በማሊ አንድ አውቶብስ ከድልድይ ላይ ተገልብጦ በርካታ መንገደኞች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ማሊ አንድ አውቶብስ ከድልድይ ላይ በመገልበጡ 31 መንገደኞች ሞቱ።
ክስተቱ ያጋጠመውም ትናንት ማክሰኞ የካቲት 19/ 2016 ዓ.ም በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 11 ሰዓት ነው።
አውቶብሱ ከማሊዋ ኬኒባ ከተማ ወደ ጎረቤት አገር ቡርኪናፋሶ እየተጓዘ የነበረ ሲሆን የባጎ ወንዝ በሚያቋርጠው ድልድይም ላይ ነው አደጋው የደረሰበት።
ከሟቾች በተጨማሪ 10 ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን የአንዳንዱም ጉዳት የከፋ ነው ተብሏል።
የአካባቢው ባለስልጣናት የአደጋው ምክንያት ምናልባትም “አሽከርካሪው አውቶብሱን መቆጣጠር ባለመቻሉ ነው” ብለዋል።
“ከኬኒባ ወደ ቡርኪናፋሶ እየተጓዘ የነበረው አውቶብስ ከድልድይ ላይ ተገልብጧል። የአደጋው ምክንያት ደግሞ አሽከርካሪው አውቶብሱን መቆጣጠር ባለመቻሉ ሳይሆን አይቀርም” ሲልም የትራንስፖርት ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ አትቷል።
በአደጋው ህይወታቸውን ያጡት ማሊያውን እንዲሁም ከሌሎች የምዕራብ አፍሪካ አገራት የመጡ ዜጎችም እንደሚገኙበትም አክሏል።
በማሊ የመንገድ ላይ አደጋዎች በብዛት የሚከሰቱ ሲሆን ለዚህም ዋነኛው ምክንያቶች የበርካታ መንገዶች በትክክል አለመጠገን እንዲሁም የህዝብ ትራንስፖርት መስጫዎች ከተፈቀደላቸው መጠን በላይ መጫናቸው እንደሆነም ይጠቀሳል።
በተጨማሪም በህዝብ ትራንስፖርት መስጫ አገልግሎት ላይ ያለው የቁጥጥር ስርዓት ደካማ በመሆኑ ነው።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ወደ መዲናዋ ባማኮ ይጓዝ የነበረ አውቶብስ ከከባድ መኪና ጋር ተጋጭቶ 15 ሰዎች ሲሞቱ 46 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።












