‘ከእናቴ አስከሬን ጋር በረሃ ላይ ቀረሁ’ - ወደ ግብፅ የሚሰደዱ ሱዳናውያን ሰቆቃ

በክፍት መኪና በሱዳን በረሃ የሚጓዙ ሰዎች

ከሱዳን ወደ ግብፅ እየሄዱ ነው። ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎቹ “እኔን እና ሟች እናቴን በረሃ መሐል ጥለውን ሄዱ” ትላለች ኦም ሳልማ*።

ከእናቷ ጋር በክፍት መኪና ተጭነው ነበር የሚጓዙት። የ25 ዓመቷ ወጣት እናት ሕይወታቸው ያለፈው የተሳፈሩበት መኪና ተጋጭቶ ከመኪናው በመውደቃቸው ነው።

“አሽከርካሪው ፍጥነት እንዲቀንስ ልንነግረው ሞከርን” ብትልም ዘግይተው ነበር። የ65 ዓመቷ የኦም ሳልማ እናት በአደጋው ጭንቅላታቸው ጉዳት ደርሶበት ሕይወታቸው አለፈ።

ኦም ሳልማ እንባዋ ከቁጥጥር ውጪ ሆነ። ወንድም እና እህቶቿን ጨምሮ ከያዙት ጥቂት እቃዎች ጋር ከመኪና ወረዱ። ሕገውጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎቹ አስከሬኑን ለማጓጓዝ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ጠቅሰው ጥለዋቸው ሄዱ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሱዳን ግጭት “ዓለም ላይ ትልቁን መፈናቀል አስከትሏል” ሲል ገልጾታል። ኦም ሳልማ እና ቤተሰቦቿ ለመሸሽ እየሞከሩ ነበር።

የመንግሥታቱ ድርጅት እንዳስታወቀው በሱዳን ጦር ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (አርኤስኤፍ) መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት ከስምንት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል። ባለፉት 10 ወራት ውስጥ 450 ሺህ ሰዎች ሱዳንን ለቀው ወደ ግብፅ እንደተሻገሩ ይገመታል።

ባለፈው ዓመት በዋና ከተማዋ ካርቱም በአገሪቱ ጦር መሪዎች መካከል በተፈጠረ የሥልጣን ሽኩቻ ከፍተኛ ጦርነት ተቀስቅሷል። በፍጥነት በመላ አገሪቱ ተስፋፍቶ በርካታዎች ከቀያቸው ትተው እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል።

ውጊያው እሰፋ ሄዶ ወደ ኦም ሳልማ የትውልድ ከተማ ኦምዱርማን ተቃረበ። የተኩስ ድምጽ መስማት ስትጀምር “መውጣት አለብን። ሕይወታችን አደጋ ላይ ነው” አለች። ብዙዎችም በሕጋዊ መንገድ ወደ ግብፅ ለመጓዝ የሚያስችል ቪዛ ማግኘት እንደማይቻል ነግረዋቸዋል። ስለዚህ ቤተሰቦቿን ከሱዳን ለማስወጣት በነፍስ ወከፍ 300 ዶላር የሚያስከፍል ሰው አገኘች።

ሱዳን እና ግብፅ በሚጋሩት 1200 ኪሎ ሜትር በሚረዝመው ድንበር ላይ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተስፋፍቷል።

ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች (አብዛኛው ወንዶች ናቸው) በሰሜን ሱዳን እና በደቡብ ግብፅ በወርቅ ማዕድን ሥራ ላይ የተሠማሩ ናቸው። አስቸጋሪውን በረሃማ አካባቢ እንደ እጃቸው መዳፍ ያውቁታል። ሰዎችን ለማጓጓዝ የጭነት መኪና እንዴት እንደሚያገኙም ያውቁታል።

ኦም ሳልማ እና ቤተሰቦቿ ወደ ኋላ ተመለሱ። በሰሜን ሱዳን ወደምትገኘው ጋብጋባ ከተማ። ይህ ድንበር አቋርጠው ለሚሰደዱ ሰዎች የታወቀ መነሻ ነው። ለዚህም ነው የአካባቢው ነዋሪዎች ከተማዋን የጋብጋባ አየር ማረፊያ የሚል ቅጽል ስም የሰጧት።

