“በሕይወት ይወጣ እንደሁ ብለን ጋራ ጋራውን እያየን ሁለት ሳምንት ሆነ” በማዕድን ዋሻ ውስጥ የተቀበረ ወጣት ወንድም

ኦፓል

የፎቶው ባለመብት, MOM

በደቡብ ወሎ ዞን፣ ደላንታ ወረዳ የከበረ ማዕድን ለማውጣት በቁፋሮ ላይ የነበሩ ማዕድን አውጪዎች በዋሻው ውስጥ ከተቀበሩ ዛሬ ሐሙስ የካቲት 14/2016 ዓ.ም. ሁለት ሳምንት ሞላቸው።

አደጋው መከሰቱ ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ የአካባቢው ማኅበረሰብ እና የመንግሥት አካላት በቁፋሮ ሰዎቹን ለመታደግ ጥረት ቢያደርጉም ሙከራቸው ሳይሳካ አብዛኞቹ ወጣት የሆኑት ማዕድን ፈላጊዎች በናዳው ተቀብረው ይገኛሉ።

በደላንታ ወረዳ 018 አለኋት ቀበሌ ቆቅ ውሃ በተባለው አካባቢ ሐሙስ ጥር 30/2016 ዓ.ም. ሌሊት በቁፋሮ ላይ ሳሉ ዋሻው ተንዶ መውጫ ያጡት ሰዎች ቁጥር እስካሁን በትክክል ባይታወቅም፤ ከስምንት እስከ 20 ሊደርሱ እንደሚችሉ የአካባቢው ምንጮች አሳውቀዋል።

ቤተሰቦቻቸውም መንግሥት እና አቅሙ ያላቸው ተቋማት በናዳ ተይዘው ለሚገኙት ሰዎች እንዲደርስላቸው እየተማፀኑ ነው።

በዋሻው ውስጥ ተቀብረው ከሚገኙ ማዕድን አውጪዎች መካከል አንዱ የሆነው የፋሲል ሞላ ታላቅ ወንድም ጌጡ ሞላ፣ ወንድማቸው በሕይወት ይወጣል የሚል ተስፋ ቢኖራቸውም ቀኑ እየተራዘመ በሄደ ቁጥር ተስፋቸውም እየተመናመነ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ጌጡ እንደሚሉት የ29 ዓመቱ ፋሲል ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ውጤት ስላላገኘ ነበር ወደ ማዕድን ቁፋሮው የገባው።

ፋሲል ላለፉት 13 ዓመታትም በደላንታ አካባቢ በስፋት ይገኛል የሚባለውን እና ለጌጣጌጥ መሥሪያነት የሚውለውን ውድ ማዕድን ኦፓል በመፈለግና በማውጣት ሥራ ላይ ተሰማርቶ ቆይቷል።

በሥራው በሚያገኘው ገቢም አቅመ ደካማ ወላጆቹን እየጦረ እና ታናናሾቹን እያስተማረ ባለበት ወቅት ነበር ይህ አደጋ ያጋጠመው።

“ጠዋት ማታ እያለቀስን ነው፤ ነገር ግን ምንም መፍትሔ አላገኘንም” ብለዋል አቶ ጌጡ ያሉበትን ሁኔታ ሲገልጹ።

የማዕድን ማውጣቱ ሌሊትም ቀንም እንደሚሠራ የገለጹት አቶ ጌጡ፣ አደጋው በደረሰበት ዕለት ወንድማቸው አዳሩን ለቁፋሮ መውጣቱን፣ ነገር ግን ጠዋት ላይ ዋሻው እንደተናደባቸው መስማታቸውን ይናገራሉ።

ሆኖም ከዚህ ቀደምም መሰል አደጋዎች በአካባቢው አጋጥመው ስለነበር የሰሙትን ዜና አክብደው አላዩትም ነበር።

ጠዋት ሥፍራው ድረስ ሄደው ካዩት በኋላ ነበር ወንድማቸው ከባድ ሁኔታ ውስጥ መሆኑን የተረዱት።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በነዋሪው የጉልበት ኃይል እንዲሁም በአካባቢው በሚገኙ የመንግሥት አካላት ድጋፍ ሰዎቹን ለማውጣት ቢሞከርም አለመሳካቱን ገልጸዋል።

