ሽልማት ያሸነፈው የልጆች መጽሐፍ ደራሲ ዚነት ከማል

ዚነት ከማል ሁለት የልጆች መጽሐፍትን ደርሳለች

የፎቶው ባለመብት, Zinet Kemal

የምስሉ መግለጫ, ዘኒት ከማል ሁለት የልጆች መጽሐፍትን ደርሳለች

ዚነት ከማል በ2013 (እኤአ) ከትውልድ ስፍራዋ አዲስ አበባ ወደ አሜሪካ የሔደችው ዲቪ ደርሷት ነው።

የተሻለ ሕይወትን ፍለጋ ወደ አሜሪካ ከማምራቷ በፊት ዚነት በሕግ ትምህርት ከጅማ ዩኒቨርስቲ ተመርቃ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ በሙያዋ ስታገለግል ነበር።

አሜሪካ ከሄደች በኋላ በሚኒሶታ ግዛት ከሚትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ በአይቲ የትምህርት ዘርፍ በከፍተኛ ውጤት ተመርቃለች።

አራት ልጆች እያሳደገች፣ አዲስ የትምህርት ዘርፍ እየተማረች ሁለት የልጆች መጽሐፍ መድረሷን የምትናገረው ዚነት ከማል፣ በሕይወት መንገድ ላይ ዝለት አጋጥሟት አርፋ እንደማታውቅ ታስረዳለች።

ሽልማት ያሸነፈው የልጆች መጽሐፍ

ዚነት ከኢትዮጵያ ከመውጣቷ በፊት የምታውቀው ነገር ቢኖር የሕግ ባለሙያ መሆኗን እንጂ ጥበብ በነፍሷ ውስጥ ዘር እንዳላት አይደለም።

አሜሪካ ከሄደች እና የሙያ ለውጥ ካደረገች በኋላ ግን አካባቢዋን ስትቃኝ የነፍስ ጥሪዋን አገኘች።

የነፍስ ጥሪዋን እንድታገን ያደረጋት ደግሞ ከጥያቄ ቅመም የተሰሩት ልጆቿ ናቸው።

ልጆቿ እንደማንኛውም ልጅ ጠይቀው አይረኩም።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአካባቢያቸው ለሚካሄደው ማንኛውም ነገር ንቁ ተመልካች፣ ብሩህ አሰላሳይ ናቸው።

ይህ የልጆቿ የነቃ መንፈስ የዚነትን የነፍስ ጥሪ አነቃው።

ዘኒት “ይህንን መጽሐፍ ከማሳተሜ በፊት ልጆቼ ትምህርት ቤት የሚያጋጥማቸውን ነገሮች እየመጡ ይነግሩኝ ነበር" ትላለች።

ልጆቿ ትምህርት ቤት ውስጥ ስለ ፀጉራቸው ቀለም፣ ስለሚለብሱት ሂጃብ እና ስለመልካቸው ይጠየቃሉ።

ሂጃብ ስለሚለብሱ ልጆች የሚያወሩ መጻሕፍት፣ አማዞን ላይ ቢኖሩም ጥቂት ስለሆኑ፣ “የራሳችንን ታሪክ ለምን ራሳችን አንጽፍም በሚል ይህንን መጽሐፍ ጀመርኩ፤ ምክንያቱም የእኔ ልጆች ስለማንነታቸው ትምህርት ቤት ሲሄዱ ከተጠየቁ የሌሎች ቤተሰቦችም በዚሁ ጉዳይ ውስጥ ያልፋሉ ብዬ አሰብኩ።”

ዚነት ከዚህ በፊት መጽሐፍ ጽፋ እንደማታውቅ እና እጽፋለሁ ብላ አስባም አታውቅም።

የመጀመሪያ መጽሐፏን በ2021 እኤአ ‘በሂጃቧ የምትኮራዋ ልጅ’ን ከማሳተሟ በፊት መጽሐፍ እንዴት እንደሚጻፍ ልምድ ለመቅሰም የሌሎች ደራሲዎችን ተሞክሮ ስትሰማ እና ስታነብ ቆየች።

ይህ መጽሐፍ ሂጃብ መልበስ የመረጡን ሴቶችን እና አዳጊ ሕጻናትን በራስ መተማመናቸውን ለመጨመር ያለመ ነው ትላለች ዚነት።

“እንደ ፈረንሳይ እና ሕንድ አገራት ውስጥ ያሉ ሴቶች ሂጃብ እንዳይለብሱ መከልከላቸውን አይተናል፤ ሰምተናል። ስለዚህ ከእናንተ ጎን ነን የሚለውን መልዕክት ለማስተላለፍ ጭምር ነው።”

