የመንግሥት ኃይሎች ላሊበላ ከተማን መልሰው መቆጣጠራቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ረቡዕ ዕለት ከተደረገ ከባድ ውጊያ በኋላ በአብዛኛው በፋኖ ታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር ገብታ የነበረችው ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ በፌደራል መንግሥቱ ኃይሎች እጅ ሥር ተመልሳ መግባቷን ነዋሪዎች ተናገሩ።
በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን መዲና የሆነችው ላሊበላ ከተማ ባለፉት ቀናት በከባድ መሳሪያ የታገዘ ከባድ ውጊያ ሲካሄድባት የቆየች ሲሆን፣ ትናንት ረቡዕ ጥቅምት 28/2016 ዓ.ም. አብዛኛው የከተማዋ አካባቢዋ ክፍል በፋኖ ታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር ገብቶ ነበር።
ይሁን እንጂ የፋኖ ታጣቂዎች ከከባድ ውጊያ በኋላ ረቡዕ ዕለት ከሰዓት በኋላ እና ሌሊቱን በከተማዋ ውስጥ በስፋት ከታዩ በኋላ፣ ሐሙስ ጥቅምት 29/2016 ዓ.ም. ሊነጋጋ ሲል ከላሊበላ በመውጣታቸው የመንግሥት ሠራዊት ከተማዋን መልሶ በመያዙ የተኩስ ድምጽ መቆሙን ነዋሪዎች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ከሐሙስ ረፋድ ጀምሮም የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በላሊበላ ከተማ ውስጥ የቤት ለቤት ብርበራ እያደረጉ ወጣት ወንድ እና ሴቶችን እያሰሩ እንደሆነ ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማች አይጠቀስ የጠየቁ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ካለፈው ሳምንት ማብቂያ ጀምሮ በላሊበላ እና በአካባቢዋ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ሲካሄድ በቆየው ውጊያ በነዋሪዎች ላይ መጠኑ በውል ያልታወቀ የሞት እንዲሁም የአካል ጉዳት መድረሱን ቢቢሲ ለመረዳት ችሏል።
ስማቸውን መጥቀስ ያልፈቁ አንድ ነዋሪ እንዳሉት በተለይ የፋኖ ታጣቂዎች ወደ ከተማዋ ከገቡ በኋላ “የፖሊስ እና የሚሊሻ አባላትን” ኢላማ ማድጋቸውን፤ በዚህም በርካታ ሚሊሻዎች እና ፖሊሶች መገደላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የፈረንሳይ የዜና ወኪል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎችም በተመሳሳይ የፋኖ ታጣቂዎችን መውጣት ተከትሎ መከላከያ ከተማዋን መያዙን እንደገለጹ ዘግቧል።
አንድ ነዋሪ የፋኖ ታጣቂዎች ሌሊት ለሐሙስ ንጋት ላይ ከተማዋን ጥለው ከወጡ በኋላ አሁን የአገር መከላከያ ሠራዊት ከተማዋን ተቆጣጥሯል ሲሉ ተናግረዋል።
ሌላ ነዋሪም እንዲሁ “ረቡዕ ፋኖ አብዛኛውን የከተማዋን አካባቢዎች ተቆጣጥሮ ነበር። ነገር ግን ጠዋት ስንነሳ ታጣቂዎቹ ወጥተው እየጨርሰው ነበር። አሁን ላይ ከተማ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የመከላከያ አባላት ይታዩኛል” ብለዋል።
ረቡዕ ዕለት በነበረው ከባድ ውጊያ የአገር መከላከያ ሠራዊት ላሊበላ ከተማ ዙሪያ ላይ ወደሚገኘው ጦር ሰፍር ተገፍቶ እንደነበረ ነዋሪዎች ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ የፋኖ ታጣቂዎች እንቅስቃሴ በበረታበት ጊዜ ከተማዋን ለቀናት መቆጣጠር ችለው እንደነበር ይታወሳል።
በቅርቡ ደግሞ፤ በተለይ ካሳለፍነው ቅዳሜ ጥቅምት 24/2016 ዓ.ም. ጀምሮ በታሪካዊቷ ከተማ በመንግሥት እና በታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ውጊያ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተዘግቦ ነበር።
ባለፉት ቀናት የላሊበላ ከተማ የተለያዩ ክፍሎች በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች ስር ቆይተው ነበር። ነገር ግን ረቡዕ ዕለት ለሰዓታት ከተካሄደ ከባድ ውጊያ በኋላ የከተማዋ አብዛኛው ክፍል በፋኖ ታጣቂዎች እጅ ሥር መግባቱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በላሊበላ በከባድ ጦር መሳሪያ የታገዘ ውጊያ መባባስ በከተማዋ ያሉ የጥንታውያኑን አብያተ ክርስቲያናት ደኅንነት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል ሲሉ ነዋሪዎች ስጋታቸውን ገልጸው ነበር።
ሮይተርስ የዜና ወኪል ያናገረው አንድ ዲያቆን ለአብያተ ክርስቲያናቱ መጠለያነት የተሰሩ የብረት ሽፋኖች በተባራሪ ጥይቶች መመታታቸውን እንዲሁም የካበድ መሳሪያ ተኩስ ንዝረት እንደሚሰማ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ጉዳዩን አስመልክቶ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት የላሊበላ ቅርሶች ይህ ነው የሚባል የደኅንነት ስጋት የለባቸውም ብሏል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ሰላማዊት ካሳ “ከክልሉ ባገኘነው መረጃ መሠረት የላሊበላ ከተማ እና ቅርሶቿ በሙሉ ሰላም ናቸው” በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
መንግሥት የክልል ልዩ ኃይልን በማፍረስ መልሶ ለማደራጀት እና ሌሎች ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት መወሰኑን ተከትሎ ካለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ጀምሮ በአማራ ክልል የተከሰተው ውጥረት ተባብሶ ሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ ወደለየለት ግጭት መገባቱ ይታወሳል።
የፌደራል መንግሥቱ በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግ ኃይሎቹን ቢያሰማራም፣ ክልሉ ወደ መረጋጋት ሳይመለስ ግጭቱ ባስ፣ ቀዝቀዝ እያለ ወራት ተቆጥረዋል።
በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት መቀጠሉ ያሳሰባቸው የተለያዩ ወገኖች ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግ ጥሪ ቢያርቡም ቀውሱ በአሁኑ ጊዜ እየተባባሰ ይገኛል።












