በደቡብ ወሎ መውጫ ያጡ የማዕድን ቆፋሪዎች ቤተሰቦች ከ19 ቀናት በኋላ ሐዘን ተቀመጡ

ማዕድን አውጪዎች ከመሬት በታች (ፎቶ ከፋይል)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ማዕድን አውጪዎች ከመሬት በታች (ፎቶ ከፋይል)

በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን ከ19 ቀናት በፊት የማዕድን ማውጫ ዋሻ የተናደባቸውን ሰዎችን ለማውጣት ሲጥሩ የነበሩት ቤተሰቦች እና የአካባቢ ነዋሪዎች፤ ማዕድን አውጪዎቹን በሕይወት የማግኘት ተስፋቸው ተመናምኗል።

የማዕድን አውጪዎቹ ቤተሰቦቹ ካለፈው ሳምንት ወዲህ ሐዘን መቀመጥ የጀመሩ ሲሆን፣ እስካሁን ለቅሶ ሳይቀመጥ የቆየው ሁለት ወንድማማቾች ዋሻ ውስጥ የተቀበሩበት ቤተሰብ በዛሬው ዕለት “እርም” እያወጣ መሆኑ ተነግሯል።

በደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ፤ ባለፈው ወር መጨረሻ ጥር 30/2016 ዓ.ም. ሌሊት የኦፓል ማዕድን ለማውጣት ወደ ዋሻ ገብተው ናዳ ያጋጠማቸውን ቢያንስ ስምንት ሰዎችን ለማዳን ባለፉት ሳምንታት ጥረት ሲደርግ ቆይቷል።

ይህንን ሙከራ ሲያደርጉ የቆዩት ቤተሰቦች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ትላንት ሰኞ የካቲት 19/2016 ዓ.ም. የመከላከያ ሠራዊት ያደረገው ሙከራ አለመሳካቱን ተከትሎ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ገብተዋል።

በትናንትናው ዕለት ሰኞ ማዕድን አውጪዎችን ለማዳን ቁፋሮ የሚያደርጉ “ሰዎች ላይ ተደርምሶ ጉዳት ያደርሳል” የሚል ስጋት የፈጠረው የተንጠለጠለ የገደል ክፍል አስር ጊዜ ያህል በታንክ እንዲመታ መደረጉን የደላንታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አያሌው በሪሁን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይሁንና በመከላከያ ሠራዊት የተደረገው ይህ ሙከራ አለመሳካቱን የሚናገሩት ዋና አስተዳዳሪው፤ “የሚቻለው ሁሉ ተሞከረ፤ ከተፈጥሮ ጋር መታገል፣ ተፈጥሮን ማሸነፍ አልተቻለም” ሲሉ የተተኮሰው ከባድ መሳሪያ ሊናድ ይችላል የተባለውን የተንጠለጠለ የዋሻውን ክፍል ለማውረድ አለመቻሉን ገልጸዋል።

ነፍስ የማዳኑ ጥረት ያለውጤት በመራዘሙ “አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የቆፋሪው ቁጥር እየቀነሰ መጣ” የሚሉት ዋና አስተዳዳሪው “እርም ለማውጣት” ሐዘን የተቀመጡ ቤተሰቦች መኖራቸውንም አንስተዋል።

የማዕድን አውጪዎቹን ለማዳን የተደረገውን ጥረት የተቀላቀለው የመከላከያ ሠራዊት፤ ሰኞ ያከናወነው የገደሉን ክፍል በመድፍ የመምታት ሙከራ የመጀመሪያው አይደለም። ባለፈው ሳምንት ሰኞ ዕለት በዚህ የገደል ክፍል ላይ ፈንጂ አጥምዶ ለመናድ ሙከራ አድርጎ የነበረ ቢሆንም ውጤት አላስገኘም።

ከዚህ ሙከራ አለመሳካት በኋላ የማዕድን አውጪዎቹ ቤተሰቦች ተስፋ በመቆረጥ ወደ ሐዘን መሄዳቸውን 28 ዓመት ዕድሜ ያለው የአጎቱ ልጅ በዋሻው ውስጥ የሚገኘው ክንድዬ ተስፋዬ ለቢቢሲ ተናግሯል።

“አንድ ቤተሰብ ካልሆነ በቀር ሌላው ፈንጂ ተሞክሮ አልሳካ ካለ ወዲህ ነው [ቤተሰብ ሐዘን መቀመጥ] የጀመሩት” የሚለው ክንድዬ አንድ ቤተሰብ ከዚህም አስቀድሞ ሐዘን እንደተቀመጠ አስታውሷል።

ማዕድን አውጪዎቹ የቤተሰብ አባላት በዋሻ ውስጥ ከቀሩባቸው ስምንት ቤተሰቦች ውስጥ እስከ ትላንት ሰኞ ድረስ ሐዘን ሳይቀመጥ የቆየው እንድ ቤተሰብ ብቻ እንደነበር ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት ቤተሰቦች እና በአካባቢው የሚገኘው የወርቅ ዋሻ የከበሩ ማዕድናት አምራች እና ግብይት ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ አጋዥ ተናግረዋል።

