ከምዕራብ ወለጋ ቶሌ ዳግም ጥቃትን በመስጋት ነዋሪዎች ሸሽተው መውጣታቸውን ተናገሩ

ቀደም ባለው ጊዜ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በመሸሽ ከወለጋ ተፈናቅለው አማራ ክልል ሐይቅ ከተማ ውስጥ በተፈናቃዮች ማዕከል ውስጥ የሚገኙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከዚህ ቀደም በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በመሸሽ ከወለጋ ተፈናቅለው አማራ ክልል ሐይቅ ከተማ ውስጥ በተፈናቃዮች ማዕከል ውስጥ የሚገኙ

ባለፈው ዓመት ሰኔ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በታጣቂዎች የተገደሉባት ቶሌ ቀበሌ ነዋሪዎች ዳግም ተመሳሳይ ጥቃት ሊፈፀምብን ይችላል በሚል ስጋት አካባቢያቸውን ለቀው መውጣታቸውን ገለጹ።

ከአራት ወራት በፊት ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ውስጥ መንግሥት በሽብርተኛ ቡድንነት ሰይሞ ሸኔ በሚል የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት 400 የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂዩማን ራይትስ ዎች ገልጾ ነበር።

በአብዛኛው የአማራ ብሔር ተወላጆች የሆኑ ነዋሪዎችን ኢላማ አድርጎ በነበረው ጥቃት በርካታ ሴቶችና ህጻናት ሰለባ በሆኑበት በዚያ ጥቃት የተገደሉት ነዋሪዎች ቁጥር 338 መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ መግለጹ ይታወሳል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ይህ ጥቃት ከተፈጸመ ከጥቂት ወራት በኋላ የአማር ብሔር ተወላጅ የሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ተመሳሳይ ጥቃት ሊፈጸም ይችላል በሚል የደኅንነት ስጋት ከቶሌ ቀበሌ ተፈናቅለው መውጣታቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የቀበሌው ነዋሪዎች በአካባቢው የነበረው የፌደራል መንግሥቱ የፀጥታ ኃይሎች እንዲወጡ እንደነገሯቸውና አርብ ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ተነስተው ለሰዓታት በመጓዝ በምሥራቅ ወለጋ በሚገኘው አርጆ ጉደቱ ወደተባለ አካባቢ መሸሻቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሁለት ልጆች እናት የሆነች ሴት ከዚህ ቀደም ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ በስፍራው የፌደራል ፖሊስ ተሰማርቶ እንደነበረ ገልጻ፣ ባለፈው ዓርብ ጥቅምት 25/2015 ዓ.ም. ከቦታው እንደሚለቁ ነግረውን “ሕይወታችሁን ለማትረፍ ውጡ እንሸኛችሁ” አሉን ስትል ትናገራለች።

ሌላኛው የቶሌ ቀበሌ ነዋሪ የሆነው እና የአራት ልጆች አባት የሆነው ግለሰብ እንደገለጸው፣ በስፍራው ሰፍረው የነበሩት የፌደራል ፖሊስ አባላት ከእኩለ ለሊት በኋላ 9 ሰዓት ላይ መኖሪያ ቤታቸው ድረስ በመምጣት አካባቢውን ጥለው እንዲወጡ እንደነገሯቸው ለቢቢሲ ተናግሯል።

“ከእንቅልፍ ቀስቅሰው ተነሱ አሉን። የምናውቀው ነገር የለም በእግር ተጉዘን አምስት ሰዓት አርጆ ደረሰን” የሚለው ነዋሪው ከቀያቸው በድንገት በመውጣታቸው ምንም ነገር ሳይዙ መውጣታቸውን ያስረዳሉ።

ከስድስት የቤተሰብ አባላቷ ጋር ከቶሌ ቀበሌ የወጣች ሌላ እናት ደግሞ “ከዚህ በፊት ብዙዎች እዚያው ከፊታችን ታርደውም፣ ተቃጥለውም ሲገደሉ ስላየን ሕይወታችንን ለማዳን ስንል ወጣን” ስትል ትናገራለች። 

ቢቢሲ በአካባቢው ስላለው ሁኔታ ከዞኑ ባለሥልጣናት እንዲሁም ከወረዳው አስተዳደሮች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካለትም።

