ታጣቂዎች የወልዲያ ማረሚያ ቤትን ሰብረው እስረኞችን አስለቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Woldia Communication
በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ወልዲያ ውስጥ በሚገኘው እስር ቤት ላይ ታጣቂዎች ጥቃት ፈጽመው በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን ማስለቀቃቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።
የፋኖ ታጣቂዎች ናቸው የፈጸሙት የተባለው ይህ ጥቃት በእስር ቤቱ ላይ የተፈጸመው ትናንት ሐሙስ ኅዳር 13/2016 ዓ.ም. ለአርብ ሌሊት ላይ መሆኑን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሦስት ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ዋነኛ እስር ቤት በሆነው የወልዲያ ማረሚያ ቤት ላይ ታጣቂዎቹ ጥቃቱን የፈጸሙት እኩለ ሌሊት አካባቢ ጀምሮ ሲሆን፣ በአካባቢው ለሰዓታት የቆየ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ መካሄዱን ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያናገራቸው አንደኛው የወልዲያ ነዋሪ እንዳሉት የተኩስ ልውውጡ የተጀመረው በግምት ከምሽቱ 5፡45 አካባቢ መሆኑን በመጥቀስ፣ የዞን ማረሚያ ቤት በሆነው እስር ቤት አካባቢ ሲሰማ የነበረው የተኩስ ልውውጥ ለሰዓታት ቆይቶ በከተማዋ ውስጥ ሲሰማ እንደነበር ገልጸዋል።
ነዋሪዎች እንዳሉት በማረሚያ ቤቱ ውስጥ የነበሩት እስረኞች አሃዝ ወደ 600 ይጠጋ እንደነበር አመልክተው፣ ከፋኖ ታጣቂዎቹ ጥቃት በኋላ ግን ሁሉም አምልጠው ነበር። ነገር ግን ኋላ ላይ የከተማዋ የፀጥታ ኃይሎች ባደረጉት አሰሳ የተወሰኑትን ብቻ መልሰው መያዛቸው ተነግሯል።
ዛሬ አርብ ከጠዋት ጀምሮ ያመለጡትን አብዛኞቹን ታሳሪዎች ለማግኘት ፍለጋ እየተካሄደ መሆኑን ነዋሪዎች ጨምረው ተናግረዋል።
እኩለ ሌሊት ላይ በተፈጸመው ጥቃት የተፈጸመበት የዞኑ ማረሚያ ቤት የታጣቂዎቹ ዒላማ ሊሆን የቻለው “ከባሕር ዳር ተዘዋውረው ወደ ወልዲያ ማረሚያ ቤት ታስረው የመጡ የቀድሞው የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት እና በወቅታዊ ጉዳይ የታሰሩ ወጣቶችን ለማስፈታት ሊሆን ይችላል” በማለት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ግለሰብ ገልጸዋል።
ታጣቂዎቹ በማረሚያ ቤቱ ላይ ጥቃት በፈጸሙበት ጊዜ ጥበቃ ላይ በነበሩ ሦስት የፖሊስ አባላት ላይ መጠነኛ ጉዳት እንደደረሰ ለቢቢሲ የገለጹ አንድ ለማረሚያ ቤቱ ቅርብ የሆኑ ግለሰብ የሞተ ሰው እንደሌለ ተናግረዋል።
እስረኞችን ያስለቀቁት ታጣቂዎች ከማረሚያ ቤቱ ጠባቂዎች መካከል የተወሰኑ የፖሊስ አባላትን አግተው ከወሰዱ በኋላ አርብ ንጋት ላይ እንደለቀቋቸው ምንጫችን ገልጸዋል።
በከተማዋ ውስጥ ካሉት ፖሊሶች በተጨማሪ፣ የአድማ ብተና ኃይል፣ ፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሠራዊት የነበሩ ቢሆንም የተፈጸመውን ጥቃት ማስቆም አለመቻላቸው ን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ሐሙስ ሌሊት የፋኖ ታጣቂዎች የዞን አስር ቤት በሆነው የወልዲያ ማረሚያ ቤት ላይ ጥቃት ፈጽመው ከሄዱ በኋላ አርብ ከጠዋት ጀምሮ ከተማዋ በተለመደው መደበኛ እንቅስቃሴ ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ የትራንስፖርት እና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማት ክፍት መሆናቸውንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወደ ክልሉ እና ዞኑ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ስልክ በመደወል ሙከራ ቢያደርግም ሳይሳካ ቀርቷል።
በተለይ ለሰሜን ወሎ ዞን ፖሊስ እና ለወልዲያ ማረሚያ ቤት ኃላፊዎች በግል ስልካቸው በተደጋጋሚ ብንደውልም ስልካቸው ሊነሳ አልቻለም።
ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ የፌደራል መንግሥቱ የክልል ልዩ ኃይሎች ፈርሰው ወደ ሌሎች የፀጥታ መዋቅሮች እንዲካተቱ እና ሌሎች ታጣቂዎችም ትጥቅ እንዲፈቱ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በአማራ ክልል አለመረጋጋት መፈጠሩ ይታወቃል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር በሚገኘው የአማራ ክልል ውስጥ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ለወራት ግጭቶች እና ውጊያ እየተካሄደ ይገኛል።
የፋኖ ታጣቂዎች ከፌደራሉ ሠራዊት እና ከክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ጋር ከሚያደርጉት ግጭት በተጨማሪ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙ እስር ቤቶች ላይ ጥቃት ከመሰንዘራቸው ባሻገር፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ዒላማ እንደሚያደርጉ ሲዘገብ ቆይቷል።
የፌደራል መንግሥቱም ካለፈው ነሐሴ ጀምሮ ሠራዊቱን በክልሉ ውስጥ በማሰማራት በከባድ መሳሪያ እና በድሮኖች በታጣቂው ቡድን ላይ ጥቃት እየፈጸመ መሆኑን መዘገቡ ይታወቃል።
በክልሉ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ግጭት ሳቢያ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና የመንግሥታቱ ድርጅት ባወጧቸው ሪፖርቶች ላይ አመልክተዋል።