“እስካሁን ድረስ በሕይወት ይኖሩ ነበር። ታፍነው ነው እንጂ የሚሆነው፣ እስካሁን አደጋው እንዳልገደላቸው እናውቃለን። የክልሉ እና የፌደራል መንግሥቱ የተሻለ ጥረት ቢያደርግልን በሕይወት እናገኛቸው ነበር።” ይላሉ።

የዋሻው ርዝመት 150 ሜትር እንደሆነና በቁፋሮ የተናደው 50 ሜትር የማይሞላ በመሆኑ ሰፊ ቦታ ስለሚያገኙ እንዲሁም ዋሻው አየር የሚያገኙበት ክፍተቶች ስላሉት በአፋጣኝ ቢደረስላቸው በሕይወት የመውጣት ዕድል እንደሚኖራቸው ይናገራሉ።

የማዕድን ማውጫ ዋሻ

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የቤተሰብ አባሎቻቸው ከዋሻው መውጣት ሳይችሉ ሁለት ሳምንት የሆናቸው ሰዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን እና ቀኑ እየገፋ ሲሄድ በሕይወት የመውጣታቸው ነገር አጠያያቂ እየሆነ መምጣቱን አመልክተዋል።

አቶ ጌጡ ወንድማቸው ፋሲል ከዚህ በፊትም በሥራው ምክንያት ቀለል ያለ አደጋ አጋጥሞት እንደነበርና ከሁለት ቀናት በኋላ በሕይወት መውጣቱን አስታውሰዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት በወቅቱ ወንድማቸው እና ሌሎች አብረውት የነበሩ ማዕድን አውጪዎች ይዘውት የገቡት ባትሪ ኃይል በመጨረሱ ጨለማ ውስጥ ለሁለት ቀናት ከመቆየታቸው ውጪ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስባቸው በቁፋሮ መውጣት ችለዋል።

ምንም እንኳን እንደ መጀመሪያው ሁሉ አሁንም ፋሲል ከዋሻው ውስጥ በሕይወት ይወጣል የሚል ተስፋ በቤተሰቡ ዘንድ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን አስጨናቂ ስጋት ተፈጥሮባዋቸል።

በአካባቢው ባለው የኦፓል ማዕድን ማውጫ ዋሻ ላይ ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ የመደርመስ አደጋ አጋጥሞ፣ ማዕድን ፈላጊዎቹ ለ11 ቀናት ያህል በዋሻ ውስጥ ቆይተው በሰው ኃይል በተደረገ ቁፋሮ በሕይወት የወጡ ሰዎችም አሉ።

የፋሲል ቤተሰብም ከዛሬ ነገ ከተደረመሰበት ጉድጓድ ከጓደኞቹ ጋር በሕይወት ይወጣል በሚል በተስፋ እንዲጠብቁ ያደረጋቸውም ይህ ነው።

ነገር ግን ቀናት በቀናት ላይ ተደርበው ሳምንት አለፋቸው፤ ከዚያም እነሆ አሁን ሁለት ሳምንት ሆናቸው። ይህ ቀስ እያለ እየተራዘመ የሄደው ጊዜ በውስጣቸው የነበረውን ተስፋ እያመናመነው እንደሆነ ቤተሰቦች እየተናገሩ ነው።

“እዚያ ዋሻ ውስጥ ሆነው እርስ በርስ እየተያዩ መሞት መፈጠርን የሚያስጠላ ነው” የሚሉት አቶ ጌጡ፣ መንግሥት የተሻለ መፍትሔ ይዞ በፍጥነት ያልደረሰበት ምክንያት አልገባኝም” ሲሉም ይጠይቃሉ።

