ኤርትራ እና ሶማሊያ መከላከያ እና ደኅነትን ያጠቃለለ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ

የፎቶው ባለመብት, shabait
ሁለቱ የኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት ኤርትራ እና ሶማሊያ ምጣኔ ሃብታዊ እና የደኅንነት ጉዳያዎችን ያጠቃለለ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።
ይህ የመግባቢያ ሰነድ የተፈረመው የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ የኤርትራ ለቀናት ያደረጉት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሲያጠናቅቁ ነው።
የሁለቱ አገራት መሪዎች ዛሬ ሐምሌ 05/2014 ዓ.ም. በኤርትራ መዲና አሥመራ በሰባት ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
በሁለቱ አገራት ሕዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጎልበት እንዲሁም የሁለቱን አገራት ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ብሔራዊ ፍላጎቶችን ለማጠናከር ኤርትራ እና ሶማሊያ ተስማምተዋል።
በንግድ፣ በኢንቨስትመን፣ በውሃ ደኅንነት፣ በግብርና፣ በጤና እና በትምህርት ላይ ትኩረት በማድረግም ምጣኔ ሃብታዊ ግንኙታቸውን ለማጠናከር መስማማታቸውን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የሶማሊያው አቻቸው ሐሰን ሼክ ሞሐመድ በፊርማቸው አረጋግጠዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ሰላም፣ መረጋጋትን እና ደኅንነትን ለማረጋገጥ ሁለቱ አገራት የመከላከያ እና የደኅንነት ትብብራቸውን ለማጠንከር ተስማምተዋል።
ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ የአራት ቀናት ጉብኝታቸውን አጠናቀው ዛሬ ማክሰኞ ረፋድ ላይ ወደ አገራቸው ከመመለሳቸው በፊት በኤርትራ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን መጎብኝታቸውን ከአሥመራ የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በኢሳያስ አፈወርቂ ታጅበው፤ በደቡባዊ እና ቀይ ባህር የኤርትራ አካባቢዎች ጉብኝት ማድረጋቸው ተመልክቷል።
የፕሬዝንደት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ የኤርትራ ጉብኝነትን ተከትሎ የበርካቶችን ቀልብ ስቦ የነበረው ጉዳይ በኤርትራ ሲሰለጥኑ ነበሩ የተባሉ በርካታ የሶማሊያ ጦር አባላት በይፋ ተመርቀዋል መባሉ ነው።
ላለፉት ዓመታት ሞቃዲሾም ሆነች አሥመራ የሶማሊያ ወታደሮች በኤርትራ ስለመኖራቸው በይፋ ያሉት ነገር አልነበረም።

የፎቶው ባለመብት, @HAWELTI
ይልቁንም በሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በእርስ ጦርነት በኤርትራ የሚገኙ የሶማሊያ ወታደሮች ከአዲስ አበባ ጎን ተሰልፈው የትግራይ ኃይሎችን ወግተዋል የሚል መረጃ በስፋት ሲጋራ ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ከአንድ ዓመት በፊት ባወጣው ሪፖርት በኤርትራ የሰለጠኑ የሶማሊያ ወታደሮች ከፌደራሉ መንግሥት ጎን በመሰለፍ በትግራይ ጦርነት ተሳትፈዋል ብሎ ነበር።
ነገር ግን በወቅቱ ሶማሊያ ወታደሮቿ በኢትዮጵያ በተካሄደው ውጊያ ላይ አልተሳተፉም ብሏል። የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደርም የሶማሊያ ወታደሮች በትግራዩ ጦርነት ውስጥ ተሳትፈዋል የሚለውን ክስ ማስተባበሉንም በወቅቱ ብሉምበርግ ዘግቧል።
የሶማሊያውን ፕሬዝደንት ጉብኝነት ተከትሎ የኤርትራ መንግሥት እሁድ ሐምሌ 03/2014 ለሦስት ዓመታት ወታደራዊ ሥልጠና ሲወስዱ የነበሩት የሶማሊያ ወታደሮች ተመርቀዋል ብሏል።
በዚህ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ምን ያህል የሶማሊያ ወታደሮች ሥልጠናቸውን እንዳጠናቀቁ፣ ምን አይነት ሥልጠናዎችን እንደወሰዱ፣ ሶማሊያውያኑ ወደ ኤርትራ መቼ እንደገቡም ሆነ መቼ ወደ ትውልድ አገራቸው እንደሚመለሱ የተገለጸ ነገር የለም።