ኦም ሳልማ በረሃውን አቋርጠው በድንበር በኩል ወደ ደቡብ ግብፅ የአስዋን ከተማ እንደሚጓጓዙቸው ነግሯቸው። መንገድ ጀምረው ለስምንት ሰዓታት ተጓዙ። አደጋው ከመከሰቱ በፊትም ምሽት ላይ ለመተኛት ቆመው ነበር። በረሃው ውስጥ ሆነው እጃቸው ላይ የቀረው አነስተኛ ምግብ እና ውሃ እንዲሁም የእናቷ አስከሬን ነው።

ካርታ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እነ ኦም ሳልማ በረሃ ውስጥ ለሰዓታት ከቆዩ በኋላ መኪና አገኙ። መኪናው ከግብፅ ወደ ሱዳን የምግብ እና የኤሌትሪክ እቃዎችን ያጓጉዛል። ከእናታቸው አስክሬን ጋር ቀደም ብለው ወደነበሩበት አቡ ሃማድ ከተማ እንዲወስዳቸው ሾፌሩን አሳምናዋለች።

ቤተሰቡ በሠላም አቡ ሃማድ ደረሰ። የኦም ሳልማን እናትም እዚያው ተቀበሩ።

መጀመሪያ ላይ ሰዎች ስለጉዳዩ ለማውራት ፍቃደኛ አልነበሩም። ማውራት ሲጀምሩ ግን የኦም ሳልማ ታሪክ ከሌሎች ብዙም ያልተለየ ነው። ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ክፍት መኪኖችን ተጠቅመው ከባለሥልጣናት ለማምለጥ በፍጥነት ድንበሩን ለማቋተጥ ያሽከረክራሉ።

አሁን መኖሪያውን በካይሮ ያደረገው ኢብራሂም* የሚባል ግለሰብ ከሱዳን ሲወጣ መኪናው በፍጥነት ሲጓዝ ከድንጋይ ጋር በመጋጨቱ አብሮት የነበረው ሰው አንገቱ ሰብሮ ሕይወቱ ማለፉን ተናግሯል። ግለሰቡ ብቻውን እየተጓዘ ነበር። ሕገወጥ አዘዋዋሪዎቹ አስከሬኑን በረሃ ውስጥ እንዲቀብሩት ጠየቁ።

“ሁሉም ሰው በጣም ደነገጠ። ስንሄድ በመስኮቱ በኩል መቃብሮችን ተመለከትኩኝ። በጭነት መኪናው ውስጥ የነበሩት ሴቶች እና ህጻናት እያለቀሱ ነበር”ብሏል ኢብራሂም።

ዘረፋም የተለመደ ነው። የ60 ዓመቷ ሃሊማ* ግብፅ ከመድረሷ በፊት ከቤተሰቦቿ ጋር በሱዳን በረሃ ስትጓዝ በጣም የሚያስደነግጥ ነገር እንዳጋጠማት ተናግራለች።

“የእኛ መኪና ተበላሽቶ ሲቆም ጭንብል በለበሱ አራት ታጣቂዎች ጥቃት ደረሰብን። ወደ ላይ በመተኮስ ልጄን በጥፊ መትተው ንብረታችንን ዘረፉ” ብላለች። ሌላ መኪና ሲመጣ ግን ዘራፊዎቹ ደንግጠው ሸሹ። ዕድለኛ ሆነው የሌላኛው መኪና ሹፌር ሊረዳቸው ተስማምቶ ወደ ድንበሩን ወሰዳቸው።

ሃሊማ እንደምትለው የ25 ዓመት ልጇ በጣም በሁኔታው በጣም በመደናገጧ በማግስቱ ግብፅ ሲደርሱ እንደሞተች ተናገራለች።

“በጣም ደንግጣ ስለነበር መተንፈስ አልቻለችም” ያለችው ሃሊማ፣ የህክምና እርዳታ በወቅቱ ማግኘት እንዳልቻለች ተናግራለች። ቢቢሲ የተመለከተው የሞት የምስክር ወረቀት ሕይወቷ ያለፈው በመተንፈስ ችግር ነው ይላል።

