ትራምፕ የተጋረጠባቸውን የሕግ ፈተና የሚያስረዱ 7 ቁልፍ ጥያቄዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በኒው ዮርክ የዶናልድ ትራምፕን ጉዳይ ሲመለከት የነበረው የዳኞች ስብስብ በቀድሞ ፕሬዝዳንት ላይ ክስ እንዲመሰረትባቸው ከወሰነ በኋላ ትራምፕ የወንጀል ክስ የሚመሰረትባቸው የመጀመሪያው አሜሪካንን ፕሬዝዳንት ያገለገሉ ሰው ሆነዋል።
ትራምፕ የሚቀርብባቸው የክስ ዝርዝር እስካሁን በይፋ አልሆነም። ስለዚህ ዐቃቤ ሕግ በቀድሞው ፕሬዝዳንት ላይ ምን ዓይነት ክስ ሊመሠርት እንደሚችል በትክክል አናውቅም። ትራምፕ ነገ ማክሰኞ ፍርድ ቤት ቀርበው ክሳቸው ይነበብላቸዋል።
ይሁን እንጂ ክሱ ትራምፕ የ2016ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከመካሄዱ ጥቂት ሳምንታት በፊት ከወሲብ የፊልም ተዋናይቷ ጋር የነበራቸው ግንኙነት አደባባይ እንዳይወጣ ገንዘብ ከፍለዋል በሚለው ክስ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
በትራምፕ ዙሪያ ምን እየተካሄደ እንዳለ ለመረዳት የሚረዱን ሰባት ቁልፍ ጥያቄዎችን አንስተን ምላሽ እንሰጣለን።
ክሱ ምንድን ነው?
ሐሙስ ዕለት የትራምፕን ጉዳይ የተመለከቱት የዳኞች ስብስብ የቀድሞ ፕሬዝዳንት በወንጀል እንዲከሰሱ ድምጽ ሰጥተዋል።
ይህ የዳኞች ስብስብ (ግራንድ ጁሪ) የሚቀረቡ ማስረጃዎችን ተመልክቶ፣ የዐይን ምስክሮችን ቃል አድምጦ አንድን ሰው በወንጀል ለመክሰስ በቂ ማስረጃ መኖር አለመኖሩን የሚወስን የዜጎች ስብስብ ነው።
ትራምፕ ላይ የቀረበው ክስ ደግሞ አንድ ዓመት እና ከአንድ ዓመት በላይ በእስር ሊያስቀጣ የሚችል ወንጀል ቀርቦባቸዋል።
ትራምፕ ይታሰራሉ?
መከሰሳቸው በቁጥጥር ስር መዋልን አያስከትልም።
ዐቃቤ ሕጎች ከትራምፕን ጠበቆች ጋር ድርድር ካደረጉ በኋላ የቀድሞው የፕሬዝዳንት ቡድን እና ሌሎችም ባለሙያዎች ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት ራሳቸውን አሳልፈው እንደሚሰጡ ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል።
በትክክል ይህ እንዴት እንደሚሆን እስካሁን ግልፅ አይደለም። ትራምፕ እጃቸውን ከሰጡ ግን በተለመደው የወንጀል እስራት ሂደት ውስጥ ማለፍ ይጠበቅባቸዋል።
ትራምፕ ወደ ችሎት በሚሄዱበት ወቅት እጃቸው በካቴና ታስሮ ሊሆን ይችላል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ማክሰኞ እጅ ሲሰጡ በኒው ዮርክ ከተማ ፍርድ ቤት ደጃፍ ተሰበሰበው ካሜራ እና ማይክሮፎን ደቅነው ከሚጠብቋቸው እልፍ ጋዜጠኞች ፊት ማለፍ ሊያስፈልጋቸው ይችላል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ትራምፕ በካቴና ታስረው ይታዩ ይሆን?
አንዳንድ ተጠርጣሪዎች በካቴና ታስረው እና በፖሊስ ሲታጀቡ ሌሎች ደግሞ በራሳቸው ወደ ፍርድ ቤት እንዲገቡ ይፈቀድላቸዋል።
በእግር በሚጓዙበት ጊዜ የሚነሱ ምስሎች በተወሰኑ ጉዳዮች ዙሪያ አይረሴ ትዝታን የሚፈጥሩ ናቸው።
የቀድሞው የሆሊውድ ፊልም አዘጋጅ ሃርቪ ዌይንስታይን በአስገድዶ መድፈር እና ከሁለት ሴቶች ጋር በተያያዘ የወሲብ ወንጀል ፈጽሟል ተብሎ በተከሰሰበት ወቅት፤ እጁ በካቴና ታስሮ ወደ ኒው ዮርክ ፖሊስ ህንፃ ገብቷል።
በካሜራዎች የተነሳው ያ ቅጽበት በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃtኦችን በመቃወም በተቀታጠለው የ'ሚ ቱ' እንቅስቃሴ በጣም ታዋቂ ከሆኑ ምስሎች እንደ አንዱ ተደርጎ ይቆጠራል።
ሌላው ታዋቂ ክስተት የቀድሞ የአይኤምኤፍ ኃላፊ ዶሚኒክ ስትራውስ-ካን በጾታዊ ጥቃት እና የቤት ሠራተኛቸውን አስገድደው በመድፈር ሙከራ የተከሰሱበትን ያስታውሳል።
ዶሚኒክ ስትራውስ-ካን እጃቸው በካቴና ታስሮ በመገናኛ ብዙኃን ፊት መታየታቸው ፍትሃዊ አይደለም ሲሉ ቅሬታቸውን አስምተው ነበር።
ስትራውስ-ካን በ2013 ለአሜሪካው የዜና ማሰራጫ ሲኤንኤን “ጥፋተኛ እስካልተባልክ ድረስ ንፁህ ሆነ የመታየት መብት አለህ… ወንጀለኛ እንደሆንክ ማንም ሰው በማያውቅበት ወቅት እንደ ወንጀለኛ ትታያለህ” ብለዋል።
ነገ በፍርድ ቤት ምን ይፈጠራል?
