ለትግራይ የሚቀርበው እርዳታ መቋረጡን ተከትሎ 1 ሺህ 400 ሰዎች በረሃብ መሞታቸው ተነገረ

በትግራይ እርዳታ ላልተገባ ዓላማ መዋሉን ተከትሎ እርዳታ በመቋረጡ ቢያንስ 1 ሺህ 400 ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን አንድ ባለሥልጣን ተናገሩ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም እንዲሁም የአሜሪካ መንግሥት የዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) ለትግራይ የሚያደርጉትን የምግብ እርዳታ ከአራት ወራት በፊት አቋርጠዋል።
የትግራይ ባለሥልጣናት ባደረጉት ምርመራ ወደ 500 የሚጠጉ ሰዎች በስርቆቱ ተሳትፈው መገኘታቸውን አንድ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በትግራይ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. የተከሰተውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ተከትሎ በርካቶች ለረሃብ ተዳርገዋል።
ለበርካታ ሚሊዮኖች ሰቆቃ ምክንያት የሆነውን ይህንን ጦርነት ለመቋጨትም በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በህወሓት እና በፌደራሉ መንግሥት መካከል ከዘጠኝ ወራት በፊት ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት ተፈርሟል።
በዚህ ጦርነት ላይ በርካታ የጦር ወንጀሎችን መፈጸማቸው ሪፖርት የተደረገው የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ጦር ጋር አጋር ሆነው ተዋግተዋል።
በጦርነቱ ወቅት መብራት፣ ውሃ እና የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎትን ጨምሮ በርካታ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲታገዱ ተደርጓል፤ እንዲሁም የሰብዓዊ እርዳታዎችም እንዲቆሙ ሆነው ቆይተዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ተወካይ በመሆን አሸማጋይ የነበሩት የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት ወደ 600 ሺህ ያህል ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል ብለዋል።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች የረገፉት በጦርነት፣ በረሃብ እና በሕክምና በማጣት እንደሆነ ተመራማሪዎች ተናግረዋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና ዩኤስኤአይዲ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆችን ለመርዳት የሚያደርጉትን እርዳታ ከአራት ወራት በፊት ሲያቆሙ የሰጡት ምክንያት እርዳታው ለተቸገሩ ሰዎች ሳይደርስ በገበያዎች ላይ ለሽያጭ እየዋለ በመሆኑ ነው።
ነገር ግን እርዳታውን ባልተገባ መልኩ ማን ወደ ገበያ እያሰራጨው እንዳለ አልገለጹም።
“የወንጀል ድርጊት ሲፈጸም ዐይናችንን ጨፍነን ዝም ብለን እርዳታ ማድረስ አንችልም” ሲሉ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቃለ አቀባይ በዚህ ሳምንት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቢቢሲ የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና ዩኤኤስኤአይዲ የመሳሰሉ የተራድኦ ድርጅቶች አርማዎችን የያዘ ምግብ በትግራይ መዲና መቀለን ጨምሮ፣ በሌሎች ከተሞች በገበያዎች ላይ ተመልክቷል። ነገር ግን የእርዳታ እህሉ በሙስና “አቅጣጫው ተቀይሮ ገበያ” ላይ ውሎ ይሁን ወይም እርዳታ ተቀባዮች ገንዘብ ፈልገው ለነጋዴዎች ሸጠውት ይሁን ግልጽ አይደለም።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም እንዲሁም የአሜሪካ መንግሥት የዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) በተቀረውም የኢትዮጵያ ክፍል የሚያደርጉትን እርዳታ በሰኔ ወር ማቋረጣቸውን አስታውቀዋል።
ዩኤስኤአይዲ በጦርነት፣ በድርቅ እና በኑሮ ውድነት ምክንያት ለእርዳታ ጥገኛ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን የሚረዳ ትልቁ የምግብ ለጋሽ ነው።
የውጭ አገራት ለጋሽ ድርጅቶች ውስጣዊ ማስታወሻ በበኩሉ ለተረጂዎች መድረስ የነበረበት መጠነ ሰፊ እርዳታ በፌደራል እና በክልል የመንግሥት አካላት አቀናባሪነት ስርቆት መፈጸሙን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ይህ ሰብዓዊ እርዳታ ለኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት እና ለቀድሞ ተዋጊዎች መዋሉም ተነግሯል።
