በጦርነት እያታመሰ በሚገኘው መካከለኛው ምሥራቅ የሰላም ተስፋ እየጨለመ ነው?

አንዲት ሴት በጥቅምት ሰባቱ ጥቃት የተገደሉ እስራኤላዊያንን ምስል ከያዘ ቢልቦርድ ፊት ቆማ

የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/REX/Shutterstock

በጦርነት እያታመሰ በሚገኘው መካከለኛው ምሥራቅ የሰላም ተስፋ እየጨለመ ነው?

የመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ በጦርነት ነውጥ መናጥ ከጀመረ እነሆ አንድ ዓመት ደፈነ።

እስራኤል በታሪኳ እጅግ ዘግናኝ የሚባል ጥቃት ደርሶባታል። ጋዛ በእስራኤል የቦምብ ጥቃት ወድማለች።

እርግጥ ነው የእስራኤል-ፍልስጤም ግጭት አዲስ አይደለም። ነገር ግን ላለፉት ዓመታት የመገናኛ ብዙኃን ርዕስ ከመሆን ተቀዛቅዞ ቆይቷል።

አሁን ነጋ ጠባ ዜናው እስራኤል፣ ፍልስጤም፣ መካከለኛው ምሥራቅ ሆኗል።

ብዙዎች ባልጠበቁት ጊዜ ነው ይህ የሆነው። እንዲያውም የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን ከሐማስ ጥቃት ከአንድ ሳምንት በፊት ነው “መካከለኛው ምሥራቅ አሁን ሰላም ሆኗል። ባለፉት 20 ዓመታት እንዲህ ያለ ሰላም ተላብሶ አያውቅም” ብለው ነበር።

እሳቸው ይህን ካሉ በኋላ ባለው አንድ ዓመት ብዙ መዓት በአካባቢው ተከስቷል።

ከ41 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል። ሁለት ሚሊዮን የጋዛ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል። በዌስት ባንክ 600 ፍልስጤማውያን ተገድለዋል። በሊባኖስ ደግሞ ከ2 ሺህ በላይ ሲሞቱ ከአንድ ሚሊዮን በላዩ ተሰደዋል።

ከአንድ ዓመት በፊት በአንድ ቀን ከ1200 በላይ እስራኤላውያን በሐማስ ጥቃት ተገድለዋል። በጋዛ ባለው ጦርነት ምክንያት እስራኤል ከ350 በላይ ወታደሮች ተገድለውባታል።

እንዲሁም ከ200 ሺህ በላይ እስራኤላውያን ከጋዛ አቅራቢያ እና ከሊባኖስ ድንበር ተፈናቅለዋል። በሄዝቦላህ የሮኬት ጥቃት ከ50 በላይ ወታደሮች እና ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።

በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ ሌሎች አገራት እና ቡድኖች ጦርነቱን ተቀላቅለዋል። አሜሪካ ሁኔታውን ለማብረድ ያደረገችው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ውጤት አላስገኘም። ከኢራቅ እና ከየመን ሳይቀር ሮኬቶች እየተተኮሱ ነው።

ዓይን እና ናጫ የሆኑት እስራኤል እና ኢራንም የሚሳዔል ጉልበታቸውን እየተለካኩ ነው። ወደፊት ተጨማሪ ጥቃት እንደሚሰነዝሩም አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ እየዛቱ ይገኛሉ።

ዋሺንግተን እንዲህ አቅም አልባ ሆና ታይታ አታውቅም።

መገናኛ ብዙኃን ከአንድ ዓመት በፊት የጋዛ ነዋሪዎች ሕይወት ምን ይመስል እንደነበር የረሱት ይመስላሉ። ሁሉም ትንፋሹን ዋጥ አድርጎ እየተጠባበቀ ያለው በመካከለኛው ምሥራቅ “የለየለት ጦርነት” ይከሰታል ወይ የሚለው ነው።

መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ በፈጸመው ጥቃት ሕይወታቸው የተመሰቃቀለ እስራኤላውያንም ጉዳይ ተረስቷል።

“እኛ ተገፍተናል” ይላሉ ልጃቸው በሐማስ የታገተባቸው አባት የሁዳ ኮኽን። ኮኽን ኔታኒያሁ “ጠላቶቻችን እንዲተባበሩብን ያደረገ የማይረባ ጦርነት ውስጥ አስገብቶናል” ሲሉ ይወቅሳሉ።

“የመስከረም 26 ጥቃትን ኢምንት ለማስመሰል ብዙ ነገር እያደረገ ነው [ኔታኒያሁ] እየተሳካለትም ነው” ይላሉ።

 በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7/2023 የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ በእስራኤል ዋና ዋና ከተሞች ሰልፍ ተካሂዷል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, እስራኤላዊያን ከአንድ ዓመት በፊት የደረሰባቸውን ጥቃት ዘክረውታል

እርግጥ ሁሉም እስራኤላዊ የኮኽንን ሐሳብ ይጋራል ማለት አይደለም። ብዙዎች እንሚያምኑት ከአንድ ዓመት በፊት ሐማስ ያደረሰው ጥቃት የእስራኤል ጠላቶች አገሪቱን ለማጥፋት የሚያደርጉትን ዘመቻ ያሳየ ነው።