አቶ ጌጡ ከሁሉም ያሳሰባቸው በከባድ ሐዘን ውስጥ የሚገኙት እናታቸው ሁኔታ ነው።

“እናታችን በጣም እየተጎዳች ነው። ወንድሜ ለሳምንታት ያለበት ሁኔታ ሳይታወቅ እንደወጣ በመቅረቱ የተፈጠረባት ስሜት ከባድ ነው። እራሷ ላይ ጉዳት እንዳታደርስ እየተጠበቀች ነው” ሲል አደጋው በቤተሰባቸው ላይ የፈጠረውን ቀውስ ተናግረዋል።

የማዕድን ማውጫው ያለበት ገደላማ ስፍራ የቁፋሮ ማሽን ማስገባት ብቻ ሳይሆን፣ በርካታ ሰዎችን ለቁፋሮ ለማሰማራት አስቸጋሪ ከመሆኑ በተጨማሪ በዋሻው አናት ላይ የተንጠለጠለ አለት ተደርምሶ አደጋ ሊያደርስ ይችላል በሚል ስጋት ቁፋሮው ከተቋረጠ ቀናት ተቆጥረዋል።

በሰው ኃይል ሲደረግ የቆየው ነፍስ የማዳን ቁፋሮ ተጨማሪ አደጋን እንዳያስከትል እንዲቆም ከተደረገ በኋላ ሌላ አማራጭ ሲፈለግ ቀናት ተቆጥረዋል።

በዚህም የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ሰኞ የካቲት 11/2016 ዓ.ም. ሊደረመስ ይችላል የተባለውን የዋሻውን የላይኛ ክፍል በፈንጂ ለማፍረስ ሞክረው ነበር። ነገር ግን ይህ አማራጭ የሚፈለገውን ውጤት ሳያስገኝ መቅረቱን የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በትክክል በዋሻው ውስጥ ተቀብረዋል ተብለው በውል የታወቁ ስምንት አባላቱ ሕይወት አደጋ ላይ እንደሆነ የሚገልጸው የከበሩ ማዕድናት አምራቾች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ አጋዥ፣ ሊደረመስ ይችላል የተባለው የዋሻ ክፍልን “በታንክ የመምታት” ሃሳብ እንዳለ ተናግሯል።

ስጋት የሆነው ከዋሻው በላይ የተንጠለጠለው አለት ሊወገድ ከቻለ “ሰዎቹን ቆፍሮ የማውጣት ዕድል ይኖር ነበር” ይላል አቶ ተስፋዬ፤ ይህ ስፍራ ከተናደ በኋላ ነዋሪዎች ቁፋሯቸውን ቀጥለው ማዕድን አውጪዎቹን ማዳን ይችላሉ የሚል እምነታቸውንም ገልጸዋል።

ይሁንና “በታንክ መምታት” የሚለው ሃሳብን በተመለከተ እስካሁን ድረስ ውሳኔ ላይ አለመደረሱን ጠቅሰዋል።

አቶ ጌጡ በበኩላቸው ቀደም ብለው ዋሻው በመድፍ እንዲመታ ጠይቀው እንደነበር በመግለጽ “ለጥያቄያችን መልስ አላገኘንም” ብለዋል።

ተመሳሳይ ሃሳብ የሚያነሱት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪው አቶ አሊ “መፍትሄ መስጠት የሚቻለው ባለሙያዎች ሁኔታውን አይተውት፤ በታንክ ቢመታ የሚፈለገው ውጤትን ያስገኛል ወይ የሚለው መረጋገጥ አለበት” ሲሉ ለውሳኔው መዘግየት ምክንያቱን ጠቅሰዋል።

የአማራ ክልል መስተዳደርም ሆነ ከመከላከያ ሠራዊቱ ውጪ የፌደራል መንግሥቱ የሚመለከታቸው አካላት እስካሁን በይፋ ያሉት ነገር የለም።

ቢቢሲ ስለ ጉዳዩ የማዕድን ሚኒስቴር ባለሥልጣናትን ለማነጋገር ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራም ስልካቸው ባለመነሳቱ አልተሳካም።