በሱዳኑ ግጭት በማደጎ ቤት ውስጥ መውጫ አጥተው የነበሩ 300 ሕጻናትን መታደግ ተቻለ

ከማዕከሉ ከወጡ ሕጻናት መካከል

የፎቶው ባለመብት, ICRC

በሱዳኑ ግጭት መውጫ አጥተው የነበሩ ወደ 300 የሚጠጉ ሕጻናትን አደገኛ በሆነ ሁኔታ መታደግ መቻሉ ተገለጸ።

የሰብዓዊ ድርጅት ሠራተኞች አስቸጋሪ እና አደገኛ በሆነ ሁኔታ ሕጻናቱን መታደግ ግድ የሆነባቸው በአንድ መጠለያ ጣቢያ 67 ልጆች መሞታቸውን ተከትሎ ነው።

ማይጎማ ተብሎ በሚጠራው ሕጻናት ማሳደጊያ ማዕከል ዙሪያ እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት ባለሙያዎች ሕጻናቱ ወዳሉበት ስፍራ መቅረብ ሳይችሉ ቀርተው ነበር።

በዚህም ምክንያት በማዕከሉ ውስጥ የነበሩት ወላጅ አልባ ሕጻናት በረሃብ፣ በውሃ ጥም እና በበሽታ ሕይወታቸው አልፏል።

ሕጻናቱን አስጠልሎ የሚገኘው የማደጎ ማዕከል የአገሪቱ ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በሚፋለሙበት ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ለደኅንነት አስጊ በሆነ ሁኔታ 297 ልጆችን የተሻለ ሰላም አና መረጋገት ወዳለበት ቦታ መውሰድ ተችሏል። ከአደገኛ የጦርነት ቀጠና ማውጣት ከተቻሉት ሕጻናት መካከል 200 ያህሉ ከሁለት ዓመት በታች ናቸው።

በመንግሥት የሚተዳደረው ማይጎማ ወላጅ አልባ ሕጻናት ተቋም ጦርነት እስከተቀሰቀሰበት ወቅት ድረስ እሰከ 400 ልጆችን አስጠልሎ ይዞ ነበር።

የመጠለያ ጣቢያው መገኛ ስፍራ የግጭት ቀጠና ሆኖ በመቀጠሉ ሐኪሞች እና ድጋፍ ሰጪዎች ወደ ማዕከሉ መቅረብ ሳይችሉ ቀርተዋል።

በአካባቢው የኤሌክትሪክ ኃይል እና ውሃ አቅርቦት መቋረጡን ተከትሎ የአየር ሙቀቱን መቋቋም ወደማይቻልበት 43 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ደርሷል።

በዚህ እና በሌሎች ምክንያት ጨቅላ ሕጻናቱ መሞት ጀምረው ነበር።

“በፍጥነት በሞት እየተነጠቅን ነው። በቅርብ ቀናት ሦስት ልጆችን አጥተናል” ሲሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሱዳናዊ የመብት ተቆርቋሪ ሳዴኢ አል-ራሺድ ሃሚድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ግጭቱ ከሁለት ወር በፊት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ በማይጎማ 67 በማደጎ ማዕከሉ ውስጥ ያሉ ልጆች ሕይወት አልፏል ይላል።

ባለፉት ሳምንታት የአገር ውስጥ እና የዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ሕጻናቱን ከግጭት ቀጠና ለማውጣት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ሕጻናቱን ከስፍራው ለመታደግ ከጦር አመራሮች የደኅንነት ማረጋገጫ ማግኘት አዳጋች ሆኖ ከመቆየቱም በላይ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕጻናትን በተሸርካሪ ከግጭት ቀጠናው ለማውጣት የሎጂስቲክ አቅርቦትም ከፍተኛ ፈተና ሆኖ ቆይቷል።

ሱዳናዊቷ የመብት ተቆርቋሪ ሳዴኢ አማራጭ ባለመኖሩ ሕጻናቱን አደገኛ በሆነ ሁኔታ ከግጭት ቀጠና ከማውጣት ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበረም ብላለች።

በርካታ የአካባቢው መብት ተሟጋቾችን በማስተባበር እድሜያቸው ከፍ ያሉ ልጆችን ከስፍራው በማውጣት የሕይወት አድን ሥራው መጀሩን ገልጻለች።

“ሞት አይቀሬ ከሆነበት የተሻለ ተስፋ ወዳለበት ቦታ አዘዋወረናቸው” በማለት የሚናገሩት ደግሞ የማዕከሉ ሠራተኛ የሆኑት ሄባ አብዱላህ ናቸው።

ሕጻናት የጫኑት ሚኒ ባስ መኪኖችም ሕጻናት መጫናቸውን የሚያመላክት ጽሑፍ በማንገብ በግጭት ቀጠና ውስጥ በርካታ ኬላዎችን አልፈው የተሻለ ሰላም እና መረጋገት ወዳለበት ቦታ ደርሰዋል።

ከማዕከሉ ከወጡት ሕጻናት መካከል በአስቸኳይ ወደ ሆስፒታል የተወሰዱም አሉ። በምግብ እጥረት እጅግ ተጎድቶ የነበረ አንድ ታዳጊ ሕይወቱ ማለፉም ተዘግቧል።

የዩኒሴፍ በሱዳን ምክትል ተወካይ ሜሪ ሉዊስ ኤግልተን አሁን ቀጣዩ ሥራ የሚሆነው ልጆቹን በማደጎ የሚወስድ ቤተሰብ መፈለግ ነው ብለዋል።

“ሕጻናቱን ለመውሰድ ሥልጣና ወስደው ዝግጁ ሆነው የሚጠባበቁ ቤተሰብ ዝርዝር አለ” ብለዋል።

በሱዳኑ ግጭት በቀጥታ የተጎዱ ልጆች ቁጥር ወደ 13 ሚሊዮን እንደሚጠጋ ተገልጿል።