በአሜሪካ የኢትዮጵያውያንን ትስስር ለማጥበቅ የሚደረገው ‘ግራንድ አፍሪካን ራን’

ሩጫ

የፎቶው ባለመብት, grand african run

ከአራት ዓመት በፊት የተጀመረው እና በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ የሚካሄደው “ግራንድ አፍሪካን ራን” ዘንድሮ ለአራኛ ጊዜ ጥቅምት 05/2015 ይደረጋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚሳተፈበት ይህ ዝግጅት፣ ከአሁን በፊት አንድ ጊዜ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት፣ በበይነ መረብ አማካይነት [ቨርቿል] የተካሄደ ሲሆን ሁለት ጊዜ ደግሞ በአካል ዋሽንግተን ውስጥ ተካሂዷል።

በዝግጅቱ የኦሊምፒክ ሜዳሊስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በመሳተፍ አብረው ይታደሙበታል። ከእዚህ በፊት በነበሩት ውድድሮች አትሌት ደራርቱ ቱሉ እና ሚሊዮን ወልዴ ተሳታፊ ነበሩ።

ዘንድሮ በሚካሄደው አራተኛው ዝግጅት ደግሞ ከደራርቱ እና ከሚሊዮን በተጨማሪ አትሌት ቀነኒሳ በቀለም እንደሚሳተፍ አዘጋጆቹ ገልጸዋል። 

ለ15 ዓመታት ኑሮውን በአሜሪካን አገር ያደረገው ሚካኤል አስራት ከአሁን በፊት ከነበሩት ውድድሮች አንዱን ብቻውን፣ ሁለቱን ደግሞ ከቤተሰቦቹ ጋር ተሳትፏል። “ዘንድሮም ለአራተኛ ጊዜ ለመሳተፍ ተዘጋጅቻለሁ” ይላል። 

“ከእዚህ በፊት በዝግጅቱ የተለያዩ ስመ ጥር አትሌቶች ተሳትፈው ከእነርሱ ጋር የመገናኘት ዕድል ገጥሞን ነበር። ዘንድሮም ከአሁን በፊት ያልተሳተፉትን ጨምሮ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ስለሚሳተፉ ከዝግጅቱ የምንጠብቀው እና የምንጓጓለት ጉዳይ ነው” የሚለው ሚካኤል ዘንድሮ ከሦት ልጆቹ እና ባለቤቱ ጋር ይሳተፋል።

አሜሪካን አገር ተወልደው ያደጉ ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች ትልቅ ራዕይ እንዲሰንቁ፣ አርዓያዎቻቸውን እንዲያዩ እና በአካል እንዲገናኙ እንዲህ ያሉ ዝግጅቶች አስፈላጊ ናቸው።

“በቴሌቪዥን ብቻ የምናውቃቸውና ዝናቸው በዓለም ላይ የናኘ ሰዎች እኛ ጋር በአካል ስለሚሮጡ ለልጆቻችን ትልቅ ተስፋ እና ደስታ ይፈጥርባቸዋል” ብሏል ሚካኤል አስራት።

ከእዚህም በተጨማሪ “እርስ በእርሳችን ከመገናኘትና የምናደንቃቸውን ሰዎች ከማግኘት ባሻገር ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚደረጉ የበጎ አድራጎት ሥራዎች በምንችለው መንገድ አስተዋጽኦ ማድረጋችን ትልቅ እርካታ ይሰጠናል” ብሏል ሚካኤል።

በተለይ በአሜሪካ በሰላም እየኖርን ሃብት ንብረት እያፈራን ነው። ነገር ግን አንድነታችንን በማጠናከር በተለያዩ ዘርፎች በመደራጀት በጎ ሥራዎችን መሥራት አለብን ይላል።

“ማኅበረሰባችንን ከሚለያዩ ነገሮች ይልቅ አንድነታችንን አጠናክረን፣ እንደሌሎች አገራት ጠንካራ ኮሚዩኒቲ ብንመሰርት ተጠቃሚ እንሆናለን። ያንን ለማድረግ ደግሞ እንደእዚህ አይነት ዝግጅቶች አስተዋጽዖ አላቸው” ብሏል።

ሚካኤል አስራት እና ቤተሰቡ

የፎቶው ባለመብት, Michael Asrat

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከአሁን በፊት ሁለት ጊዜ የዝግጅቱ ተሳታፊ የነበረችው የ14 ዓመቷ የመጀመሪያ ልጁ ኑሃሚን ሚካኤል ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ ለትሳተፋለች።

