ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ የታይም መጽሔት የዓመቱ ምርጥ ሰው ተብለው ተሰየሙ

የፎቶው ባለመብት, Time Magazine
ሩስያ ዩክሬንን ከወረረችበት አንስቶ በዓለም ሚዲያዎች ላይ የማይጠፉት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ በታይም መጽሔት የዓመቱ ምርጥ ሰው ተብለው ተሰየሙ።
ታይም መጽሔት ከፕሬዝዳንቱ በተጨማሪ ለማይበገረው የዩክሬናውያን የትግል መንፈስም ዕውቅና ሰጥቷል።
የመጽሔቱ ሽልማት ባለፉት 12 ወራት ውስጥ በዓለም አቀፍ ክስተቶች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖንን ማምጣት ለቻለ የሚበረከት ነው።
በዘንድሮው የመጽሔቱ የመጨረሻ እጩዎች ከነበሩት የኢራን ተቃዋሚዎች፣ የቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ እና የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይገኙበታል።
በመጨረሻም ፕሬዝዳንት ዜለንስኪን የመረጠ ሲሆን ውሳኔውንም አስመልክቶ የመጽሔቱ አዘጋጅ “በጣም ግልጽ የሆነ ነው” ብለዋል።
“በተከፋፈለችው ዓለም ውስጥ የሰው ልጅ አንድ ላይ የመጣበት ምክንያት ነው” ሲሉ አዘጋጁ ኤድዋር ፈለንስታል የዩክሬኑ ጦርነት በዓለም ላይ ስላለው ስፍራ አስፍረዋል።
በተጨማሪም በመጽሔቱ ላይ ዕውቅና ከተሰጠው የዩክሬናውያን መንፈስ ከጀርባ ሆነው ድጋፍ የሰጡትን ጨምሮ በተለያየ መንገድ የታገሉትን በዓለም ዙሪያ ያሉ ዩክሬናውያንን እንደሚያመለክት ተናግረዋል።
ከነዚህም መካከል በሺዎች ለሚቆጠሩ ዩክሬናውያን በነጻ ምግብ የለገሱትን ሼፍ ሌቭገን ክሎፖቴንኮ እንዲሁም በሩሲያ ጦር ለሦስት ወር ተይዛ የነበረችው የሕክምና ባለሙያ ዩሊያ ፓዬቭስካ ተጠቅሰዋል።
መጽሔቱ ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ዩክሬናውያንን በማነሳሳትና የሩስያን ወረራ በመቃወም ባሳዩት ድፍረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና አግኝተዋል ብሏል።
“ዜለንስኪ እንደ ጦርነቱ መሪነታቸው ስኬታቸው በብዙዎች ዘንድ መደፋፋርንም መፍጠር መቻላቸው ነው” ብለዋል አዘጋጁ
በጦርነቱ የተጎዱትን ለመርዳት ወደ ዩክሬን ያቀኑት እንግሊዛዊው የቀዶ ጥገና ሐኪም ዴቪድ ኖት በመጽሔቱ ሽፋን ላይ ምሥላቸው ከወጡ ሌሎች በርካታ ሰዎች አንዱ ናቸው።
የኢራን ሴቶች የታይም መጽሔት የ2022 ጀግኒቶች የሚል ዕውቅና ሲቸራቸው የኮሪያው የፖፕ ሙዚቃ ባንድ ብላክ ፒንክ የዓመቱ አዝናኝ የሚል ስያሜን አግኝቷል።
በተጨማሪም አሜሪካዊው ቤዝቦል ተጫዋች አሮን ጀጅ የዓመቱ ምርጥ አትሌት በመባል ዕውቅና ያገኘ ሲሆን የማሌዢያ ተዋናይት ሚሼል ኢዩ የዓመቱ ምርጥ አርዓያ ተብላለች።












