ሩሲያ በዩኬ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች ላይ ማዕቀብ ጣለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሩሲያ 54 የዩናይትድ ኪንግደም ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች እንዲሁም በእንግሊዝ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ግለሰቦች ወደ አገሯ እንዳይገቡ ማገዷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
እግዱ የተጣለው ዩናይትድ ኪንግደም በሩሲያ ዜጎች ላይ ለጣለችው ዕቀባ አጸፋዊ ምላሽ መሆኑም ተገልጿል።
በሩሲያ እግድ ከተላለፈባቸው መካከል የአገሪቱ የባህል ጸሐፊ ሉሲ ፍሬዘር እንዲሁም የዓለም ዓቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ዋና አቃቤ ሕግ ካሪም ካን ይገኙበታል።
በተጨማሪም በርካታ የቢቢሲ፣ የደይሊ ቴሌግራፍ እና የጋርዲያን ጋዜጠኞችም በዝርዝሩ ውስጥ ተካትተዋል።
ይህንንም እገዳ ተከትሎ ቢቢሲ “ገለልተኛ እና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ሪፖርት ማድረጉን ይቀጥላል” ሲልም መግለጫ አውጥቷል።
እርምጃው “ለንደን ጸረ-ሩሲያ የሆኑ እና በጸበኝነት የተሞሉ እርምጃዎችን በመውሰዷ የተሰጠ አጸፋዊ ምላሽ ነው” ሲልም ነው የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያስታወቀው።
የባህል ጸሐፊዋ ሉሲ ፍሬዘር “ሩሲያ ከዓለም አቀፉ የስፖርት መድረክ እንድትገለል በንቃት በመሳተፋቸው” ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።
እንዲሁም የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስትር ዲኤታ አናቤል ጎልዲ “ለዩክሬን የጦር መሳሪያ በማቅረብ” እቀባው እንደተላለፈባቸው ሩሲያ አስታውቃለች።
የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ መጋቢት ወር ላይ የእስር ትዕዛዝ ማውጣቱ ይታወሳል።
ፕሬዝዳንቱ ህጻናትን በሕገወጥ መንገድ ከዩክሬን ወደ ሩሲያ ማፈናቀልን ጨምሮ በጦር ወንጀሎች ተጠያቂ ናቸው የተባለ ሲሆን ሩሲያ ይህንን ሐሰት ነው ብላለች።
የፍርድ ቤቱ ዋና አቃቤ ሕግ ካሪም ካን በወቅቱ ለቢቢሲ እንደተናገሩት “ህጻናት እንደ የጦር ምርኮኛ ተደርገው ሊወሰዱ አይችሉም። በአስገዳጅ መልኩ ሊወሰዱ አይገባም” ብለው ነበር።
በእቀባው ውስጥ ከተካተቱት የቢቢሲ ጋዜጠኞች መካከል ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ዲቦራ ተርነስ፣ የዜና አቅራቢ እና የትንታኔ ኤዲተር የሆነው ሮስ አትኪንስ እንዲሁም የማኅበራዊ ሚዲያ ዘጋቢዋ ማሪያና ስፕሪንግ ተጠቅሰዋል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህንን ዝርዝር እንደሚጨርምበትም ተናግሯል።
ሩሲያ ቀደም ሲል በርካታ የብሪታንያ ጋዜጠኞች፣ የመከላከያ ኃላፊዎች እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ የምክር ቤት አባላት ላይ እግድ ማስተላለፏ ይታወሳል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ በፈጸመችው ወረራ ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በርካታ ምዕራባውያን አገራት ማዕቀብ ጥለዋል። ከእነዚህም መካከል እንደ አልማዝ፣ ነዳጅ፣ ጋዝ ያሉ ከሩሲያ የሚመጡ ሸቀጦችን ከልክሏል። በተጨማሪም ከ1 ሺህ በላይ የሩሲያ የንግድ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ዩኬን ጨምሮ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ ኅብረት እና በሌሎች አገራት ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።












