በኤርትራ ሥልጠና ላይ ከነበሩ ወታደሮች መካከል የመጀመሪያዎቹ ወደ ሶማሊያ ተመለሱ

የፎቶው ባለመብት, @hawelti
ኤርትራ ውስጥ ወታደራዊ ሥልጠና ሲወስዱ ከነበሩት ወታደሮቹ መካከል የመጀመሪያዎቹ ወደ አገራቸው መመለሳቸውን የሶማሊያ መንግሥት አስታወቀ።
ከጥቂት ዓመት በፊት በምስጢራዊ ሁኔታ ከሶማሊያ ተመልምለው ለሥልጠና ወደ ኤርትራ የተላኩት የነበሩት ወታደሮች ጉዳይ ባለፈው ዓመት በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ውዝግብን አስንስቶ ነበር።
የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር አብዲካዲር ሞሐመድ ሞቃዲሾ ውስጥ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የመጀመሪያው ዙር ተመላሽ ወታደሮች ወደ አገራቸው መግባታቸውን ገልጸዋል።
ነገር ግን በሥልጠና ላይ ከነበሩት ወታደሮች መካከል ምን ያህሎቹ ወደ ሶማሊያ እንደተመለሱ ቁጥራቸውን አልተናገሩም።
በቀድሞው ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ፋርማጆ የሥልጣን ዘመን ለሥልጠና ስለተላኩት ወታደሮች ጉዳይ ለረጅም ጊዜ ምንም ሳይባል ቆይቶ፣ አዲሱ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ሁለት ጊዜ ወደ ኤርትራ ሄደው ሰልጣኞቹን ጎብኝተዋቸዋል።
ወታደሮቹ ከኤርትራ መቼ እንደሚመለሱ ሳይታወቅ ከቆየ በኋላ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የአፍሪካ አሜሪካ ጉባኤ ለመሳተፍ አሜሪካ የነበሩት ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ሚኒሶታ ግዛታ ውስጥ ለሚኖሩ ሶማሊያውያን ስለወታደሮቹ መመለስ በእርግጠኝነት ተናግረው ነበር።
ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ይህንን ካሳወቁ ከቀናት በኋላ በኤርትራ ውስጥ በሥልጠና ላይ ከሚገኙት አምስት ሺህ የሶማሊያ ወታደሮች መካከል የመጀመሪያው ቡድን በቀናት ውስጥ ወደ አገሩ መመለሱን የመከላከያ ሚኒስትሩ አሳውቀዋል።
የሶማሊያ መንግሥት ሬዲዮ እንደዘገበው ወታደሮቹን ወደ ሶማሊያ ሙሉ ለሙሉ የመመለሱ ተግባር አስከ ቀጣዩ ጥር ወር ድረስ እንደሚጠናቀቅ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, @hawelti
ከሁለት ዓመት በፊት በቀድሞው ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ፋርማጆ አማካይነት ለወታደራዊ ሥልጠና ወደ ኤርትራ የተላኩት አምስት ሺህ የሶማሊያ ምልምል ወራደሮች ጉዳይ በውጪም ሆነ በአገር ውስጥ ጥያቄን አስከትሎ ነበር።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደውን ጦርነት ተከትሎ እነዚህ የሶማሊያ ወታደሮች ከኤርትራ ሠራዊት ጎን ተሰልፈው በትግራይ በሚካሄደው ጦርነት ውስጥ ተሳትፈዋል መባሉ ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ተፈጥሮ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ የወታደሮቹ ቤተሰቦች ዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ውስጥ አደባባይ ወጥተው መንግሥት ልጆቻቸው ያሉበትን ሁኔታ እንዲያሳውቅና ወደ አገራቸው እንዲመልስ ተቃውሟቸውን ገልጸው ነበር።
የኤርትራም ሆነ የሶማሊያ ባለሥልጣናት ግን ወታደሮቹ በሥልጠና ላይ እንጂ በኢትዮጵያው ጦርነት ውስጥ አለመሳተፋቸውን በመግለጽ የተሰነዘረውን ክስ ውድቅ አድርገውታል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ምክር ቤት መጋቢት ወር ላይ ባወጣው ሪፖርት በኤርትራ የሰለጠኑ የሶማሊያ ወታደሮች ከኤርትራ ወታደሮች ጋር በመሆን በትግራይ ጦርነት መሳተፋቸውን ይፋ አድርጎ ነበር።
በኤርትራ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ያተኮረው ሰነዱ በሥልጠና ላይ የነበሩ የሶማሊያ ወታደሮች ወደ ትግራይ ጦር ግንባሮች መወሰዳቸውንና እንዲሁም በአክሱም እንደነበሩ የሚገልጹ መረጃዎችን ይዟል።
ወታደሮቹን ወደ አገራቸው የመመለስን ጉዳይ በተመለከተ ዝምታን መርጠው የነበሩት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ፣ በምርጫ ተሸንፈው ሥልጣን ሲያስረክቡ በኤርትራ ሥልጠና የወሰዱ 5 ሺህ ወታደሮች መኖራቸውን ይፋ አድርገዋል።
ፋርማጆ ወታደሮቹ በኤርትራ የነበራቸውን ሥልጠና ከአንድ ዓመት በፊት ማጠናቀቃቸውን ገልጸው፣ ሶማሊያ ውስጥ ባለው ፖለቲካዊ ሁኔታ እና በምርጫ ላይ ተጽእኖ እንዳያሳድሩ በመስጋት የመመለሳቸው ሁኔታ መዘግየቱን ተናግረዋል።
በሥልጣን ርክክቡ ወቅትም ፋርማጆ የወታደሮቹን ፋይል ለአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ተላልፎ መሰጠቱን አረጋግጠዋል።
በምስጢር ተመልምለው ወደ ኤርትራ የተላኩት አምስት ሺህ የሚሆኑት የሶማሊያ ወታደሮች ጉዳይን በተመለከተ የሶማሊያ ፖለቲከኞች ሲወዛገቡ ቆይተዋል።
ለሁለተኛ ጊዜ አገሪቱን ለመምራት ወደ መንበራቸው የተመለሱት ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ በበኩላቸው ሥልጣን በተረከቡበት ጊዜ ወታደሮቹ ወደ ወደ አገራቸው በአፋጣኝ እንደሚመለሱና አገሪቱ ከአልሻባብ ጋር በምታደርገው ፍልሚያ ላይ እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በቀዳሚነት ከጎበኟቸው አገራት መካከል ኤርትራ አንዷ ስትሆን፣ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሁለት ጊዜ ወደ አሥመራ በማቅናት ከኤርትራ ባለሥልጣንት ጋር ተወያይተዋል።
ባለፈው ዓመት ሐምሌ እና በዚህ ዓመት ኅዳር ወር ወደ ኤርትራ የተጓዙት ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ በሥልጣና ላይ ያሉ ወታደሮቻቸውን መጎብኘታቸውንና በምረቃ ሥነ ሥርዓታቸው ላይ መታደማቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንቱ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ከታጣቂው አስላማዊ ቡድን አልሻባብ ጋር ከባድ ፍልሚያ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ባለፉት ወራትም በርካታ አካባቢዎችን መልሰው ለመቆጣጠር ችለዋል።
መንግሥታቸው ይህንንም ዘመቻ አጠናክሮ በመቀጠል ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት አለው የሚባለውን ቡድን በማዳከም ለመደምሰስ ጥረት እያደረገ ነው።












