ኢሰመኮ በኮንሶ ያሉ ተፈናቃዮች የሰብዓዊ መብት አያያዝ የከፋ ነው አለ

ተፈናቃይ አርሶ አደር

የፎቶው ባለመብት, EHRC

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኮንሶ ያሉ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰብዓዊ መብት አያያዝ የከፋ ነው አለ።

ኢሰመኮ ይህን ያለው በደቡብ ክልል በኮንሶ ዞን እና በሦስት ልዩ ወረዳዎች በሚገኙ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታን በተመለከተ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ነው።

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ በኮንሶ ዞን፣ በአሌ ልዩ ወረዳ፣ በደራሼ ልዩ ወረዳ እና በአማሮ ልዩ ወረዳ በአጠቃላይ የተመዘገቡ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ከ145 ሺህ በላይ መሆኑን ገልጿል።

ኮሚሽኑ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮቹ ሰብዓዊ ድጋፍ እንደማያገኙ እና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚኖሩ ገልጿል።

የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ተቋሙ ክትትል ባደረገባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች “በቂ የሰብዓዊ ድጋፍ ባለማግኘታቸው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ከመሆኑም ባሻገር፣ በተለያዩ ጊዜያት በዚህ አካባቢ የሚያገረሹ ግጭቶች የተፈናቀሉ ሰዎችን ለተደራራቢ ጉዳት እና መፈናቀል እየዳረጉ ነው” ብለዋል።

ስለዚህም የሚመለከታቸው አካላት ለመፈናቀል መንስዔ የሆኑ ግጭቶችን ማስወገድ፣ በቂ የሰብዓዊ ድጋፍ ማቅረብ እና ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ላይ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ይህን ሪፖርት ያወጣው የአገር ውስጥ ተፈናቃዮቹ በሚገኙባቸው መጠለያ ጣቢያዎች እና ተቀባይ ማኅበረሰብ ጋር በመዘዋወር ተፈናቃዮችን፣ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎችን እና ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በማነጋገር እና የሰነድ ማስረጃዎች በማሰባሰብ ነው።

ተፈናቃዮች ቀያቸውን ጥለው እንዲሄዱ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል አንዱ እና ዋነኛው ግጭት መሆኑን ኮሚሽኑ ጠቁሟል።

የአካባቢውን ነዋሪዎች ለግጭት ከሚዳርጉ ምክንያቶች መካከልም የእርሻ፣ የግጦሽ መሬት እና የደን ሃብት ይዞታ ይገባኛል የሚለው ምክንያት አንዱ ነው። ሌሎች ጉዳዮች ደግሞ የአስተዳደር መዋቅር በሚጠይቁ እና መዋቅሩን በሚቃወሙ እንዲሁም የአስተዳደር ወሰን ግጭት በምክንያት ነት ይጠቀሳል።

ኢሰመኮ የክልሉ እና ብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ለተፈናቃዮች በቂ እና ጊዜውን የጠበቀ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያቀርቡ እና እንዲያስተባብሩ ጠይቋል።

ለመፈናቀል መንስኤ የሆኑ የአስተዳደር መዋቅር እና የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎችን የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ባሳተፈ መልኩ አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጥ ይገባልም ብሏል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንሶ አካባቢ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች በማኅበረሰቦች መካከል በተደጋጋሚ በሚከሰቱ ግጭቶች ከሚፈናቀሉት በተጨማሪ፤ የበርካታ ሰዎች ሕይወት የጠፋ ሲሆን፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረትም ለውድመት ተዳርጓል።