በተጨማሪም ሂጃብ መልበስ ጉዳይ ላይ ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ለማስተካከልም ጭምር መጽሐፉን ማዘጋጀቷን ታስረዳለች። ምክንያቱም የተሳሳተ አመለካከት የሚመጣው አንድን ጉዳይ በደንብ ካለማወቅ ነው ብላ በማሰቧ ነው።

ስለዚህ በአጠቃላይ የመጽሐፉ ዓላማ ከእኛ የተለየን ባሕል ማክበር፣ ማወቅ እና ልዩ በመሆኑ ብቻ አንድ ሰው መድረስ ወይንም ማግኘት ካለበት ስፍራ እንዳይቀር፣ እንዳያንስ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው ስትልም ታብራራለች።

ይህንን መጽሐፍ ለመጻፍ አራት ወር እንደፈጀባት የምትናገረው ዚነት፣ ይሁንና በበይነ መረብ የግብይት መድረክ ላይ ገበያው ደርቶለት በአንደኛ ደረጃ ላይ ሲሸጥ እንደነበር ታስታውሳለች።

ኋላም ይህ የሕጻናት መጽሐፍ "Distinguished Authors Guild" እና "2022 Literary Titans Book Award" የሚባሉ ሽልማቶችን አግኝቷል።

ዚነት ከማል ከሁለት መጽሐፍቶቿ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Zinet Kemal

የአንዱ ስኬት ለሌላው ጥንስስ

ዚነት ከመጀመሪያው መጽሐፏ ስኬት ባገኘችው መበረታታት በስድስት ወር ውስጥ ሁለተኛውን የልጆች መጽሐፍ ‘ኦ ኖ ሃክድ አጌን’ ( Oh No Hacked Again) አሳተመች።

“አሁንም ሁለት መጽሐፍ በስድስት ወር እንዴት መጽሐፍ አሳተምሽው ብባል ለዚህ መልስ የለኝም። ምክንያቱም በዓመት ሁለት መጽሐፍ የሚያሳትሙ ደራሲያን እንዴት ከባድ እንደሆነ ስለሚነግሩን” ትላለች።

ነገር ግን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በጀመረበት ጊዜ ልጆቿ በኢንተርኔት አማካይነት ጌም ይጫወቱ እና ትምህርት ይከታተሉ ነበር። ከእነርሱ የሁለቱ ልጆች የጌም አካውንት ሃክ ተደረገ። ይህ ልጆቿን ያጋጠመው ጉዳይ ለሁለተኛው መጽሐፍ አነሳሽ ምክንያት እንደሆናት ትናገራለች።

“መጽሐፉ ውስጥ ያሉት ገጸባህሪያት ስማቸው እንኳ ሳይቀር የልጆቼ ስም ነው። መጽሐፉ ውስጥ ሌሎች የተለየ ባህል ያላቸው ልጆችም ራሳቸውን እንዲያገኙ በሚል ስሞቹን ሃሩን እና ኢልሃን ነው ያደረግኩት”

መጽሐፉ ልጆች የኦንላየን አካውንታቸውን በመረጃ መንታፊዎች ከመሰረቅ [ሃክ] እንዴት መጠበቅ እንዳለባቸው ያስተምራል።

ይህ ሁለተኛው መጽሐፏ የመረጃ መረብ ደኅንነት [ሳይበር ሴክዩሪቲ] ባለሙያ ስለሆነች እናት ስለሚያወራም፣ ልጆች ስለወደፊታቸው ሲያስቡ ከሕክምና እና ከምህንድስና ውጪ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ቢሰማሩም ሊሳካላቸው እንደሚችል ለማሳየት ጥረት ማድረጓን ትገልጻለች።

'የእናት ደመነፍስ ስላለኝ ሳይበር ሴክዩሪቲን መረጥኩ'

ዚነት እና ባለቤቷ ከአራት ልጆቻቸው ጋር

የፎቶው ባለመብት, Zinet Kemal

ዚነት ሴቶች በየትኛውም የሥራ ዘርፍ ወደ ኋላ የሚያስቀራቸውን ምክንያት ለራሳቸው መስጠት እንደሌለባቸው ትናገራለች።

“ስለምክንያት ካወራን እኔ ከመጀመሪያው የሕግ ሙያዬ ወደ ምወደው ቴክኖሎጂ ቀይሬ ስማር አራት ልጆች እያሳደግኩ ነበር። ነገር ግን ይህ ወደ ኋላ አልመለሰኝም። ስለዚህ ምንም ምክንያት መስጠትም ሆነ መቀበል የለብንም” ትላለች።

ይህንንም ስታስረዳ ዚነት የአራት ልጆች እናት ሆና ሙያዋን ለመቀየር ስለወሰነችበት አጋጣሚ በማንሳት ነው።

“ከልጅነቴ ጀምሮ ለቴክኖሎጂ ፍቅር ስለነበረኝ፣ የሒሳብ ትምህርትን 'ሀ' ብሎ ከመማር ጀምሮ ኢንጂነር ለመሆን መስዋዕት ከፍያለሁ” ትላለች።

