በደቦ ጥቃት ስደተኞችን ለማባረር የሚሞክሩት ደቡብ አፍሪካውያን

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት በአገሪቱ በሚገኙ የውጭ ዜጎች ላይ የሚደርሰው በደል በጣም እንዳሳዘናቸው ተናገሩ።
እአአ በ 2008 በመጤዎች ጥላቻ (ዜኖፎቢያ) የተነሳው አመጽ ማዕከል በሆነችው በአሌክሳንድራ ከተማ ችግሩ የከፋ ነው። አንዳንድ ስደተኞች ከዚያ ወዲህ በፍርሃት እንደሚኖሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል ።
"ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመጡ ሰባት ነበሩ። ሁላችንንም እንድንተኛ አደረጉን። ማሽኖቹን፣ ፀጉር ማድረቂያዎቹን እና ሌሎች ዕቃዎችን ወሰዱ። መሳሪያ ስለያዙ እንዲወስዱ ከመፍቀድ ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበረንም።"
ዴቪድ (ለደኅንነቱ ሲባል ስሙ ተቀይሯል) በጆሃንስበርግ አሌክሳንድራ በሚገኘው የፀጉር ቤቱ ፊት በፍርሃት ተውጦ ተቀምጧል።
ዴቪድ ሞዛምቢካዊ ነው። የደረሰበትን ጥቃት ሲዘረዝር እጆቹን ወደ ታች ይመለከታል። ለጥቃት ተዳረገው የባዕድ አገር ሰው በመሆኑ ነው።
ጥቃት የሚያደርሱበት ደቡብ አፍሪካዊያን ናቸው። ሁሌም ተመሳሳይ ጥያቄ ያቀርቡለታል - ደቡብ አፍሪካን ለቅቆ እንዲወጣ።
"መሄድ እንዳለብን ይነግሩናል። ሥራችንን ዝጉ ይሉናል። የት መሄድ እንዳለብኝ ግን አላውቅም" ይላል።

የውበት ሳሎኑ ከሁለት ሜትር የማይበልጥ ርዝመት ያለው ጠባብ ክፍል ነው። ትንሽ ቢሆንም የዴቪድ የኩራትና የደስታ ምንጭ እንደሆነ ግልጽ ነው። የተለያዩ የፀጉር አሠራሮችን የሚያሳዩ በላስቲክ የተለበጡ ሥዕሎች በግድግዳው ላይ ይታያሉ። በጎን በኩል ደግሞ ሽርጡና እቃዎቹ ተሰቅለዋል።
እዚህ በሚያገኘው ገንዘብ ሞዛምቢክ ውስጥ የሚኖሩ ቤተሰቦቹን ይደግፋል። ነገር ግን ምንም አይነት አደጋ ሊደርስበት ቢችልም ፍላጎታቸውን ለማሟላት መፈለጉ እንደሚያደፋፍረው ተናግሯል።
"እኔን የሚያስጨንቀኝ የቤተሰቦቼ በልቶ ማደር ብቻ ነው" ይላል።
"በየትኛውም ጊዜ ሊገድሉኝ ይችላሉ። ምን እንደሚፈጠር አላውቅም።"
በቅርቡ በደቡብ አፍሪካዋ የአሌክሳንድራ ነዋሪዎች እና በውጭ ዜጋ የንግድ ባለቤቶች መካከል የተፈጠረው ግጭት በአገሪቱ ሌላ ፀረ-ስደተኛ ጥቃት ሊያስነሳ ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል። በ2008 የመጤዎች ጥላቻ የጀመረው እና የተስፋፋው በዚህች ከተማ ውስጥ ነው።
እአአ በ2021 በመጤ ጥላቻ በተፈፀመ ጥላቻ የተገደሉ የውጭ አገር ዜጎች ነበሩ። ቁጥራቸው ከ2020 ጋር ሲነጻጸር በሦስት እጥፍ የሚበልጡ የውጭ ዜጎች ተገድለዋል ሲል የአፍሪካ የፍልሰት እና ማኅበረሰብ ማዕከል አስታውቋል።
ከዚህ ግጭት መንስኤዎች መካከል አንዱ ድህነት ነው። ደቡብ አፍሪካውያን ስደተኞቹ ሥራችንን ወስደዋል በማለት በተደጋጋሚ ይከሳሉ። በአሁኑ ጊዜ መሥራት ከሚችሉት ሦስቱ መካከል አንዱ ሥራ አጥ ነው። ከ24 ዓመት በታች በሆኑት ወጣቶች ዘንድ ይህ አሃዝ ከሦስቱ ወደ ሁለቱ ከፍ ይላል።