እስራኤል በሚፈነዱ የግንኙነት መሳሪያዎች (ፔጀሮች)፣ ነጥላ በመግደል፣ ረዥም ርቀት ተጉዛ ቦምብ በመጣል እንዲሁም በደኅንነት መሥሪያ ቤቷ በኩል እያደረሰች ያለውን ጥቃት ተከትሎ በራስ መተማኗ እየጨመረ የመጣ ይመስላል።

ባለፈው ሳምንት ነው የእስራኤሉ መሪ ኔታኒያሁ “እስራኤል መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ እጇ የማይደርስበት ቦታ የለም” ሲሉ ደረታቸውን ነፍተው የተናገሩት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአንድ ዓመት በፊት ተቀባይነታቸው እያሽቆለቆለ የነበረ ሲሆን፣ በሄዝቦላህ መሪዎች ላይ በወሰዱት እርምጃ ምክንያት ያጡትን ድጋፍ መልሰው እያገኙ ነው። ይህ ተጨማሪ ጥቃት እንዲሰነዝሩ መነሳሳት ይሆናቸው ይሆን?

አሁን አሳሳቢው ጥያቄ ሁኔታዎች ወዴት እያመሩ ነው? የሚለው ነው።

ዩናይትድ ስቴትስ አሁን ተሳትፎዋ የጎላ ነው። የአሜሪካ ማዕካላዊ ዕዝ ኃላፊ ጄኔራል ማይክል ኩሪያ ከሰሞኑ ወደ እስራኤል ሄደዋል።

የአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ የጥቂት ሳምንታት ዕድሜ ቀርቶታል። መካከለኛው ምሥራቅ ተመሰቃቅሏል። ለጊዜው ያለፈው መፍትሔ ግጭቱ እንዳይስፋፋ ማድረግ ነው።

እስራኤል እና ወዳጆቿ ባለፈው ሳምንት ከኢራን ለደረሰባቸው የሚሳዔል ጥቃት ምላሽ መሰጠት እንዳለበት ያስባሉ። በጥቃቱ የተገደለ እስራኤላዊ አልነበረም። ኢራን ወታደራዊ እና የደኅንነት ዒላማዎችን መርጣ ነው የመታችው። ሆኖም ኔታኒያሁ የከፋ ምላሽ እንሰጣለን ሲሉ ዝተዋል።

ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ የጋዛ ሕፃናት

የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/REX/Shutterstock

የምስሉ መግለጫ, ከሐማስ ጥቃት በኋላ እስራኤል በጋዛ በከፈተችው ጦርነት ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ፍልስጤማዊያን ተሰደዋል

ኔታኒያሁ ለኢራን ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት ቴህራን ውስጥ የአገዛዝ ለውጥ ይመጣል ሲሉ ደፈር ብለው ተናግረዋል። “ኢራን ብዙዎች ከሚጠብቁት ጊዜ ቀድማ ነፃ ትሆናለች፤ ሁሉም ነገር ይለወጣል” ብለዋል።

አንዳንዶች የኔታኒያሁን ንግግር እና የአሜሪካ ባለሥልጣናት ኢራቅን ከመውረራቸው በፊት ያሰሙትን ንግግር አመሳስለውታል።

የኢራን አገዛዝ አጋሮቹ ሄዝቦላህ እና ሐማስ በተዳከሙበት ወቅት የመካከለኛው ምሥራቅ አድራጊ ፈጣሪ ከምትባለው እስራኤል ጋር የመግጠም ጉልበት አለው ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው።

እስራኤል ከኢራን የሚደርስባትን ጥቃት ብቻዋን መወጣት ሊከብዳት እንደሚችል ታውቀዋለች።

ፕሬዝደንት ጆ ባይደንም ሆኑ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር የተፋጠጡት ምክትሏ ካማላ ሃሪስ በኢራን የአገዛዝ ለውጥ መምጣት አለበት የሚለው ጉዳይ አጀንዳቸው ላይ ያለ አይመስልም።

ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን ላይ ሳሉ ኢራን የአሜሪካ አሳሽ ድሮንን መትታ መጣሏ ይታወሳል። ከሰባት ወር በኋላ በትራምፕ ትዕዛዝ መሠረት የኢራኑ ጉምቱ ጄኔራል ቃሲም ሴሌማኒ ተገደሉ።

ከአንድ ዓመት በፊት መካከለኛው ምሥራቅ ወደለየት ጥፋት እና ግጭት ይሄዳል ብሎ የገመተ አልነበረም። ጦርነቱ ሁለተኛውን ዓመት ቢይዝም ጋዛ እንዴት ታገግማላች ሳይሆን ሰፊ ጦርነት እናይ ይሆን? የሚለው ነው ትኩረት የተሰጠው።

ምናልባት እስራኤል ሐማስ እና ሄዝቦላህ ላይ አከርካሪ ሰባሪ ጥቃት አድርሻለሁ ብላ ስታስብ፤ የአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ተጠናቆ ሁኔታዎች ሲቀዛቀዙ፤ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ይገኝ ይሆናል።

ያ ቀን መቼ ነው የሚመጣው? የሚለውን ግን መገመት ከባድ ነው።