እስራኤል ዩኔስኮ ዕውቅና በሰጣት በሊባኖስ ታሪካዊቷ ባልቤክ ከተማ የአየር ጥቃት ፈጸመች

የእስራኤል የአየር ጥቃት በሊባኖስ

የፎቶው ባለመብት, AFP

እስራኤል በታሪካዊቷ እና በዩኔስኮ የተመዘገቡ ጥንታዊ ቅርሶች በሚገኙባት የሊባኖስ ባልቤክ ከተማ ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት በርካታ ሰዎች በጥቃቱ ሲገደሉ በርካቶች ደግሞ ከተማቸውን ለቀው ወጥተዋል።

የሊባኖስ ጤና ሚንስቴር እንዳስታወቀው በአገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል በምትገኘው ባልቤክ ከተማ ላይ በተፈጸመው የአየር ድብደባ ሕጻናት፣ ሴቶች እና አዛውንቶችን ጨምሮ 19 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።

ጥቃቱ የተፈጸመው እስራኤል ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ካስጠነቀቀች ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ነው። ማስጠንቀቂያውን ተከትሎም በከተማዋ እና በአቅራቢያው የሚገኙ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከቤታቸው ከከተማዋ ለመውጣት ተገደዋል።

የከተማዋ ከንቲባ ሙስጠፋ አል-ሼል እንደገለጹት በከተማዋ 20 የአየር ጥቃቶች ተፈጽመዋል።

አምስቱ በዩኔስኮ የተመዘገበ ቅርሶች በሚገኝበት መሃል ከተማ አካባቢ የተፈጸሙ ናቸው። እስራኤል በበኩሏ የሄዝቦላህን መሰረተ ልማት እና የማዘዣ ጣቢያዎች ለማፈራረስ ሲባል ጥቃቱ መፈጸሙን ገልጻለች።

የእስራኤል ጦር የሄዝቦላህ ነዳጅ ማጠራቀሚያን ኢላማ ማድረጉንም ገልጿል። የሊባኖስ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ዶሪስ በምትባለው ከተማ የነዳጅ ማጠራቀሚያዎች መመታታቸውን እና ይህንን ተከትሎም ከፍተኛ ጭስ መታየቱን ዘግበዋል።

ይህኛው ጥቃት የተፈጸመው አዲሱ የሄዝቦላህ ዋና ሥራ አስፈጻሚ “ለተኩስ አቁም አንለማመጥም፤ በአንጻሩ በጦር ዕቅዳችን እንቀጥልበታለን” ማለቱን ተከትሎ ነው።

ናይም ቃሲም የተባለው አዲሱ የሄዝቦላህ መሪ ሆኖ መመረጡ በተነገረ ማግሥት ከአንድ ወር በፊት ቤይሩት ውስጥ የተገደሉትን የቀድሞ የሄዝቦላህ መሪ ሃሰን ናስረላህን አጀንዳ እንደሚከተል አስታውቋል።

ቃሲም መልዕክቱን ያስተላለፈው ያልታወቀ ስፍራ ሆኖ ነው። አንዳንዶች የሄዝቦላህ ሁነኛ ወዳጅ ወደሆነችው ኢራን አምርቷል ይሉታል።

የእስራኤል ጥቃት በሊባኖስ

የፎቶው ባለመብት, AFP

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ለሳምንታት ከቀጠለው የደቡብ ሊባኖስ እና የቤይሩት ደቡባዊ ክፍል የአየር ጥቃት በኋላ የእስራኤል ጦር ጥቃቱን ወደ ምስራቃዊ ሊባኖስም አስፋፍቷል። ይህ ቀጠና በተመሳሳይ የሄዝቦላህ ታጣቂ ከፍተኛ እንቅስቃሴ የሚደረግበት እና በርካታ ደጋፊዎችን ያፈራበት ነው።

ባልቤክ በሦሪያ ድንበር አቅራቢያ የምትገኝ በቤካ ሸለቆ ውስጥ ከፍተኛ የሕዝብ አሰፋፈር ያላት ከተማ ናት።

ሄዝቦላህ በዚችው ከተማ አንዳንድ መሰረተ ልማቶቹን ያዘጋጀ ሲሆን ቀላል የማይባሉ ታጣቂዎቹንም በከተማዋ ይመለምላል።

አካባቢው ከወዳጆቹ ኢራቅ፣ ሦሪያ እና ኢራን ጋር ለመገናኘትም ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አለው። ይህንን ግንዛቤ በማስገባት ይመስላል የእስራኤል ጦር ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት ሁሉንም የባልቤክ እና የአቅራቢያ ከተሞች ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ያስጠነቀቀው።