በአይቲ ትምህርቷ የመጨረሻ ዓመት ተማሪ እያለች፣ አንድ ከዚህ በፊት ሰምታው ስለማታውቀው ስለሳይበር ሴክዩሪቲ ሰማች።

ይህ የሙያ ዘርፍ የግለሰቦችን እና የድርጅቶችን መረጃ መጠበቅ ላይ ያተኮረ ነው።

ዚነት በዚህ ለመጀመሪያ ጊዜ በተዋወቀችው የትምህርት ዘርፍ ትምህርት ቤቷን በመወከል፣ የመረጃ መረብን [ሳይበርን] የሚመለከት፣ “Collegiate Cyber Defense Competition'' በመወዳደር የሦስተኛ ደረጃን በማግኘት አጠናቅቃለች።

አክላም በመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ በሥራ ልምምድ ላይ እያለች ቋሚ ተቀጣሪ የመሆን ዕድል ማግኘቷንም ትናገራለች።

በዚህ የሳይበር ሴክዩሪቲ ዘርፍ መቀጠል ለምን እንደፈለገች ስትናገርም፣ “የእናት ደመነፍስ ስላለኝ ልጆቼን ስለምጠብቅ፣ ስለምከላከል ይህም ሙያ መረጃን የመጠበቅ እና ያለማጋለጥ ስለሆነ ይመስለኛል የወደድኩት” ትላለች።

ከዚህ በተጨማሪ ይህ የሙያ ዘርፍ "በየጊዜው ራሱን የሚያሻሽል ስለሆነ እና እኔ ደግሞ ቶሎ የምሰለች ስለሆንኩኝ ወድጀዋለሁ" ስትል ትናገራለች።

በ2017 እኤአ እንደ አዲስ የተዋወቀችውን ይህንን የሙያ ዘርፍ ለማሳደግ ከቀጥተኛ ትምህርት ውጪ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመውሰድ እና የምስክር ወረቀት በማግኘት እውቀቷን አዳብራለች።

በአሁኑ ጊዜ በዚሁ የሙያ ዘርፍ በጆርጂያ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቷን እየተከታተለች ነው።

በሥራዋ ደግሞ 'ፎርቹን 500' ዝርዝር ውስጥ ካሉ ድርጅቶች ውስጥ በአንዱ የክላውድ ሴክዩሪቲ ኢንጂኒየር ሆና እየሰራች ነው።

ዚነት ወደ አሜሪካ ለኑሮ ጓዟን ጠቅልላ ካቀናች በኋላ ሙያዋን በመቀየር ቀደም ካለው ትምህርቷ የተለየ ነገር አጥንታ ውጤታማ በመሆኗ በአሜሪካ የሚገኙ የተለያዩ ዲጂታል ሚዲያዎች ስለእርሷ ዘግበዋል።

'ዌብ ሜከርስ አዋርድ' የተባለ ለማኅበረሰባቸው ውስጥ እና በሙያቸው ስኬታማ ለሆኑ ሴቶች የሚሰጥን ሽልማትንም አግኝታለች።

በሳይበር ሴክዩሪቲ ሥራዋ ምሳሌ የሚሆን ተግባር ፊውቸርኮን (Futurecon) ከተባለ ድርጅትም እውቅና አግኝታለች።

ይህ ዘርፍ ጥቂት ሴቶች ያሉበት ቢሆንም ዚነት አራት ልጆች እያሳደገች ስኬታማ የመሆኗ ምስጢር “ቁርጠኛ በመሆን በጀመሩት ነገር ላይ ቀጣይነት ባለው መልኩ መሥራት እና በትምህርት ራስን ማሳደግ ነው” ትላለች።

“ሴቶች ይህ ሥራ ለእኔ አይሆንም ለእኔ አይመጥንም ብለን ራሳችንን ማግለል የለብንም፤ ቦታው ይሆነኛል ወይንም እችላለሁ ማለት ይገባናል” ስትል ትመክራለች።

በተለይ አሜሪካ ውስጥ በዚህ የሥራ ዘርፍ ውስጥ “ጥቁር እና ሂጃብ የምትለብስ ብቸኛዋ ሰው መሆን ደስ የሚል ነገር አይደለም። እኔ እንደ እኔ አይነት ብዙ ሰዎችን ነው ማየት የምፈልገው” ትላለች።

ከዚህ ውጪ ግን “ለእኔ ትልቁ ጫና ራሴ በራሴ ላይ የምፈጥረው ነው፤ ለራሴ እንደምችል ለማሳየት የተለያዩ ትምህርቶችን እማራለሁ፣ ከትምህርት ጎን ለጎን እሰራለሁ” ብላለች።