በደቡብ ወሎ ማዕድን ሲያወጡ ናዳ የተጫናቸውን በርካታ ሰዎች የማውጣት ጥረት አራተኛ ቀኑን ያዘ

የከበረ ድንጋይ

የፎቶው ባለመብት, South Wollo Communication

በአማራ ክልል፣ ደቡብ ወሎ ዞን ፣ ደላንታ ወረዳ የኦፓል ማዕድን በማውጣት ላይ ሳሉ ዋሻ የተደረመሰባቸውን በርካታ ሰዎች ለማውጣት የሚደረገው ጥረት አራተኛ ቀኑን ያዘ።

የአካባቢው ባለሥልጣን እና የከበረ ማዕድን አውጪዎች ማኅበር ሊቀመንበር ለቢቢሲ እንደተናገሩት በቁጥር ከ8 እስከ 30 የሚገመቱትን ሰዎች ለማውጣት የአካባቢው ማኅበረሰብ ጥረት እያደረገ ቢሆንም እስካሁን ውጤት አልተገኘም።

የወገል ጤና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ዓለምነው ፍለጋውን በማሽን ለማገዝ የአካባቢው መልከዓ ምድር ምቹ ባለመሆኑ ጥረቱን አዳጋች አድርጎታል ብለዋል።

በሕጋዊ መንገድ ተሰማርተው በማዕድን ቁፋሮ ላይ የነበሩት ሰዎች ናዳ የተጫናቸው ከአራት ቀናት በፊት ነበር። ሌሎች የአካባቢው ወጣቶችም አብረው ሳይኖሩ እንዳልቀረ ተነግሯል።

ትናንት እሁድ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ አያሌው በሪሁን ባለፉት ቀናት ከአምስት መቶ በላይ ሰዎች በነፍስ አድን ሥራው ላይ እገዛ ለማድረግ ወደ ሥፍራው ቢያቀኑም፣ ወደ ዋሻው ለማምራት የሚያስችለው መንገድ ጠባብ እና በአንድ ጊዜ ከአስር ሰዎች በላይ ማስገባት ባለመቻሉ ጥረታቸው አዝጋሚ መሆኑን ተናግረዋል።

ስምንቱ የማኅበሩ አባላት በናዳው ተይዘው እንደሚገኙ የገለጸው ወርቅ ዋሻ የከበሩ ማዕድናት አምራቾች ማኅበር ሊቀመንበር ተስፋዬ አጋዥ በበኩሉ እስካሁን በተደረገው ጥረት 150 ሜትር ርዝማኔ ወዳለው ዋሻ ዘልቆ ለመግባት መቆፈር የተቻለው 33 ሜትር ገደማ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።

ሐሙስ ጥር 30/2016 ዓ.ም. ምሽት 3፡00 አካባቢ ናዳው እንደተከሰተ ከአካባቢው ሰው መስማቱን የገለጸው ሊቀመንበሩ፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የአካባቢው ሕዝብ ሌት ተቀን ርብርብ እያደረገ ነው ብሏል።

በሰሜኑ ጦርነት እንዲሁም አሁን ላይ በክልሉ የሚካሄደውን ግጭት ተከትሎ ሕገ ወጥ የማዕድን አውጪዎች በአካባቢው ተሰማርተው እንደነበር የገለጸው ተስፋዬ፣ ይህ ለዋሻው መደርመስ አንዱ ምክንያት መሆኑን ተናግሯል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ አደጋ ከተከሰተ በኋላ በመንግሥት በኩል የተቀበሩትን ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅም ሆነ ከዋሻው ለማውጣት የተደረገላቸው ድጋፍ እንደሌለም ገልጿል።

የወገል ጤና ከንቲባ አቶ ተስፋዬ ግን እርሳቸውን ጨምሮ የወረዳውም ሆነ የከተማው አመራር በሥፍራው እንደሚገኝ ገልጸው፣ በቂ ድጋፍ ማድረግ ያልተቻለው አማራጭ ስለሌለ መሆኑን አስረድተዋል።

“ጥረቱን በማሽን ለማገዝ አልተቻለም፤ ማዕድን አውጪዎቹም ባህላዊ ማዕድን አምራች ተብለው የተሰማሩት ቦታው ከባህላዊ ቁፋሮ ውጪ የሚቻል ባለመሆኑ ነው። ቦታው ለእግር መንገድ እንኳን ምቹ አይደለም” ብለዋል።

በመሆኑም ለቀናት በዋሻ ውስጥ ተቀብረው የሚገኙትን ግለሰቦች ለማውጣት በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ተሰማርተው በእጅ ቁፋሮ ለማውጣት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ከንቲባው ገልጸዋል።

ከሦስት ዓመታት በፊት በተመሳሳይ አደጋ በዋሻ ውስጥ ተቀብረው አስራ አንድ ቀናት ቆይተው በሕይወት የወጡ ግለሰቦች መኖራቸውን ያስታወሱት ባለሥልጣኑ፣ እነዚህም በሕይወት ይወጡ ይሆናል የሚል የተስፋ ጭላንጭል እንዳላቸው ተናግረዋል።

ከ100 ሜትር በላይ ርዝማኔ ያለው ዋሻ መግቢያ ላይ የተደረመሰውን አፈር በማንሳት 30 ሜትር ገደማ መግባት እንደተቻለ እና ይህም ተስፋ እንደሰጣቸው አክለዋል።

“ዋሻው ሰፊ በመሆኑ ትንሽ አየር ማግኘት ከቻሉ በሕይወት የመትረፍ ዕድል ሊኖራቸው ይችላል” ብለዋል።

በአካባቢው በባህላዊ መንገድ ማዕድን በማውጣት ሥራ ላይ ተሰማሩ በርካታ ሕጋዊ ማኅበራት ይገኛሉ።

በወረዳው መሰል አደጋ ሲያጋጥምም ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ከዚህ ቀደም በሕገ ወጥ መንገድ ማዕድን ሲያወጡ በነበሩ ግለሰቦች ላይ ተመሳሳይ አደጋ አጋጥሞ የአራት ወጣቶች ሕይወት ማለፉን የወርቅ ዋሻ ማኅበር ሊቀመንበር አስታውሷል።

ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮም በወረዳው በማዕድን ቁፋሮ ወቅት በሚያጋጥም ናዳ ምክንያት ቢያንስ 50 ሰዎች መሞታቸውን እንደሚያውቅም ሊቀመንበሩ ተናግሯል።