በናይጄሪያ ከሃይማኖት አባት ጋር የተጋጨ ግለሰብ በደቦ ተቃጥሎ ተገደለ

የናይጄሪያ ፖሊስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በናይጄሪያዋ መዲና አቡጃ ከአንድ የእስልምና ሃይማኖት መምህር ጋር የተጋጨ ግለሰብ በደጋፊዎቻቸው ዘንድ በደቦ በእሳት ተቃጥሎ መገደሉን ፖሊስ አስታውቋል።

የ30 አመቱ አህመድ ኡስማን በአካባቢው የሚንቀሳቀስ የማህበረሰብ ጥበቃ ቡድን አባል የነበረ ሲሆን 200 የሚሆኑ ሰዎችም ከሱ በተፃራሪ መቆማቸው ተገልጿል።

ስለ ግጭቱ የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም።

ባለፈው ወር አንዲት ሴት ክርስቲያን ተማሪ የእስልምና እምነትን የሚያጠለሽ ንግግር ተናግራለች በሚል በሶኮቶ ከተማ በሙስሊም ተማሪዎች በእሳት ተቃጥላ መገደሏ ይታወሳል።

በአቡጃ ተቃጥሎ ህይወቱ ያለፈውን ግለሰብ በተመለከተ ፖሊስ እንደገለጸው “በሉግቤ አካባቢ በቲፐር ጋራዥ በሚገኘው የፌደራል ቤቶች ያለው የአካባቢ የማህበረሰብ ጥበቃ አካል” መሆኑን ነው።

ፖሊስ በአካባቢው በደረሰበት ወቅት ግለሰቡ በከፍተኛ ቃጠሎ ተጎድቶ ያገኘው ሲሆን ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም ህይወቱ ወዲያውኑ አልፋለች።

የቢቢሲ የአቡጃ ጋዜጠኛ ክሪስ ኢዎኮር በናይጄሪያ የደቦ ጥቃት እየጨመረ የመጣ ይመስላል ብሏል።

ከሁለት ሳምንት በፊት በአቡጃ ከተማ ዳርቻ በሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች እና ነጋዴዎች መካከል በተቀሰቀሰ ሁከት በትንሹ አምስት ሰዎች ተገድለዋል።

ከጥቂት ቀናት በፊት በሀገሪቱ የንግድ ማዕከል ሌጎስ የ38 ዓመቱ የሳውንድ ኢንጂነር በደቦ በደረሰበት ጥቃት ህይወቱ አልፏል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንደሚናገሩት በተደጋጋሚ የሚፈጸሙት የደቦ ጥቃቶች መንስኤው ሥር የሰደደ የጥፋተኝነት ስሜት አለመሰማት እና በፍትህ ሥርዓቱ ላይ እምነት ከማጣት የመነጨ ነው።