የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት የውጭ ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አወገዙ

አመጸኞችና ፖሊስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ዜጎች ንብረት ላይ የተፈጸመው ዝርፊያና ጥቃትን እንደሚያወግዙት አስታወቁ።

ማክሰኞ ዕለት ፕሬዝደንቱ ''ለተፈጸመው ነገር ምንም አይነት ምክንያት ሊቀመጥለት አይችልም፤ ደቡብ አፍሪካውያን ሌሎች አፍሪካውያንን ማጥቃት አይችሉም'' ሲሉ ተደምጠዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም ከአርባ በላይ ደቡብ አፍሪካውያን ከሰኞ አመሻሽ ጀምሮ በቁጥጥር ስር ውለዋል። ፖሊስ አመጸኞቹን ለመቆጣጠር አስለቃሽ ጭስ የተጠቀመ ሲሆን ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ መሆን ሲጀምሩ ደግሞ የጎማ ጥይቶችንም ጭምር ተጠቅሞ ነበር ተብሏል።

እስካሁን ቢያንስ አምስት ሰዎች መሞታቸውም ተሰምቷል።

''የተፈጸመው ዝርፊያ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የሌለው ነው፤ ይህ ነገር ደቡብ አፍሪካ ውስጥ እንዲሆን አንፈቅድም'' ብለዋል ፕሬዝዳንቱ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት የቪዲዮ መልእክት።

አክለውም ''ድርጊቱ በአስቸኳይ መቆም አለበት'' ብለዋል።

በሌላ በኩል የአፍሪካ ህብረት በበኩሉ ተቀባይነት የሌለው ድርጊት ያለውን ተግባር በእጅጉ እንደሚቃወመው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ዝርፊያውና አመጹ ማክሰኞ ዕለትም የቀጠለ ሲሆን አሌክሳንድሪያ ወደተባለችው ጆሃንስበርግ ክፍል መስፋፋቱ ተሰምቷል። አንዳንድ ነዋሪዎችም በሕገ-ወጥ መንገድ ወደሃገራችን የገቡ ስደተኞችን መንግስት ያባርልን ሲሉ ቁጣቸውን ገልጸዋል።

የተፈጠረው ምንድነው?

ጂፒ በተሰኘው አካባቢ የሬስቶራንት ባለቤት የሆነው አቶ ተከስተ ሹምዬ ስለሁኔታው ጠይቀነው ነበር።

''የሌላ ሃገር ዜጎች የሆኑ አፍሪካውያን ላይ ነው ጥቃቱ የተሰነዘረው። በተለይ ደግሞ የመኪና ሽያጭ ላይ የተሰማሩ ናይጄሪያውያን ላይ ከእሁድ ጀምሮ ጥቃት ተፈጽሟል። እስካሁን በሰማሁት ዜና ከ50 በላይ መኪና ተቃጥሏል''በማለት ሁኔታውን ያስረዳል።

Policeman confronting a woman

የፎቶው ባለመብት, AFP

እሁድ ጠዋት ላይ ሶስት ሰዎች መገደላቸውን እና አንድ ህንጻ እንደተቃጠለ ሁኔታውም እስካሁን እንዳልተረጋጋ ተከስተ ነግሮናል።

ተከስተ እንደሚለው በግምት ከአስር ቀናት በፊት ፕሪቶሪያ በተባለችው ከተማ የሃገሬው ታክሲ ሾፌሮች ከናይጄሪያውያን ሾፌሮች ጋር ተጋጭተው በናይጄሪያውያን በተተኮሰ ጥይት አንድ ደቡብ አፍሪካዊ መሞቱን ተከትሎ ትልቅ ብጥብጥ ተነስቶ ነበር።

በዚህም ምክንያት ላለፉት ቀናት ናይጄሪያውያንን ጨምሮ ከሌላ ሃገራት የመጡ ዜጎችን ንብረት መዝረፍና ማቃጠል ተበራክቶ እንደነበር ተከስተ ይናገራል።

ብዙ ጥቃት የደረሰባቸው ናይጄሪያውያን እንደመሆናቸው በናይጄሪያዋ ሌጎች ከተማ የሚገኙ የደቡብ አፍሪውያን ሱፐርማርኬቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው አንድ አይን እማኝ ለቢቢሲ አረጋግጧል።

አንድ ሌላ የአይን እማኝ ደግሞ ሱፐርማርኬቱ የሚገኝበት መንገድ ላይ የሁለት ሰዎች ሬሳ መመልከቱን ገልጿል።

የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሞሃሙዱ ቡሃሪ በበኩላቸው የሃገራቸውን ቁጣ ለመግለጽና የዜጎቻቸውን ደህንነት ለማረጋገጥ ማክሰኞ ዕለት የልዑካን ቡድን ወደ ደቡብ አፍሪካ መላካቸውን አስታውቀዋል።

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲም ጉዳዩ እስኪጣራና ዝርፊያዎቹ እስከሚቆሙ ድረስ ዜጎች ሱቆቻቸውን እንዲዘጉ አሳስቧል። አመጽ ሊነሳባቸው ከሚችላባቸው ቦታዎች እራሳቸውን እንደያርቁና ውድ የሆኑ ጌጣጌጦችን እንዳያደርጉም አስጠንቅቋል።

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም በበኩላቸው ደቡብ አፍሪካውያን ወጣቶች ከሌላ ሃገራት የመጡ ዜጎች ስራችንን ቀምተውናል በሚል መነሻ እራሳቸውን በማደራጀት ሱቆች ላይ የመዝመት ሁኔታ ታይቷል ይላሉ።

''ከዚህ ጋር በተያያዘ ዜጎቻችን በስነልቦናም ይሁን ከዝርፊያው ጋር በተገናኘ የሚያጋጥማቸው ችግር አለ፤ ይህንንም ለመፍታት ከሃገሪቱ የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር የሚቻለውን ሁሉ እየተደረገ ነው''።

የዛምቢያ ትራንስፖርት ሚኒስትር መስሪያ ቤት ደግሞ ትልልቅ የጭነት መኪኖች ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚደረጉትን ጉዞ ለጊዜው እንዲያቆሙ አድርጓል።