ከአሁን በፊት ከአትሌት ደራርቱ ቱሉ እና ከሚሊዮን ወልዴ ጋር የመገናኘት ዕድል ገጥሟታል። ዘንድሮ ደግሞ አትሌት ቀነኒሳ በቀለን ለማግኘት ጓጉታለች።

“ዝግጅቱ የአገራችንን ሰዎች እና የኦሊምፒክ ሜዳሊስቶችን ለማግኘት ጥሩ ዕድል ነው። ከአሁን በፊት ደራርቱ እና ሚሊዮንን አግኝቻቸዋለሁ። እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል። በአፍሪካ ኮሚዩኒቲ ውስጥ ተጽዕኖ የፈጠሩ ሰዎች ጋር መገናኘት መቻል ትልቅ አጋጣሚ ነው። አሁንም ሌሎች ተጽዕኖ ፈጣሪ ኢትዮጵያውያንን ለማግኘት እና በዝግጅቱ ለመዝናናት ጓጉቻለሁ” ብላለች።

በተለያየ ምክንያት ዝግጅቱ ላይ መገኘት ያልቻሉ ሰዎች ዝግጅቱን በመተግበሪያ (application) መሳተፍ እንደሚችሉም አስተባባሪው ዶ/ር ጋሻው ገልጸዋል።

“የግራንድ አፍሪካን ራን ድረገጽ ላይ በመመዝገብ በፈለጉት ቦታ ሆነው ውድድሩ ሲጀመር መተግበሪያውን በመጠቀም በመሮጥ አምስት ኪሎ ሜትሩን ሲጨርሱ መተግበሪያው ውድድሩን ማጠናቀቃቸውን ይነግራቸዋል። ከእዚያም በአድራሻቸው ሜዳሊያው ይላክላቸዋለል” ብለዋል። 

የዝግጅቱ ተሳታፊዎች የእድሜ ገደብ አይኖርባቸውም የሚሉት ዶ/ር ጋሻው፣ ለሕጻናት የአንድ ኪሎ ሜትር የመሮጫ መም የተዘጋጀ ሲሆን ለአዋቂዎች ደግሞ 5 ኪሎ ሜትር ነው።

ማንኛውም ሰው የዝግጅቱ ተሳታፊ ይሆናል። ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ፋጡማ ሮባ እና ሚሊዮን ወልዴ በዝግጅቱ ይሳተፉበታል።

የዝግጅቱ አስተባባሪ ዶ/ር ጋሻው አብዛ “ግራንድ አፍሪካን ራን ሦስት ዓላማዎችን አንግቦ የሚካሄድ ነው” ብለዋል።

ሩጫ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ያስተዋወቀ ትልቅ የስፖርት ዘርፍ በመሆን በውጭው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን እርስ በእርስ እንዲገናኙ ማድረግ እና ታዋቂ የኦሊምፒክ ሜዳሊያ አሸናፊ አትሌቶችን ተጋባዥ በማድረግ ትስስር መፍጠር ተቀዳሚ ዓላማው መሆኑን ዶ/ር ጋሻው ይገልጻሉ።

ሁለተኛው ዓላማ አገር ቤት መሄድ ያልቻሉ እና አሜሪካ ተወልደው ያደጉ ኢትዮጵያውያንን ከባሕላቸውና ከዕሴታቸው ጋር ማቀራረብ እና ማስተዋወቅ ነው ብለዋል።

ለእዚህም በዝግጅቱ የተለያዩ ባሕላዊ ክዋኔዎችን እና ባሕላዊ መገልገያ ቁሳቁሶችን በማቅረብ ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች እንዲያውቋቸው ይደረጋል ብለዋል።

ገቢ በማሰባሰብ የተያዩ በጎ አድራጎት ማኅበራትን በማገዝ ኢትዮጵያውያንን መርዳት ሦስተኛው የዝግጅቱ ዓላማ ነው የሚሉት ዶ/ር ጋሻው፣ በእዚህ ዓመት በሚኖረው ዝግጅትም በአርቲስት ሰለሞን ቦጋለ የሚመራውን “ኅብረት ለበጎ” የተሰኘውን የበጎ አድራጎት ማኅበርን ለማገዝ አቅደዋል።

ሰባት ዓመት ያስቆጠረው ኅብረት ለበጎ የበጎ አድራጎት ማኅበር፣ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የልብ ሕክምና አገልግሎት መስጫ ሆስፒታ ለመገንባት ዕቅድ አለው።

የግራንድ አፍሪካ ራን ተሳታፊዎች ሁሉም ሜዳሊያ የሚበረከትላቸው ሲሆን፣ አንድ የዝግጅቱ ተሳታፊ ደግሞ በዕጣ የመኪና ተሸላሚ እንደሚሆን አዘጋጆቹ ገልጸዋል።