በተጨማሪም እርዳታው በገበያ ላይ የዋለ ሲሆን ተፈጭቶም ወደ ውጭ አገራት መላኩም ተዘግቧል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የተባለውን ውንጀላ እያጣራሁ ነው ቢልም የምርመራው ውጤት እስካሁን ይፋ አልሆነም።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በስርቆት ከመጣ እርዳታ ተጠቃሚ እንዳልሆነ ገልጿል።
እርዳታው በመቋረጡ በሦስት ዞኖች ብቻ 1 ሺህ 411 ሰዎች በረሃብ ምክንያት መሞታቸውን የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት የአደጋ ስጋት አስተዳደር ኮሚሽነር ገብረ ሕይወት ገብረ እግዚአብሔር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኮሚሽነሩ የጠቀሷቸው ምሥራቅ፣ ሰሜናዊ ምሥራቅ እና ደቡባዊ ምሥራቅ ዞኖችን ነው።
ከትግራይ ሌሎች ሦስት ዞኖች የተገኘው መረጃ እስካሁን ያልተሰበሰበ ሲሆን፣ የሟቾችንም ቁጥር ከዚህ ከፍ ያለ እንደሚያደርገው ዶክተር ገብረ ሕይወት ተናግረዋል።
እስካሁን ድረስ ከእርዳታ ስርቆት ጋር በተያያዘ 492 ተጠርጣሪዎች ምርመራ እንደተከፈተባቸው የሚናገሩት ኮሚሽነሩ 198ቱ ላይ ክስ መመሥረቱን ገልጸዋል።
ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች መካከልም የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሠራተኞች፣ በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች በተገነቡ መጠለያዎች ውስጥ የሚገኙ አስተባባሪዎች እንዲሁም “የእርዳታ ምግብን የሚያከፋፍሉ አጋሮች” እንደሚገኙበት ዶክተር ገብረ ሕይወት ያስረዳሉ።
ምርመራው ሊጠናቀቅ ጥቂት እንደቀረው የሚናገሩት ዶክተር ገብረ ሕይወት አክለውም “የቢዝነስ ሰዎች (ነጋዴዎች) በተለይም የምግብ መሸጫ እና የእህል መፍጫ ባለቤቶችም ተሳትፈዋል” ብለዋል።
በሰኔ ወር ዩኤስኤአይዲ የምግብ እርዳታውን የሚቀጥለው “እርዳታው ለታሰበለት ለተቸገሩ ሰዎች ይደርሳል የሚል እምነት ሲጣልበት ነው” ሲል አስታውቋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቃለ አቀባይ በበኩላቸው የምግብ እርዳታውን ለማስቀጠል ተቋሙ ጥረቱን እያፋጠነ ነው ብለዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች የተወሰነ መጠን ያለው ምግብ ማከፋፈል የጀመረ ሲሆን፣ ይህም “እየተተገበሩ ያሉ ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን ለመፈተሽ እና እርዳታ ላልተገባለት ዓላማ እንዳይውል ለማረጋጋጥ” መሆኑም ተገልጿል።
“የዓለም ምግብ ፕሮግራም እርዳታው መቆሙ በሚረዳቸው ቤተሰቦች ላይ እያሳደረ ያለው ተጽእኖ በእጅጉ ያሳስበዋል። ስለዚህ የምግብ እርዳታ መድረሱን እና ለታሰቡት ተጠቃሚዎች እንዲውል ለማድረግ የመከላከያ እርምጃዎችን እያጠናከርን ነው” ብለዋል ቃለ አቀባይዋ።
ቢቢሲ በትግራይ ረሃቡ ያስከተለውን ቀውስ ለማየት ከትግራይ ትልልቅ ከተሞች አንዷ የሆነችውን የሽረ ከተማን ጎብኝቷል።
የደም ማነስ ችግር ያለባት እና የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ወይዘሮ መብርሂት ኃይላይ በምግብ እጦት ምክንያት ለመለመን መገደዷን ለቢቢሲ ተናግራለች።
“አብዛኞቹን ቀናት እንጀራ በጨው ተምትመን እንበላለን። ዶክተሮቹ የተመጣጠነ ምግብ እንድበላይ ይነግሩኛል። ነገር ግን ከየት አመጣለሁ?” ስትል የ28 ዓመቷ እናት ትጠይቃለች።
የአምስት ዓመት እና የሁለት ዓመት ተኩል ልጆቿም ሰውነታቸው ቀጭጯል፣ ዐይኖቻቸውም ጎድጉደዋል እንዲሁም አጥንታቸው ገጦ መታየቱም እያለፉበትን ያለውን ረሃብ ያሳብቃል።
“ዕድለኛ ከሆኑ በቀን አንድ ጊዜ ይመገባሉ፣ በሌለ ቀን ግን ተርበው ይተኛሉ” ትላለች መብርሂት።
መብርሂትን ቢቢሲ ባገኛት ወቅት ቀኗ የደረሰ ነፍሰ ጡር ትመስል በነበረበት ጊዜ ነው። ከጥቂት ቀናት በኋላም ሴት ልጅ በሰላም እንደተገላገለች እና ጤነኛም እንደሆነች ለቢቢሲ ተናግራለች።
በአካካቢው በሚገኝ ሆስፒታል ነርስ የሆኑት ክብራ መብራህቱ በርካታ አራሶች በረሃብ ምክንያት ጡታቸው እንደደረቀ እና ልጆቻቸውን ማጥባት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
“በርካታ ጨቅላዎች ወደዚህ ሆስፒታል ሲመጡ ለሞት ተቃርበው ነው” ብለዋል።
“በዚህ ወር ብቻ አራት ህጻናትን አጥተናል። የጦርነቱ ሰቆቃ፣ የምግብ እጥረት እና የትራንስፖርት እጦት አሁንም ጎልተው ይታያሉ” ሲሉ ተናግረዋል።
የስምንት ዓመቷ ራሄል ተወልደ የጎድን አጥንቶቿ ገጠው በሆስፒታል ውስጥ ተኝታ ቢቢሲ ተመልክቷል። ክብደቷ 10 ኪሎ ግራም ሲሆን፣ ይህም አማካይ የአንድ ዓመት ልጅ ክብደት ነው።
እናቷ ሕይወት ለባሲ ያለው ሙስ እና የምግብ እርዳታው እንዲቋረጥ ምክንያት ሆኗል የሚል ዕምነት አላት።
“እርዳታው በተገቢው ተከፋፍሎ ቢሆን ኖሮ አይቆምም ነበር” ብላለች።