ትራምፕ የቀረበባቸው ክስ ነገ በፍርድ ቤት ይነበብላቸዋል።
ትራምፕ ወይም እሳቸውን የሚወክል ጠበቃ ቃሉን ይሰጣል። ይህም ማለት ትራምፕ ወንጀሉን ፈጽመዋል ወይም አልፈጸሙም ተብሎ ይጠየቃል። ቀጥሎም ተከሳሹ ጥፋተኛ ነኝ ወይም ጥፋተኛ አይደለሁም ሲል ምላሽ ይሰጣል።
በፍርድ ቤት ውስጥ ካሜራዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ይህ የሚሆነው ግን ዳኛው ከፈቀዱ ብቻ ነው።
ከፍርድ ሂደቱ በኋላ ትራምፕ በፈቃደኝነት ወደ ፍርድ ቤት እንደሚመለሱ እና ለፍርድ እንደሚቀርቡ ቃል ገብተው ከፍርድ ቤት ይወጣሉ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ትራምፕ ለምን ተከሰሱ?
ትራምፕ ስለተከፈተባቸው ይፋዊ ክስ እስካሁን ምንም አናውቅም። ነገር ግን ትራምፕ ከ2016ቱ ምርጫ በፊት በቀድሞ ጠበቃቸው ማይክል ኮኸን በኩል ስቶርሚ ዳንኤልስ ለተባለች የወሲብ የፊልም ተዋናይ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ጋር ስለነበራት ግንኙነት እንዳትናገር ተከፍሏታል።
ክፍያው ሕገ ወጥ አልነበረም። ዐቃቤ ሕግ እንደሚለው ግን ትራምፕ ለኮኸን ክፍያውን ሲመልሱ የክፍያው ምክንያት ከሕግ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች የዋለ ነው ይላል። ይህ ማለት ትራምፕ የንግድ መዝገቦችን እያጭበረበሩ ነበር ማለት ነው ይላሉ።
ሌላ ክፍያም ካረን ማክዱጋል ለተባለች የመጽሔት ሞዴል ተፈፅሟል። እሷም ከትራምፕ ጋር ግንኙነት እንደነበራት ተናግራለች።
ሌሎች ክሶች ምን ሊሆኑ ይችላሉ?
እአአ ጥር 6 ቀን 2021 የትራምፕ ደጋፊዎቻቸውን “እንደ ዓለም ፍጻሜ እንዲዋጉ” የሚያበረታታ ንግግር ካደረጉ በኋላ ደጋፊዎቻቸው ካፒቶል ሂልን ወረሩ። በጥቃቱ ተሳትፎ አድርገዋል በሚል ትራምፕ ክስ ሊመሰረትባቸው እንደሆነ አሁንም ግልፅ አይደለም።
ሌላው ሊመሠረት የሚችለው ክስ በትራምፕ የፍሎሪዳ መኖሪያ ቤት በተገኙ ምስጢራዊ ሰነዶች ላይ እየተደረገ ባለው ምርመራ እና የምርመራው ሂደት እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ በሚል ሊሆን ይችላል።
የጆ ባይደንን የ2020 ድል ለመቀልበስ በደቡባዊ ጆርጂያ ግዛት ባለሥልጣናት ላይ ጫና በማድረጋቸውም የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ምርመራ እየተደረገባቸው ነው።
ትራምፕ በተቀረጸ የስልክ ጥሪ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊያቸው ውጤቱን ለመቀልበስ በቂ ድምጽ “እንዲያፈላልጉ” ሲጠይቁ ተሰምተዋል።
በ2024 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ መወዳደር ይችላሉ?
በወንጀል ተከሰው በ2024 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ መወዳደር ይችላሉ?
አዎ ይችላሉ። ምንም ዓይነት ክስ ወይም በእነዚህ ክሶች ቢፈረድባቸውም ትራምፕ ይህን ለማድረግ እስከፈለጉ ድረስ ለፕሬዝዳንትነት ከመወዳደር አያግዳቸውም።
በአሜሪካ ሕገ መንግሥት መሠረት የወንጀል ሪከርድ ለፕሬዝዳንትነት ከመወዳደር ከሚከለክሉ መስፈርቶች ውስጥ አይገኝም።
በከፍተኛ ወንጀሎች እና በደሎች የተከሰሱ እና የተፈረደባቸው ባለሥልጣናት ወደፊት ከሥልጣን ሊታገዱ ይችላሉ። ነገር ግን የአሜሪካ ሴኔት ትራምፕን በሁለቱም የክስ ጉዳዮች በነጻ አሰናብቷቸዋል።
የቢቢሲ የሰሜን አሜሪካ ዘጋቢ አንቶኒ ዘርቸር “በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ዕጩ ከእስር ቤትም ሆኖ የምርጫ ቅስቀሳ ከማድረግ እና ፕሬዝዳንት ሆኖ ከማገልገል የሚገድበው ምንም ነገር በአሜሪካ ሕግ ውስጥ አልሰፈረም” ብሏል።