ፋንታዬ ጌታዬ እና ደጀኔ ጌታዬ የተባሉ ሁለት ወንድማማቾች በዋሻው ውስጥ የተቀበረበት ይህ ቤተሰብ በዛሬው ዕለት ለሐዘን መቀመጡን የወንድማማቾቹ የአጎት ልጅ አቶ ካሳው መኮንን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የ26 እና 31 ዓመት ወጣት የሆኑት ሁለቱ ወንድማማቾች የራሳቸውን ቤተሰብ እንዲሁም እናት እና አባታቸውን ይረዱ የነበሩት ማዕድን በማውጣት እና በቀን ሥራ በሚያገኙት ገንዘብ እንደነበረ አቶ ካሳው ያስታውሳሉ። ባለፈው ዓመት በዚህ ወቅት ትዳር የመሠረቱት ሁለቱ ወንድማማቾቹ፤ ባለቤቶቻቸው ነፍሰ ጡር ናቸው።

እንደ አቶ ካሳው ገለጻ እስካሁን ድረስ ተስፋ የነበራቸውን የሁለቱ ወንድማማቾች ቤተሰብ በዛሬው ዕለት ሐዘን እንዲቀመጡ ያደረገው የትላንቱ ሙከራ አለመሳካት ነው።

ዋሻው የተደረመሰበት አካባቢ ገደላማ በመሆኑ የነፍስ አድን ሥራ ለማከናወን አዳጋች መሆኖ ቆይቷል

የፎቶው ባለመብት, SOUTH WOLLO COMMU.

የምስሉ መግለጫ, ዋሻው የተደረመሰበት አካባቢ ገደላማ በመሆኑ የነፍስ አድን ሥራ ለማከናወን አዳጋች መሆኖ ቆይቷል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“እስካሁን ምናልባት በመንግሥት በታንክም በምንም ሲመታ ይወርዳል የሚል ተስፋ ነበረን። ዛሬ በመንግሥትም በሕዝብም ተሞከረ ገደሉ የማይናድ ሆነ። . . . . ላለፉት 19 ቀን ጠበቅን፤ አሁን ግን መፍትሄ የለውም። ዘመድ ሁሉም በአንድ ላይ ተሸክፎ አልቅሶ ያለው ሐዘን [ለመወጣት] ነው” ሲሉ ቤተሰብ እና ዘመድ ለሐዘን መሰብሰቡን ገልጸዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ቤተሰቦች ከአሁን በኋላ ዋሻ ውስጥ መውጫ ያጡት ማዕድን አውጪዎች በሕይወት ይገኛሉ የሚል ተስፋ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

በትላንት ሰኞ ዕለት ቤተሰቦቹ ሐዘን የተቀመጡት ክንድዬ፤ “[ከዚህ ቀደም] ከ11 ቀን በኋላ በሕይወት የተገኙ ልጆች ስለነበሩ እሱን ተስፋ በማድረግ እስከ 11፣ 12 ቀን ድረስ በሕይወት እናገኛቸዋለን በሚል ርብርብ ነበር። አሁን ላይ በሕይወት የማናገኛቸው ከሆነ ሌላ መስዋዕትነት ማስከፈል አንፈልግም [እየተባለ ነው]” ሲል ማዕድን አውጪዎቹን በሕይወት የማግኘት ተስፋ መመናመኑን አስረድቷል።

የወርቅ ዋሻ የከበሩ ማዕድናት አምራች እና ግብይት ማህበር ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬም በቤተሰቦች ዘንድ ይህ ስሜት መፈጠሩን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፈንጂ እና የታንክ ሙከራው ባለመሳካቱ “ተስፋ ቆርጠን ነው ያለነው” የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ “ጊዜው ረዘመና መታገዝ ባለመቻላችን አሁን ላይ ተስፋ እየቆረጥኩ ነው። ቢያንስ በሕይወት [ማግኘት] ቀርቶ አስከሬናቸው መውጣት አለበት” ብለዋል።

የማኅበር ሊቀመንበሩ፤ ይናዳል የሚል ስጋት የፈጠረው የገደሉ ክፍል በታንክም ተመትቶ ባለመውረዱ አሁንም ቢሆን በሰዎች የሚደረገው ቁፋሮ መቀጠል አለበት ብለው እንደሚያምኑ አስረድተዋል።

ይህንን ሀሳብ እንደሚጋሩት ለቢቢሲ የተናገሩት የደላንታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አያሌውም፤ በነገው ዕለት ረቡዕ በድጋሚ በሰዎች የሚደረግ ቁፋሮ ይቀጥላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

በደቡብ ወሎ በደላንታ ወረዳ 018 አለኋት ቀበሌ ቆቅ ውሃ በተባለው አካባቢ በሚገኘው የኦፓል ማዕድን ማውጫ ዋሻ ውስጥ ሳሉ አደጋው የደረሰባቸው ሰዎች ከ20 በላይ ሊሆኑ ይችላል ተብሎ መጀመሪያ ላይ የተነገ ቢሆንም፣ በዋሻው ውስጥ ተቀብረዋል ተብለው ማንነታቸው የተለየ ሰዎች ቁጥር 8 መሆኑን ነዋሪዎች እና የአካባቢው ባለሥልጣንት ተናግረዋል።

ዋሻው ተደርምሶባቸው መውጫ ካጡ ሦስት ሳምንት ሊሞላቸው የተቃረቡትን ሰዎች ለማትረፍ ከመጀመሪያው አንስቶ በአካባቢው አስተዳዳሪዎች እና ነዋሪዎች ጥረት ቢደረግም፣ የማዕድን ማውጫው ያለበት ስፍራ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ በርካታ ሰዎችንም ሆነ የመቆፈሪያ መሳሪያ ለማስገባት አዳጋች ባለመሆኑ ጥሩ ስኬት ሳያስገኝ ቀርቷል።