የሰዱን በረሃን ለማቋረጥ መኪና የሚጠቀሙ ሰዎች

የግብፅ መንግሥ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ምን እየሠራ እንደሚገኝ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።

አስዋን የሚገኘው የሱዳን ቆንስላ ባልደረባ የሆነው አብደልቃድር አብዱላህ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ያለ ቪዛ የበረሃ ድንበሮችን ማቋረጥ ሕገወጥ መሆኑን እና ሕብረተሰቡ ከሕገወጥ ሰዎች ዝውውር ጋር ተያይዞ ያለውን አደጋ ለማስጠንቀቅ ዘመቻ መጀመሩን አስታውቀዋል።

አብዱላህ አክለውም “በአስዋን የሚገኘው የሱዳን ቆንስላ የቪዛ ሂደቱን ለማፋጠን፣ የማመልከቻዎችን ቁጥር ለመጨመር እና ብዙ ሱዳናውያን በሕጋዊ መንገድ እንዲገቡ ለማድረግ ከግብፅ መንግሥት ጋር እየሠራ ነው” ብለዋል።

ሴቶች እና ህጻናት ያለ ቪዛ ወደ ግብፅ እንዲገቡ ይፈቀድላቸው ነበር። በሱዳን ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ግን መንግሥት አዳዲስ እገዳዎችን ጥሏል። ሱዳናውያን ግጭቱን መሸሽ ስለሚፈልጉ የግብፅ ቪዛ ፍላጎት ከፍተኛ ሆኗል።

በሱዳን ሁለት ቦታዎች ለግብፅ ቪዛ ማመልከት ይችላሉ - በሰሜን ዋዲ ሃልፋ እና በምሥራቅ ደግሞ በፖርት ሱዳን። ብዙዎች ወደ ዋዲ ሃልፋ ያቀናሉ። ቦታው በሱዳን እና በግብፅ መካከል የሚገኝ ዋና የድንበር ማቋረጫ ከሆነው አርጌን አቅራቢያ ይገኛል። ግን በዋዲ ሃልፋ ግን ምንም ዓይነት መሠረተ ልማት የለም ማለት ይቻላል።

ቪዛ ለማግኘት ለሰዓታት ወረፋ መያዝ ይጠበቅባቸዋል። ማመልከቻ ካስገቡ በኋላ ቪዛ ማግኘታቸውን ለማወቅ ወራትን ሊወስድ ይችላል።

የተፈናቀሉ እና ጥቂት ገንዘብ ያላቸው በርካታ ሱዳናውያን የማመልከቻቸውን ውጤት ለመስማት በዋዲ ሃልፋ ለመጠባበቅ ይገደዳሉ። በትምህርት ቤቶች፣ በጎዳናዎች ወይም ባገኙት ቦታ ሁሉ ይተኛሉ።

ከሱዳን ለመውጣት በድጋሚ የወሰነችው ኦም ሳልማ፣ ሁለተኛ ሙከራዋ ሕጋዊውን መንገድ የተከተለ እንዲሆን ትፈልጋለች። በግብፅ ቆንስላ ቪዛ ለመጠየቅ ወደ ፖርት ሱዳን ተጉዛለች።

ለሁለት ወራት ያህል ከጠበቀች በኋላ ተስፋ ቆርጣ እንደገና ሕገወጥ መንገዱን መርጣለች። ብዙ ሰዎች ቪዛ ተከልክለዋል። የመቆየት አቅም ስለሌላቸውም በአብዛኛው የተረፋቸውን ትንሽ ገንዘብ ለሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ከፍለው ከአገር ለመውጣት ይወስናሉ።

ኦም ሳልማ ከመጀመሪያው ሙከራዋ ከደረሰባት አስደንጋጭ አደጋ በመማሯ ሌላ ሕገወጥ አዘዋዋሪ አግኝታለች። “አሁን ለጉዞው ተዘጋጅተናል” ስትል እንደ ምግብ እና ውሃ ያሉ ነገሮችን ማዘጋጀቷን ገልጻለች።

