ወደ ዋይት ሐውስ ለመግባት ቁልፍ ናት የምትባለው ‘ወላዋይዋ’ ግዛት

ዶናልድ ትራምፕ እና ካማላ ሀሪስ

ወደ ዋይት ሐውስ የሚወስደው መንገድ ስሙ 1600 ፔንሲልቬኒያ አቬንዩ ነው። እሱን ይዘው ከዘለቁ ነጩ ቤተ-መንግሥት ይደርሳሉ። የሚያስገባዎት ግን የለም።

ወደ ዋይት ሐውስ መግባት ከፈለጉ ግን የግዛቷን ነዋሪዎች ቀልብ መግዛት አለብዎት።

የፔንሲልቬኒያ ግዛትን ድምፅ ያገኘ/ች ዕጩ ዋይት ሐውስ የመግባቱ/ቷ ነገር 90 በመቶ እርግጥ ነው ይላል የምርጫ ተንታኙ ኔት ሲልቨር።

“ወላዋይ ከሚባሉ ግዛቶች እጅግ ወሷኟ ናት” የሚሉት ዲሞክራቱ የኮንግረስ አባል ፓትሪክ መርፊ ከአውሮፓውያኑ 2007 - 2011 ሰሜን ምሥራቅ ፔንሲልቬኒያን ወክለው አገልግለዋል።

የአሜሪካ ምርጫ ኢሌክቶራል ኮሌጅ በተባለ ሥርዓት ይመራል። ይህ ማለት እያንዳንዱ ግዛት የተሰጠው የኤሌክቶራል ኮሌጅ (ድምፅ) መጠን አለው ማለት ነው። እንመለስበታለን።

ፔንሲልቬኒያ 19 ኢሌክቶራል ኮሌጅ አላት። በአሜሪካ ብዙ ነዋሪ ካላቸው ግዛቶች አምስተኛዋ ናት ስትሆን፤ ከ‘ወላዋይ’ ግዛቶች መካከል ደግሞ እጅግ ወሳኟ ናት። ወላይዋይ ግዛት ምንድነው? እሱንም እንመለስበታለን።

መግለጫ

ትራምፕ እና ካማላ ሃሪስ ተፋጠዋል። በተለይ ወሳኝ የሚባሉ ግዛቶች መራጮችን ልብ ለመያዝ ደፋ ቀና እያሉ ነው። ከሰሞኑ እንቅልፍ ያላቸው አይመስሉም።

ዲሞክራቶች ፔንሲልቬኒያን፣ ዊስኮንሲን እና ሚሺጋን የተባሉትን ግዛቶች ካሸነፉ እና ከኔብራስካ ግዛት አንዱን ቀጣና ከጨመሩበት ካማላ ሃሪስ ማንም ሳያግዳቸው ወደ ዋይት ሐውስ ይገባሉ።

ሪፐብሊካኖች ደግሞ ፔንሲልቬኒያን ጨምሮ ኖርዝ ካሮላይና እና ጆርጂያን የራሳቸው ካደረጉ ዶናልድ ትራምፕ መንበረ ሥልጣኑን ያለማንም ከልካይ ይይዛሉ።

አሜሪካ ፕሬዝደንቷን የምትመርጠው ኢሌክቶራል ኮሌጅ በተባለ መንገድ ነው። ይህ ማለት እያንዳንዱ ግዛት እንዳለው የሕዝብ ብዛት መጠን ድምፅ ይሰጠዋል ማለት ነው።

በጠቅላላው 538 ኢሌክቶራል ኮሌጅ የሚባሉ ድምፆች አሉ። ዕጩዎች ዋይት ሐውስ ለመግባት ቢያንስ 270 የግዛቶችን ኢሌክቶራል ኮሌጅ ድምፅ ማግኘት አለባቸው።

ትራምፕ ፔንሲልቬኒያን ካላሸነፉ አሊያም የዲሞክራቶች ከሚባሉ ግዛቶች አንደ ሦስቱን ካልጠቀለሉ ወደ ነጩ ቤተ-መንግሥት የመግባታቸው ነገር አጠራጣሪ ነው።

በእንግሊዝኛው ‘ኪስቶን ስቴት’ ይሏታል። ቁልፍ ግዛት ብንላት ትርጉሙ ይመጥናታል።

ቢቢሲ የአሜሪካ ምርጫን በተለመለከተ የሚያዘጋጀው ልዩ ዘገባ ቀጥታ የሚሠራጨው ከዚህች ግዛት ነው። ታድያ ቁልፍ ግዛት መባል ያንሳታል?

የምርጫው አውድማዋ ትንሿ አሜሪካ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ወላዋይ ግዛት የሚል ሐሳብ አንስተን ነበር። አሜሪካ 50 ግዛቶች አሏት። ሁለቱ አውራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማለትም ዲሞክራት እና ሪፐብሊካን እኒህን ግዛቶች ተቃርጠዋቸዋል። ይህ ማለት የትኛው ግዛት ለየትኛው ፓርቲ ድምፁን እንደሚሰጥ ይታወቃል ማለት ነው።

ነገር ግን ሰባት ግዛቶች ይህ ነገር አይመለከታቸውም። ለዚህ ነው ‘ወላዋይ’ የሚባሉት።

ፔንሲልቬኒያ አሜሪካን ትመስላለች። የመሬት አቀማመጧ፣ ምጣኔ ሀብቷ እና የፖለቲካ ሁኔታዋ ትንሿ አሜሪካ አስብሏታል።

ይህች ግዛት በቀደመው ጊዜ የፋብሪካዎች መገኛ ነበረች። ለዚህ ደግሞ ምክንያቷ የነዳጅ ማከመቻ መሆኗ ነው። ግብርና ሁለተኛው ትልቁ ኢንዱስትሪዋ ነው።

