ከመቀለ ትልቁ ወህኒ ቤት ለማምለጥ በተደረገ ሙከራ አራት እስረኞች መገደላቸው ተነገረ

ወህኒ ቤት

የፎቶው ባለመብት, Tigrai Television

በትግራይ ክልል መቀለ ታራሚዎች ከወህኒ ቤት ለማምለጥ ባደረጉት ሙከራ አራቱ በጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘገበ።

ቅዳሜ ህዳር 1/ 2016 ዓ.ም ምሽት ላይ 125 የሚሆኑ እስረኞች “ተረኛ የማረሚያ ቤቱ ጠባቂዎችን” በማጥቃት በመቀለ ትልቁ ከሆነው ወህኒ ቤት ለማምለጥ ሞክረዋል ተብሏል።

የመቀለ ዞን ተብሎ በሚጠራው የከተማው ትልቁ ማረሚያ ቤት በጠባቂዎች እና በእስረኞች መካከል ግጭት መፈጠሩንም በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተንሸራሸረ ነበር።

ቅዳሜ ከምሽቱ 11፡30 20 ፖሊሶች ላይ ጥቃት በመክፈት እና የሶስት ህንጻዎቹን በር በመስበር ሊያመልጡ እንደሞከሩም የትግራይ ቴሌቪዥን የማረሚያ ቤቱን አስተባባሪ ኮማንደር አማኑኤል ፍስሐን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

ታራሚዎቹ ከእስር ቤቱ ምግብ ማብሰያ ክፍል ቢላዋ በመውሰድ በፖሊሶች ላይ ጥቃት ሰንዝረው ለማምለጥ ቢሞክሩም 112ቱ በቁጥጥጥር ስር መዋላቸው ተዘግቧል። “ታራሚዎችን እንዳያመልጡ ለማድረግ በተወሰደው እርምጃ አራቱ ህይወታቸው ማለፉን” አስተባባሪው ተናግረዋል። ታራሚዎቹ ሞባይል ስልኮችን ወስደው እንደነበር ተገልጿል።

ዘገባው ሊያመልጡ ከሞከሩት ውስጥ 112 ታራሚዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ቢገልጽም ያመለጡ እንዳሉ ያለው ነገር የለም። ታራሚዎቹ እንዳያመልጡ ለማድረግ በተደረገው ሙከራ አራት የጸጥታ ኃይል አባላት ከባድ ጉዳት ሲደርስባቸው ሶስቱ ደግሞ ቀላል ጉዳት መድረሱንም ጣቢያው ጨምሮ ዘግቧል።

ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ተከትሎ በትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ወንጀሎች መበራከቱ እየተዘገበ ይገኛል። በትጥቅ የታገዙ ዘረፋዎች እንዲሁም ግድያዎች አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ረዳ ከጥቂት ወራት በፊት በክልሉ መንግሥታቸው የማያውቀው “የግል ማረሚያ ቤቶችን” ጨምሮ የስርቆት ወንጀሎች መበራከታቸውን ተናግረው ነበር።

ለማምለጥ ሞክረዋል በተባሉ እስረኞች መካከል የተፈጠረው ግጭት እሁድ እለት መቀጠሉን የትግራይ ቴሌቪዥን ዘግቧል።