የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በምስጢራዊ ሰነድ አያያዝ ክስ ቀረበባቸው

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, THE WASHINGTON POST

የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ዋይት ሐውስን ከለቀቁ በኋላ ምስጢራዊ ሰነዶችን የያዙበት መንገድ ተገቢ አይደለም ተብለው ክስ ቀረበባቸው።

የ76 ዓመቱ ትራምፕ ያለአግባብ ምስጢራዊ ስነዶችን ይዘዋል የሚለውን ጨምሮ ሰባት ክሶች ቀርቦባቸዋል።

ክሶቹ እስካሁን ለሕዝብ ይፋ አልተደረጉም።

ትራምፕ ክስ ሲቀርብባቸው ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን፣ የቀድሞ ፕሬዝደንት በፌዴራል ደረጃ ክስ ሲቀርብበት ትራምፕ የመጀመሪያው ናቸው።

ዶናልትድ በ2024 ድጋሚ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ለመሆን የምረጡኝ ቅስቀሳ ላይ ናቸው።

የሕግ አዋቂዎች እንደሚሉት ክሱ ትራምፕ ለፕሬዝደንትነት በሚያደርጉት ጥረት ላይ እክል አይሆንም።

ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ማኅበራዊ ሚድያቸው ትራምፕ ‘ከደሙ ንፁህ’ መሆናቸውን ገልጸው በፍሎሪዳ ግዛት ማያሚ በሚገኝ አንድ የፌዴራል ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መታዘዛቸውን አመልክተዋል።

በሚመጣው ማክሰኞ ትራምፕ ወደ ፍርድ ቤቱ በመሄድ በቁጥጥር ሥር ውለው የቀረበባቸውን ክስ ያደምጣሉ።

“ለአንድ እንኳን የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት እንዲህ ዓይነት ነገር ይገጥመዋል ብዬ አስቤ አላውቅም” ብለዋል።

“ይህ ለአሜሪካ ድቅድቅ ጨለማ የሰፈነበት ቀን ነው። በፍጥነት እያሽቆለቆልን ያለ አገር ሆነናል። ነገር ግን በጋራ አሜሪካን እንደገና ታላቅ እናደርጋታለን።”

የትራምፕ ጠበቃ ኪም ትረስቲ፤ ሲኤንኤን ለተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደተናገሩት የቀድሞው ፕሬዝደንት በምን ጉዳይ እንደተከሰሱ ይፋ ተደርጎላቸዋል።

ጠበቃው እንደሚሉት መዝገቡ፤ ሴራ፣ የሐሰት መግለጫ፣ ፍትህን ማጓተት እና በአገር ክህደት ውስጥ የሚካተተው ጥብቅ መረጃዎችን መያዝ የሚሉ ክሶችን ይዟል።

የአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት የተቆጠበ ሲሆን፣ ክሱ ለሕዝብ ይፋ አልሆነም።

የአሜሪካ የደኅንነት ሰዎች ትራምፕ እና ረዳቶቻቸውን አግኝተው ወደ ማያሚ ፍርድ ቤት እንዴት እንደሚወስዷቸው ይመክራሉ።

ባለፈው ዓመት ፍሎሪዳ የሚገኘው ማራ-ላጎ የተሰኘው የትራምፕ መኖሪያ ተፈትሾ 11 ሺህ መዛግብት የተገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል 100 ገደማዎቹ ጥብቅ መረጃዎች ናቸው ተብሏል።

ባለፈው ሳምንት መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት፤ ትራምፕ ዋይት ሐውስን ለቀው ሲወጡ ጥብቅ መረጃ ይዘው እንደወጡ የሚናገሩበት የድምፅ ቅጂ በዐቃቤ ሕግ እጅ ገብቷል።

በአሜሪካ ሕግ መሠረት ፕሬዝደንትን ጨምሮ ማንኛውም የፌዴራል ባለሥልጣን ፈቃድ ሳይሰጠው ምስጢራዊ ሰነድን ማስወገድም ሆነ መደበቅ አይችልም።

የሕግ ባለሙያዎች እንደሚሉት ዶናልድ ትራምፕ ቢከሰሱም ለምርጫ ከሚያደርጉት ዘመቻቸው የሚያግዳቸው ነገር የለም።

በቤት ሽያጭ እና በቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅነት ሰፊ እውቅናን ለማግኘት የቻሉት ትራምፕ፤ ፕሬዝደንት ለመሆን ከሪፐብሊካን ዕጩዎች መካከል የተሻለ ዕድል ያላቸው ሰው ናቸው።

ትራምፕ አሁን ከቀረበባቸው ክስ በተጨማሪ ያለፈውን ምርጫ ውጤት ለመቀልበስ ጥረት አድርገዋል ተብለው መከሰሳቸው አይዘነጋም።

የቀድሞው ፕሬዝደንት በኒው ዮርክ ቀርበው ይህን ክሳቸውን ይከታተላሉ።