ሜክሲኳዊው ፖለቲከኛ በዋትስአፕ የተወራበትን አሉባልታ ተከትሎ በደቦ ጥቃት ተገደለ

በደቦ ጥቃት የተገደሉት ሜክሲኳዊ ፖለቲከኛ ዳንኤል ፒካዞ

የፎቶው ባለመብት, DANIEL PICAZO

የምስሉ መግለጫ, በደቦ ጥቃት የተገደሉት ፖለቲከኛ የሜክሲኮ ምክር ቤት አማካሪ ሆነው ሰርተዋል

ሜክሲኳዊው የፖለቲካ አማካሪ "ህጻን ልጅ አግቷል" የሚል ያልተረጋገጠ ወሬ በዋትሰአፕ መሰራጨቱን ተከትሎ በደቦ ጥቃት ተደብድቦ መገደሉን ባለሥልጣናት ገለጹ።

ዳንኤል ፒካዞ የተባለው የ31 ዓመቱ ወጣት ፖለቲከኛ በሜክሲኮ ማዕከላዊ ክልል በምትገኘው ፑይብላ ግዛት 200 የሚደረሱ ሰዎች በተሳተፉበት የደቦ ጥቃት ተደብድቦ እና በእሳት ተቃጥሎ ነው ተገደለው።

ፖለቲከኛው በጥቃቱ ከመገደሉ በፊት ፓፓታልዛኮ የተሰኘችውን ከተማ እየጎበኘ ነበር።

የአካባቢው ባለሥልጣናት ጥቃቱን “አረመኔያዊ” ድርጊት ሲሉ ኮንነውታል።

በአካባቢው ነዋሪዎች የቡድን የዋትስአፕ መልዕክት መለዋወጫ መድረክ ላይ "ግለሰቡ ህጻን ልጅን አግቷል" የሚል መልዕክት ሲሰራጭ፣ ፖለቲከኛው በከተማ ውስጥ አያቱን ለመጠየቅ ነበር የተገኘው።

ጥቃት አድራሾቹ ፒካዞን ወደ ደበደቡበት ቦታ እየጎተቱ ከመውሰዳቸው በፊት ከሁለት ባልደረቦቹ ጋር ከነበሩበት ቦታ ለይተው መውሰዳቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ፖሊስ ፖሊስ ደርሶ ፖለቲከኛውን ከጥቃቱ ለማዳን በተሽከርካሪ ለመውሰድ የሞከረ ቢሆንም የአካባቢው ነዋሪዎች በብዛት ተሰብስበው ከፀጥታ ኃይሎቹ አቅም በላይ በመሆን አሰቃቂውን ግድያ ፈጽመዋል ተብሏል።

የከተማ አስተዳደሩ ባወጣው መግለጫ ደርጊቱን አጥብቆ የተቃወመ ሲሆን ወንጀለኛ የሆኑ ሰዎች ጉዳይ በሕግ ብቻ ሊታይ የሚገባ ነው ብሏል።

“የሚመለከታቸው አካላት ተጠያቂዎችን ለመለየት ምርመራ ማድረግ ጀምረዋል” ተብሏል። ሆኖም ፖሊስ ከግድያው ጋር በተገናኘ እስካሁን በቁጥጥር ሥር ያዋለው ሰው እንደሌለ ታውቋል።

ሟቹ ፖለቲከኛ ‘የእንደራወሴዎች ምክር ቤት’ በተሰኘው የሕግ አውጪ አካል ውስጥ እስከ የካቲት ድረስ ሲሰሩ ሲሰራ ቆይቷል።

የምክር ቤት አባል የሆኑት ጆዋና ቶሬስስ ፣"ፒካዞ ችሎታ ያለው፣ ሥራውን በትጋት ይሰራ የነበረ፣ ለአገሩ በታላቅ ህልም በቁርጠኝነት የሚሰሩ ወጣት ፖለቲከኛ” ነበር ብለዋል።

የኮንግረንስ አባሏ “ነፍሱ በሰላም እንድታርፍ እና ቤተሰቡም እንዲጽናና እጸልያለሁ” ሲሉም አክለዋል።

በምክር ቤቱ በርከት ያለ መቀመጫ ያለው ፓርቲ በበኩሉ ለድርጊቱ ተጠያቂነት እንዲኖር እና ፍትህ እንዲሰፍን ጠይቋል።

በሜክሲኮ በተለይም በገጠራማው ክፍል የደቦ ጥቃት የተለመደ ነው። በእነዚህ ገጠራማ አካባቢዎች ችግር በሚፈጠር ጊዜ ፖሊስ በፍጥነት ስለማይደርስ ሰዎች ለደቦ ጥቃት ይዳረጋሉ።

በዚህ ዓመት በተመሳሳይ ግዛት ውስጥ በደቦ ጥቃት የተገደለ ሁለተኛው ሰው ናቸው።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 ሰባት ሰዎች በደቦ ጥቃት ተደብድብው በሕይወት እያሉ በእሳት ተቃጥለው ተገድለዋል።