አሌክሳንድራ ዱዱላ የሚባል እንቅስቃሴ ተፈጥሯል። እንቅስቃሴው የሥራ ማጣትን እና የከተማው የንግድ ዕድሎችን የማግኘትጉዳይን በዋነኝነት ያነሳል። በዙሉ ቋንቋ ዱዱላ ማለት "ወደኋላ መግፋት" ወይም "ማባረር" እንደማለት ነው።
የሕገወጥ ስደተኞች ናቸው ያሏቸውን ሱቆች እና መደብሮች ዘግተዋል። እንደ ዴቪድ ያሉ የውጭ አገር ዜጎች የዱዱላ እንቅስቃሴ አባላት ጥቃቱን ይፈጽማሉ ይላሉ።
የቢቢሲ የጋዜጠኞች ቡድን በከተማው ሲንቀሳቀስ የዱዱላ የማኅበረሰብ አንቂዎች የስደተኞችን የኢሚግሬሽን ወረቀት እየዞሩ ለመጠየቅ ሲዘጋጁ አግኝቷቸዋል።
ቃል አቀባይዋ አግነስ ማላትጂ ቡድኑ ሕጉን በራሱ ለማስፈጸም መሞከሩ እንዴት እንደሚታይ ጥያቄ ቀርቦላት ነበር።
"እናንተ ወንጀለኞች፣ ሕገ-ወጦች ብላችሁ ስም እንዳወጣችሁልን አይደለም። ይህ ለትክክለኛ ዓላማ የሚታገለውን ማኅበረሰብ መንፈስ እንዲሰብር አንፈቅድም" ትለኛለች።
ባለሥልጣናት የኢሚግሬሽን ሕግን አይተገብሩም ወይም ደቡብ አፍሪካውያን ሲጠቁ ምላሽ አይሰጡም ስትል ትከሳለች።
"መንግሥት በትክክለኛው መንገድ ቢሠራ ሕገ-ወጥነት አይኖርም። እኛም እንዋከባለን። ለምሳሌ መጋቢት 7 በውጭ አገር ዜጎች በዱላና በመሳሪያ ተጠቅተናል። ስለዚህ አንዳንድ ነገሮች ከፍተኛ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል።"

አሌክሳንድራ በአገሪቱ ውስጥ ካሉ በጣም ድሃ ከሆኑ አካባቢዎች አንዷ ናት። በአፍሪካ እጅግ የሃብታሞች መናኸሪያ ከሚባለው የሳንድተን አብረቅራቂ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች በቅርብ ርቀት ተቀምጣለች።
ለሃብት እና ለዕድል ያለው ቅርበት ከአገሪቱም ሆነ ከአህጉሪቱ የሚመጡ አዲስ መጤዎች ዓይናቸውን ጆሃንስበርግ ላይ እንዲጥሉ ሲያደርግ ቆይቷል።
ይህ ደግሞ በአካባቢው ሃብቶች ላይ ጫና ማሳደር ጀመረ። ጫናው እየጨመረ በሄደ ቁጥር በቅርብ ጊዜ በመጡ እና በነባር ነዋሪዎች መካከል ግጭት ሊፈጠር ይችላል ።
የፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የወንጀል ጉዳዮች ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ሉፉኖ ሳዲኪ እነዚህ ሁሉ የጥቃት ዑደቶቹን ለማስረዳት ረዥም መንገድ ይፈልጋል። ይህንን ለማስረዳትም 'ስትሬይን' የተባለውን ንድፈ ሐሳብን ተጠቅመዋል።
"ሁላችንም ጥሩ ህይወት እንፈልጋለን። ሁላችንም ግን ጥሩ ህይወት ማግኘት አንችልም።"
"በሳንድተን እንደ መጸዳጃ ቤት ስትጠቀምበት የነበረውን ባልዲ ለማውጣት በማለዳ መነሳት አይጠበቅብህም። ቧንቧ ስትከፍት ውሃ ታገኛለህ። እነዚህን ሁሉ ነገሮች በቀላሉ እጅህ ላይ ታገኛለህ። መንገድ ተሻግረህ ወደ አሌክሳንድራ ስታቀና ታሪኩ ሌላ ነው።"
"ብስጭትህን እንደሚያጎላ መስታወት ማለት ነው። ያለውን ልዩነት ነጋ ጠባ ከፊትህ ትመለከተዋለህ። የምትፈልገው ነገር ከመንገድ አለ አንተ ቤት ግን አታገኘውም። አንዳንድ ጊዜ ለዚህ መልስ ከሌለህ ቀላሉ ነገር ሌላውን ማጥቃት ነው።"
የ19 ዓመቱ ጆን (ለደኅንነቱ ሲባል ስሙ የተቀየረ) ባለፈው ዓመት ከሞዛምቢክ ጆሃንስበርግ ከደረሰ በኋላ እሱም መሰል ጥቃቶችን እያስተናገደ መሆኑን ይገልጻል።
እሱ እና ጓደኞቹ ለከተማው መንገደኞች የሚሸጡት ሥጋ እና ገንፎ የሚያበስሉበት የመንገድ ዳር መደብ አላቸው።
የዱዱላ እንቅስቃሴ አባላት ነን የሚሉ ደቡብ አፍሪካውያን ብዙ ጊዜ ጥቃት እንዳደረሱባቸውና ንብረታቸውን እንደሰረቁ ይናገራል።
"ዱዱላ አባላት በቆዳ አለንጋ ገረፉን፣ መቱን። ሲመጡ ዕቃችንን ጥለን መሮጥ አለብን።"
ለጆንም ሕልሙ በሞዛምቢክ የሚኖሩ ቤተሰቦቹን መደገፍ ነው። የመጀመሪያ መኪናውን ለመግዛትም በቂ ገንዘብ መቆጠብ እንደሚችሉ ተስፋ አድርጓል።
ሕልሞቹ እውን ስለመሆናቸው እርግጥ አይደለም።
"ወደ ሌላ አገር ስለመሄድ እያሰብኩ በጣም ፈርቻለሁ። ሞዛምቢክ ውስጥ በደቡብ አፍሪካ ያለንበትን ሁኔታ ስለሚያውቁ ስለእኛ ይጸልያሉ" ይላል።