በተሳካ ሁኔታ ወደ ደቡብ ግብፅ ድንበር ከመግባታችን በፊት “በበረሃ ውስጥ ለስድስት ቀናት ያህል አሳልፈናል” ትላለች።

በግብፅ ሚገኙ ስደተኞች

ግብፅ ከገቡ በኋላም የሱዳናውያን ስደተኞች ችግር አያበቃም። የስደተኛ ወረቀት ከሌላቸው ወይም ለማመልከት ቀጠሮ እንዳላቸው ማረጋገጥ ካልቻሉ ሊባረሩ ይችላሉ።

ቀጠሮ ለማስያዝ ደግሞ ወደ ካይሮ ወይም አሌክሳንድሪያ መሄድ ይጠበቅባቸዋል።

በካይሮ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር (ዩኤንኤችሲአር) ማዕከል በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ስደተኞች (በአብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት የሆኑ) ረጅም ወረፋ ይዘው ለመመዝገብ እና ቢጫ ካርድ ለማግኘት ይጠባበቃሉ።

ሃሊማ “ብርድ ውስጥ ለሰዓታት ቆማ ያገኘቸው ከአራት ወራት በኋላ እንደትመለስ የሚያስችል ቀጠሮ ብቻ ነው።”

“የተባበሩት መንግሥታት የስደተኛ ድርጅት ተመዝጋቢ ከተሆነ በኋላ የሚገኘው ቢጫ ካርድ በሕጋዊ መንገድ ሥራ እንዲሠሩ እና ከድርጅቱ ወርሃዊ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያገኙ ያስችላል” ስትል ታስረዳለች።

ኢብተሳም* በተባበሩት መንግሥታት የተመዘገበች ስደተኛ ስትሆን፤ ነገሩ እንደሚባለው ቀላል እንዳልሆነ ትናገራለች።

ኢብተሳም ባለፈው ክረምት ነበር ወላጆቿን እና ቤተሰቦቿን ጨምሮ 17 ሆነው ከሱዳን ወደ ግብፅ በድብቅ ያቀኑት።

ቢጫ ካርድ ቢኖራትም በሰኔ ወር ግብፅ ከደረሰች ጀምሮ ምንም ዓይነት ገንዘብ እንዳላገኘች ትናገራለች። “ቤተሰቤን እንዴት መርዳት እንደምችል አላውቅም። ባለቤቴ ሞቷል። በየወሩ የምከፍለው የቤት ኪራይ እና የትምህርት ቤት ክፍያ አለብኝ። ማንም ደግሞ እየረዳን አይደለም” ብላለች።

የዩኤንኤችሲአር ቃል አቀባይ ክሪስቲን ቢሻይ በጋብጋባ የሚገኙ ሱዳናውያን ስደተኞች ያለባቸውን ብስጭት እና ስቃይ አምነው፤ ድርጅቱ “የገንዘብ እጥረት አጋጥሞታል” ሲሉ ገልጸዋል።

“አቅማችንን በ900 በመቶ አሳድገናል። ስለዚህ ቅድሚያ ሰጥተን 'መጀመሪያ እርዳታ የሚፈልገው ማን ነው?' ብለን ማሰብ አለብን” ብለዋል።

እንደ ኦም ሳልማ ያሉ በግብፅ የሚገኙ ሱዳናውያን ስደተኞች በትንሽ እርዳታ ወይም ገንዘብ የሚኖሩበት ቦታ ማግኘት አለባቸው።

ስለወደፊቱ እንደምትጨነቅ ትናገራለች። አንድ ቀን ወደ አገሯ መመለስ ትፈልጋለች። በሱዳን ባለው ግጭት ምክንያት ግን ይህ ላይሳካ ይችላል ስትል ትሰጋለች።

*ለመረጃ ሰጪዎቹ ደኅንነት ሲባል ስሞቹ ተቀይረዋል