አብዛኞቹ ነዋሪዎች ነጮች ናቸው። ቁጥሩ እያደገ ያለ ስደተኛም መገኛው ፔንሲልቬኒያ ናት። ለምሳሌ አለንታውን የተባለችው መንደር በርካታ የስፔን ቋንቋ ተናጋሪዎች ይኖራሉ። ከፔንሲልቬኒያ ሕዝብ 12 በመቶው ጥቁር ነው።

ከግዛቲቱ ከተሞች መካከል ፊላደልፊያ እና ፒትስበርግ ገዘፍ ያሉ ናቸው። እኒህ ከተሞች ድምፃቸውን የሚሰጡት ለዲሞክራቶች ነው። ገጠራማው ክፍል ደግሞ ድምፁን የሚሰጠው ለሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩዎች ነው።

ከከተማ ወጣ ብለው የሚኖሩ ሰዎች አሊያም አነስ ያሉ ከተሞች በቀደመው ጊዜ ወግ አጥባቂ ነበሩ። በሌላ ቋንቋ ምርጫቸው ሪፐብሊካን ነበር። ነገር ግን አሁን አሁን ግራ ዘመም እየሆኑ መጥተዋል።

በ2020 የአሜሪካ ምርጫ በፔንሲልቬኒያ ግዛት ጆ ባይደን ተቀናቃኛቸው ዶናልድ ትራምፕን የረቱት በ80 ሺህ ድምፅ ልዩነት ነው። ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ በ2016 ሂላሪ ክሊንተንን ያሸነፉት በ40 ሺህ ድምፅ።

ባለፉት 40 ዓመታት የአሜሪካ ምርጫ ታሪክ በፔንሲልቬኒያ ግዛት በሰፊ የድምፅ ልዩነት የረቱት ባራክ ኦባማ ብቻ ናቸው።

የቅድመ ምርጫ ትንበያዎች እንደሚጠቁሙት በዚህ ቁልፍ ግዛት ካማላ ሃሪስ እና ዶናልድ ትራምፕ አንገት ለአንገር ተናንቀዋል።

538 እና ኤቢሲ ኒውስ ባወጡት መረጃ መሠረት ካማላ ሃሪስ ከአንድ በመቶ ባነሰ ድምፅ ትራምፕን ይመራሉ።

መግለጫ

ሃሪስ እና ትራምፕ በኪሳቸው ያላቸውን እያሟጠጡ የፔንሲልቬኒያን ቀልብ ለመሳብ የምርጫ ዘመቻ እያደረጉ ነው። በተለይ ደግሞ ብዙ ወጭ እያወጡ ያሉት በቴሌቪዥን ለሚተላለፍ ማስታወቂያ ነው። ሁለቱም ዕጩዎች ፔንሲልቬኒያን ሳይጎበኙ አያድሩም።

ሃሪስ ምክትላቸው ሆነው የሚወዳደሩት ቲም ዋልዝን ለሕዝብ ያስተዋወቁት ፊላዴልፊያ ላይ ባደረጉት የምርጫ ቅስቀሳቸው ነው። የምርጫ ክርክር የተደረገውም በዚህች ግዛት ነው። ሃሪስ ከሁለት ሳምንት በፊት የምጣኔ ሀብት ዕቅዳቸውን ይፋ ያደረጉትም በዚህች ግዛት ነው።

ባለፈው ቅዳሜ ትራምፕ ወደ ፔንሲልቬኒያ አቅንተው በበትለር ከተማ ቅስቀሳ አድርገዋል። የቀድሞው ፕሬዝደንት ከጥቂት ወራት በፊት በበትለር ቅስቀሳ እያደረጉ ሳለ የግድያ ሙከራ እንደተደረገባቸው አይዘነጋም።

ሁለቱ ዕጩዎች መገኘት ባይችሉ እንኳ የፓርቲያቸውን ሰዎች ይልካሉ። ግዛቷ በጣም ትልቅ ስለሆነች በየመንደሩ እየዞሩ የምርጫ ቅስቀሳ የሚሠሩ ካድሬዎች ሞልተዋል።

የወቅቱ የፔንሲልቬኒያ ግዛት አስተዳዳሪ ዲሞክራቱ ጆሽ ሻፒሮ ናቸው። ይህ ደግሞ ለዲሞክራቶች ትልቅ ድጋፍ ነው። የሰላ ንግግር በማሰማት የሚታወቁት ሻፒሮ የካማላ ምክትል ይሆናሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

ካማላ በሁለቱ ከተሞች ማለትም ፊላደልፊያ እና ፒትስበርግ በርካታ ድምፅ ካገኙ ትራምፕን ድል ሊነሷቸው ይችላሉ።

የትራምፕ ዕቅድ ደግሞ በዚህች ግዛት የሚኖሩ ድምፃቸውን ለሪፐብሊካን ፓርቲ የሚሰጡ አሜሪካውያንን ቀልብ መግዛት ነው። የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ‘ውጡና ምረጡ’ የሚል መፈክር ይዟል። እያንዳንዷ ድምፅ ዋጋ እንዳላት በማሰብ ሳይሆን አይቀርም።

በዚህች ግዛት ድምፃቸውን ለመስጠት የተመዘገቡ ዲሞክራቶች ቁጥር ከሪፐብሊካኑ ይበልጣል። ነገር ግን ልዩነቱ ጠባብ ነው።

ፔንሲልቬኒያ ድምጿን ለማን ትሰጥ ይሆን? ምላሹን የምንሰማበት ቀን ተቃርቧል።