ከዚህ በፊት በቶሌ ቀበሌ በንጹሃን ዜጎች ላይ ግድያ የተፈጸመው የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጥቃቱን ለመከላከል በቂ ጥበቃ ባለማደረጋቸው ነው ተብሎ ነበር።

ካርታ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሂዩማን ራይትስ ዎች ባለፈው ሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. በምዕራብ ኦሮሚያ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች በታጣቂዎች ሲገደሉ የኢትየጵያ መንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ጥቃቱን ለመከላከል በቂ ጥበቃ አላደረጉም ነበር ሲል ባወጣው መግለጫ ብሎ ነበር።

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቅዳሜ ሰኔ 11/2014 ዓ.ም. በኃይል የታጠቁ ኃይሎች ስምንት ሰዓታት በፈጀ ጥቃት ሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ 400 የሚጠጉ ሰላማዊ የአማራ ተወላጆችን ቶሌ እና ሰኔ ቀበሌዎች ውስጥ ገድለዋል ብሏል።

ከዚህ ቀደም በተፈፀመው ጥቃት ከአንድ በላይ የቤተሰብ አባላቶቻቸውን እንዳጡ የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፣ ያለምንም ሰብዓዊ ድጋፍና መጠለያ ሕጻናት እና ነፍሰጡር እናቶች ጭምር ለበሽታ መጋለጣቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በታጣቂ ቡድኑ ጥቃት ሊፈጸምብን ይችላል በሚል ስጋት ቀያቸውን ለቀው የወጡት ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት አስፈላጊ የደኅንነት ከለላ እና ሰብዓዊ አርዳታ እንዲደረግላቸው መንግሥትን ተማጽነዋል።

ነዋሪዎቹ፣ አካባቢያቸውን ለቀው የወጡት በቁጥር ከ1500 በላይ እንሚሆኑ የገመቱ ሲሆን፤ የአማራ ማኅበር በአሜሪካ ከሦስት ቀናት በፊት በትዊተር ገጹ ባጋራው መግለጫ፣ ከሦስት ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን እና ንብረታቸውም በሌሉበት እየወደመ እና እየተዘረፈ መሆኑን አስታውቋል።

ማኅበሩ በዚሁ መግለጫው፣ በምዕራብ ወለጋ፣ ጊምቢ ወረዳ የምትገኘውን ቶሌ ቀበሌ በታጣቂው ቡድን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ቁጥጥር ሥር መሆኗን አስታውቆ ነበር።

ይሁን እንጂ መንግሥት ኦነግ ሸኔ በሚል በሽብርተኝነት የፈረጀውና ይህ ቡድን ግን ቶሌ ቀበሌን በቁጥጥሩ ስር ስላማስገባቱ አስካሁን ያለው ነገር የለም።

ታጣቂ ቡድኑ እሁድ ዕለት ቶሌ ቀበሌ ከምትገኝበት ወረዳ ጊምቢ በ100 ኪሎ ሜትር ገደማ በምትርቀው ነቀምት ከተማ ዘልቆ በመግባት ተኩስ መክፈቱን ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ታጣቂው ቡድኑ በስፋት በሚንቀሳቀስበት የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙ ከሰባት በላይ ወረዳዎችን ባለፈው ሳምንት መያዙን ገልጿል።

ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች እና አንድ የዞኑ ባለሥልጣንም፣ መንዲ፣ ቂልጡ ካራ እና ለታ ሲቡ ተብለው የሚጠሩ ከተሞችን መቆጣጠራቸውንና በዚያም ንብረት ማውደማቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሽብር ቡድንነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰየመው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በተለይ በምዕራባዊ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከሚፈጸሙ ጥቃቶች ጋር ስሙ ይነሻል።

ቡድኑ በተለያዩ ጊዜያት በነዋሪዎች፣ በመንግሥት ሠራተኞች፣ በአካባቢ በለሥልጣናት ላይ እና ተቋማት ላይ ጥቃት ሲፈጽም መቆየቱን በተደጋጋሚ ተዘግቧል።

በተለይ ባለፈው ዓመት በተደጋጋሚ በተፈጸሙ እና ነዋሪዎች እንዲሁም መንግሥት በቡድኑ የተፈጸሙ ናቸው ባሏቸው ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ከቀያቸው መፈናቀላቸው ተነግሯል።