚያ ገንዘብ ባለመኖሩ፣ ቢታተምም መጽሐፍቱን የሚገዙት ቱሪስቶች እየመጡ ባለመሆናቸው ምክንያት “መደርደሪያ ላይ ተቀምጠዋል” ይላል።
በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ አስጎብኚ ወጣቶች ከባንክ ተበድረው የቱሪስት ማጓጓዣ ተሽከርካሪ ገዝተዋል። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ገቢያቸው ሙሉ በሙሉ በመቆሙ ብዙ ጓደኞቹ ያንን ዕዳ መልሶ ለመክፈል መቸገራቸውን ይገልጻል።
በመሆኑም “መንግሥት ቢያንስ ታኅሣሥ እና ጥር ወራትን ተኩስ አቁም ማድረግ አለበት” የሚል ሃሳብ ሰንዝሯል። ምክንያቱም በሁለቱ ወራት ቢያንስ እንግዶችን በመቀበል የተወሰነ ሥራ መሥራት ይቻላል ሚል ተስፋ አለው።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱ የክልል ልዩ ኃይሎችን በማፍረስ መልሶ ለማደራጀት እንዲሁም ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በአማራ ክልል ተቃውሞ ገጥሞታል።
በዚህም ምክንያት በክልሉ ውስጥ ያሉ ታጣቂዎች ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር ተደጋጋሚ ግጭት አካሂደው በርካታ ትላልቅ ከተሞችን መቆጣጠር ችለው ነበር።
ይህም ሁኔታ ከክልሉ አቅም በላይ መሆኑን በመግለጽ የክልሉ መስተዳደር የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ በጠየቀው መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ የመከላከያ ሠራዊት ተሰማርቶ ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ለወራት የዘለቀ ግጭት እየተካሄደ ነው።












