ደቡብ አፍሪቃዊቷን የቦክስ ቻምፒዮን ገድሏል የተባለው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ውሏል

ደቡብ አፍሪቃዊቷን የቦክስ ቻምፒዮን የገደለው ተያዘ

የፎቶው ባለመብት, Department of Arts & Culture/SA

ደቡብ አፍሪቃዊቷን የቡጢ ተፋላሚ ቻምፒዮን በክፉ ሁኔታ ተኮሱ ገድሏል የተባለ አንድ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ውላል።

ሊያንድሬ ጄንግልስ [በቅፅል ስሟ ቤቢ ሊ] በመባል የምትታወቀው ቦክሰኛ በምስራቃዊ ደቡብ አፍሪቃ አርብ ዕለት ነው በተተኮሰባት ጥይት የሞተችው።

ባለሥልጣናት ገዳዩ የደቡብ አፍሪቃ ፖሊስ አግልግሎት አባል ነው ሲሉ አሳውቀዋል።

በጥቃቱ ቦክሰኛዋ ሕይወቷ ሲያልፍ አብረዋት መኪና ውስጥ የነበሩት እናትዋ ጉዳት እንደደረሰባቸው ታውቋል።

ወጣቷ ደቡብ አፍሪቃዊት ቦክሰኛ ባለፉት 9 ግጥሚያዎቿ ያልተሸነፈች ብርቱ ተቧቃሽ ነበረች። ለሚቀጥለው ውድድሯም ዝግጅት ላይ እንደነበረች ተሰምቷል።

በጥቃቱ ሥፍራ አብሯት ነበረ የተባለው ይህ የ37 ዓመት ግለሰብ የቦክሰኛዋ የአሁን ወይም የቀድሞ የፍቅር ጓደኛ ሳይሆን አልቀረም የሚሉ ዘገባዎች እየወጡ ነው።

ለሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ቃላቸውን የሰጡት የፖሊስ አፈ-ቀላጤ የጥቃቱ መንስዔ በጥንዶቹ መካከል የተከሰተ ግጭት ሳይሆን አይቀርም ብለዋል።

ቃል አቀባዩ የፖሊስ ባልደረባ የሆነው ግሰለብ ጓደኛው ላይ በተከታታይ ተኩሷል፤ ጥቃት የደረሰባት ግለሰብም ወዲያውኑ ሕይወቷ ሊያልፍ ችሏል ሲሉ ተናግረዋል።

በቁጥጥር ሥር የዋለው ግለሰብ ሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሎ ይጠቃል።

በርካታ ደቡብ አፍሪቃውያን ጥቃቱን በማሕበራዊ ድረ-ገፆቻቸው አማከይነት እየኮነኑት ይገኛሉ።