የተባበሩት መንግሥታት እስራኤል በጋዛ ሆስፒታሎች ላይ የፈፀመችው ጥቃት የጦር ወንጀል ነው ሲል ወቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተባበሩት መንግሥታት መርማሪ ኮሚሽን እስራኤል ከሐማስ ጋር በምታደርገው ጦርነት “የጋዛን የጤና ሥርዓት ለማጥፋት ያለመ ፖሊሲ አራምዳለች” ሲል ወቅሷል።
ኮሚሽኑ እንዳለው እስራኤል በጋዛ የጤና ተቋማት ላይ የምታደርሰው ጥቃት እና ፍልስጤማዊያን እስረኞች ላይ እያደረሰች ያለችው ጥቃት ከጦር ወንጀል እና ሰብዓዊነትን “ለማጥፋት” ከሚፈፀም ወንጀል ጋር የሚስተካከል ነው።
ሐማስ እና ሌሎች የፍልስጤም ቡድኖችም በተለይ ጋዛ ባሉ እስራኤላዊያን ታጋቾች ላይ በሚያደርሱት ጥቃት በጦርነት እና ሰብዓዊነት ላይ በሚፈፀም ወንጀል ተወቅሰዋል።
እስራኤል ለዚህ የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት እስካሁን ምላሽ ባትሰጥም ከዚህ ቀደም የወጡ የመንግሥታቱ ድርጅት ዘገባዎችን ማጣጣሏ እና ድርጅቱ ሚዛናዊ አይደለም ስትል መወቀሷ አይዘነጋም።
አዲሱ የምርመራ ውጤት ለተበባሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ በያዝነው የአውሮፓውያኑ ወር መገባደጃ ላይ ይቀርባል።
ኮሚሽኑን የሚመሩት ደቡብ አፍሪካው የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኃላፊ ናቪ ፒሌይ ናቸው።
የእስራኤል ጦር ሠራዊት አባላት “ሆን ብለው የጤና ባለሙያዎችን ገድለዋል፣ አስረዋል እንዲሁም አሰቃይተዋል” የሚለው ሪፖርት ሕፃናት “በፈራረሰ የጤና ሥርዓት” ውስጥ እየተወደለዱ መሆኑን አመላክቷል።
የኮሚሽኑ ረፖርት ከቤተሰቦቿ ጋር በመሸሽ ላይ ሳለች መኪናዋ በቦምብ የተመታው የአምስት ዓመቷ ሂንድ ራጃብን ታሪክ ዋቢ አድርጊ አካቷል። በቦምብ ጥቃቱ ምክንያት በርካታ ሰዎች ሲመቱ ሂንድ የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ማሕበር ስልክ ላይ ደውላ እርዳታ ጠይቃለች። ነገር ግን የቦምብ ጥቃቱ ወደደረሰበት ሥፍራ ሲሄድ የነበረው አምቡላንስም ጥቃት ደርሶበታል። ሂንድ፣ ቤተሰቦቿ እና የአምቡላንሱ አባላት ተገድለዋል።
ሪፖርቱ አክሎ በጤና ተቋማት ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት “ለሚመጣው የፍልስጤም ትውልድ ትልቅ ውድመትን ትቶ ያለፈ እና ለመላው የፍልስጤም ሕዝብ ትልቅ ጉዳይ ሊሆን የሚችል ነው” ይላል።
ኮሚሽኑ ሐማስን ጨምሮ የፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖች እስራኤላዊያን ታጋቾችን “ለአካላዊ ስቃይ፣ ለወሲባዊ ጥቃት፣ ለመገለል ዳርገዋል። ንፅሕና፣ ውሀ እና ምግብ ከልክለዋል፣ አስፈራርተዋል፤ አዋርደዋቸዋል” ሲል ወቅሷል።
በሐማስ እገታ ሥር የሚገኙ እስራኤላዊያን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በፍጥነት እንዲለቀቁ ኮሚሽኑ ጠይቋል።
ሪፖርቱ በእስራኤል የታሰሩ ሕፃናትን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማዊያን እስረኞች ያሉበት ሁኔታም እንደሚያሳስበው አሳውቋል።
የእስራኤል የፀጥታ ኃይል አባላት የተቀነባበረ ጥቃት፣ ስቃይ፣ መደፈር እና ሌሎች ወሲባዊ ጥቃቶች እያደረሱባቸው ነው ሲል ኮሚሽኑ ይወቅሳል።
ኮሚሽኑ በምርመራ ውጤቱ እንደሚለው የእስራኤል ደኅንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን-ግቪር በሰጡት “ትዕዛዝ መሠረት ነው” ይህ በደል ሊደርስ የቻለው ሲል የሚኒስትሩን ስም ጠቅሶ ወቀሳውን አሰምቷል።
ሪፖርቱ በርካታ ዝርዝር መረጃዎች ይዞ የወጣ ሲሆን ዓለም አቀፉ የፍትሕ ችሎት እና ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ካወጡት ጋር የሚተካከል ሲሆን በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ሁኔታ አስጊ መሆኑን ያመለክታል።
ሐማስ ከአንድ ዓመት በፊት እስራኤል ላይ ባደረሰው ጥቃት 1200 ሰዎችን ገድሎ 251 ሰዎችን ደግሞ አግቶ መውሰዱ ይታወሳል። ይህን ተከትሎ እስራኤል በጋዛ የመሬት ለመሬት እና የአየር ጥቃቶችን ስታደርስ ቆይታለች።
ባለፉት 12 ወራት በጋዛ ከ42 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።












