ለሩሲያ ሲሰልል ተይዞ ለእሥር የተዳረገው አሜሪካዊ ሰላይ ማረሚያ ቤት ሞቶ ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለሩሲያ ሲሰልል የተያዘው የአሜሪካው ኤፍቢአይ መኮንን እሥር ቤት ውስጥ ሞቶ ተገኘ።
በአሜሪካ የስለላ ታሪካ ከባድ ጥፋት የፈፀመው ሰው ተብሎ የሚጠራው ሮበርት ሃንሰን ጥብቅ በሚባለው የኮሎራዶው ፍሎረንስ እሥር ቤት ነበር።
የ79 ዓመቱነ ሃንሰን ከሩሲያ ሰላዮች 1.4 ሚሊዮን ዶላር በጥሬው፣ አልማዞችና ሌሎችን ጥቅማጥቅሞች ተቀብሏል።
ግለሰቡን ለመከታተል አሜሪካ 300 ያክል ሰላዮችን አሰማርታ ነበር።
ሃንሰን በፈረንጆቹ 2002 ነው በሕገ-ወጥ መንገድ የደኅንነት መረጃ መሰብሰብ ወንጀል የዕድሜ ልክ እሥራት የተፈረደበት።
ግለሰቡ ለእሥር ከመዳረጉ በፊት ቨርጂኒያ ውስጥ ከሚስትና ስድስቱ ልጆቹ ጋር አራት አልጋ ክፍሎች ባሉት ቤት ይኖር ነበር።
ለበርካታ ምስጢራዊ መረጃዎች ቅርብ የነበረው ሃንሰን በ1985 ነው ለሩሲያ እኒህን መረጃዎች መቸብቸብ የጀመረው።
በ1976 ኤፍቢአይን የተቀላቀው ግለሰቡ መረጃ “ራሞን ጋርሲያ” የተሰኘ ስም በመጠቀም ይታወቃል።
ኤፍቢአይ በድረ-ገፁ እንደሚለው ግለሰቡ “በርካታ የሰው ኃይል፣ የስለላ ዘዴዎችን፣ ምርመራዎች፣ የአሜሪካ መንግሥት ምስጢራዊ ፋይሎችን እና ክብደት ያላቸው ቴክኒካዊ ሥራዎችን አደጋ ላይ ጥሏል።”
ግለሰቡ ምንም እንኳ አንዳንድ ጊዜ የሚያደርጋቸው ነገሮች አጠራጣሪ ቢሆኑም ዓይን ውስጥ ሳይገባ ለዓመታት ቆይቷል።
አልድሪኽ ሃዜን የተባለው ሰላይ በኤፍቢአይ ቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ነው የአሜሪካው የምርመራ ቢሮ ውስጡ መረጃ አሾላኪ እንዳለ የተረዳው።
ሃንሰን ጡረታ ሊወጣ እያሟሟቀ ሳለ ኤፍቢአይ እጅ ከፍንጅ ሊይዘው ፈልጎ ምርመራውን አጣደፈው።
የይምሰል የቤት ሥራ የተሰጠው ሃንሰን፤ በድብቅ ካሜራዎችና ድምፅ ማጉያዎች በታጠረው አዲሱ ቢሮው እንቅስቃሴውን ቀጠለ።
ከአንድ ወር በኋላ የኤፍቢአይ ሰዎች ግለሰቡ አንድ ፓርክ ውስጥ መረጃ ሊያቀብል እንደሆነ ደረሱበት።
የካቲት 18/2001 ሃንሰን ምስጢራዊ መረጃ በፕላስቲክ ከረጢት ይዞ ቨርጂኒያ ወደሚገኘው ፎክስቶን ፓርክ አመራ።
ነገር ግን እግር እግሩን ሲከቱሉን የነበሩት የኤፍቢአይ መኮንኖች መኪና ውስጥ ሲገባ ጠብቀው በቁጥጥር ሥር አዋሉት።
በቁጥጥር ሥር በዋለበት ወቅት የአፍቢአይ ሰዎችን “ምነው ዘገያችሁ?” ሲል እንደጠየቃቸው ይነገራል።
ሃንሰን የፈፀመውን ተግባር አፍረጥርጦ መናገር ባይሻም የሞት ቅጣት ለማምለጥ ሲል አድርጎታል።
ሃንሰን ወግ-አጥባቂ የሚባል አባት ነበር። ቤተሰቡ ዘወትር እሑድ በአንዲት አርጀት ባለች መኪና ወደ ቤተ-እምነት ያቀናል። ልጆቹ ያለአባታቸው ፈቃድ ቴሌቪዥን መመልከት አይችሉም።
ነገር ግን በድብቅ ወሲባዊ ቅሌት ያናወዘው ግለሰብም ነበር። ሃንሰን ሚስቱ እርቃን ሳለች በድብቅ በቪድዮ ቀርፆ ለአንድ ጓደኛው አሳይቷል።
በታሠረበት ወቅት ወደ እርቃን ዳንስ ቤቶች መሄድ እንደሚያዘወትርና እዚያ የሚሠሩ ሰዎችን የካቶሊክ እምነት እንዲቀበሉ ማሳመን እንደሚወድ ተነግሮ ነበር።
አልፎም ወሲባዊ ይዘት ያላቸውን የሱና የሚስቱ ታሪኮች እንዲሁም የሚስቱን እርቃን ፎቶዎች በይነ-መረብ ላይ ለጥፎ ያውቃል።
ሃንሰን ለቀረበበት 15 ክስ ጥፋተኛ እንደሆነ አምኖ ግንቦት 2002 የዕድሜ ልክ ፅኑ እሥራት ተፈርዶበታል።