አንድ የዓይን እማኝ እንደገለጹት የእስራኤል ጦር ማስጠንቀቂያን ተከትሎ በከተማዋ ከፍተኛ ትርምስ ተፈጥሮ ነበር።

ነዋሪዎች ቤታቸውን፣ ሱቆቻቸውን እና ሌሎች የንግድ ተቋሞቻቸውን ዘግተው ጎዳናዎችን አጥለቅልቀዋቸው እንደነበር ተናግረዋል። ከተማዋን ለቀው ከወጡት ነዋሪዎች መካከል ከሌላ አካባቢ በጦርነቱ ተፈናቅለው የመጡ ሰዎችም ይገኙበታል።

በማኅበራዊ ሚዲያ የተጋሩ ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት የከተማዋ ዋና ጎዳና በከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ሲታመስ ይስተዋላል።

የከተማዋ ከንቲባ ሙስጠፋ አል -ሼል እንደገለጹት ማስጠንቀቂያው በተሰጠ በሁለት ሰዓታት ውስጥ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች ከተማዋን ለቀው ወጥተዋል። አንዳንዶች በራሳቸው ምክንያት በከተማዋ ለመቆየት የወሰኑ መኖራቸውንም ከንቲባው ገልጸዋል።

ከንቲባው እንደገለጹት የእስራኤል የመጀመሪያው ጥቃት በከተማዋ ጫፍ ላይ የሚገኙ መኖሪያ ቤቶችን እና ሕንጻዎችን ደብድቧል። “እስራኤል ምን ዒላማ እንዳደረገች ግልጽ አይደለም” ያሉት ከንቲባው፣ “በከተማዋ የመሣሪያ ክምችት እንደሌለ ግን በግልጽ መናገር እችላለሁ” ብለዋል።

በጥቃቱ በሁለት ሥፍራዎች ብቻ 19 ሰዎች መገደላቸውን የሊባኖስ ጤና ሚንስቴር አስታውቋል።

ጤና ሚንስቴሩ በተመሳሳይ ሶህሞር በምትባል ከተማም በእስራኤል የአየር ጥቃት 11 ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል።

እስራኤል በበኩሏ ጥቃቱ ሂዝቦላህ ከኢራን የሚያገኛቸውን መሣሪያዎች የሚያከማችበትን የመሣሪያ ግምጃ ቤትና የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዲፖዎችን ዒላማ ያደረገ ነው ብላለች።

የእስራኤል የአየር ጥቃት በሊባኖስ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ሄዝቦላህ ነዋሪዎችን እና የህዝብ መሰረተ ልማቶችን እንደ ምሽግ እየተጠቀመ መሆኑንም እስራኤል አክላለች። በአንጻሩ ሄዝቦላህ ይህንን ክስ አይቀበለውም።

የከተማዋ ከንቲባ ሼል የአየር ጥቃቱ በከተማዋ ሰፊ ውድመት ቢያስከትልም በዩኔስኮ በተመዘገበው ቅርስ ላይ ግን ጉዳት አለመድረሱን ገልጿል።

የእስራኤልን የአየር ድብደባ ተከትሎ በቅርስነት የተመዘገቡ ታሪካዊ ቅርሶች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ዩኔስኮ አስጠንቅቋል።

“ሁለቱም ተፋላሚዎች የእነዚህን ቅርሶች ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት አለባቸው። ቅርሶቹ የማንም ሳይሆኑ የሁሉም የሰው ልጅ ቅርሶች ናቸው” ብሏል በኤክስ ገጹ ባጋራው መረጃ።

በሳምንቱ መጀመሪያ በባልቤክ ከተማ በሚገኘው ቅርስ አቅራቢያ እስራኤል በፈጸመችው የአየር ጥቃት በርካታ ግዙፍ ሕንጻዎች ተደረማምሰዋል። ከ60 በላይ ሰዎችም ተገድለዋል።

የሊባኖስ ጠቅላይ ሚንስትር ናጆብ ሚካቲ በእስራኤል እና ሄዝቦላህ መካከል በቅርቡ የተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚደረግ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ሁለት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት በእስራኤል እና ሄዝቦላህ መካከል የ60 ቀን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማስፈጸም የአሜሪካ አደራዳሪዎች እየሠሩ ይገኛሉ።

እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ ላይ እየፈጸመችው የሚገኘው ጥቃት በሰሜን እስራኤል ላይ የሚደርስን ማንኛውንም ጥቃት ለመመከትና የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ እንደሆነ ገልጻለች።

እስራኤል በባልቤክ ከተማ ላይ የአየር ጥቃት ስትፈጽም ሄዝቦላህ በበኩሉ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን ተኩሷል። የእስራኤል ጦር እንደገለጸው ሄዝቦላህ 60 ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ቢያስወነጭፍም አንዳቸውም ጉዳት አላደረሱም ብሏል።

በሄዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል ይፋዊ ጦርነት መካሄድ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ሊባኖስ ውስጥ ብቻ ከ2 ሺህ 8 መቶ ሰዎች በላይ ተገድለዋል። እንደሊባኖስ ባለስልጣናት መረጃ ከ1 ሚሊዮን 2 መቶ ሺህ በላይ ነዋሪዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

በእስራኤል በኩል ደግሞ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል እና በጎላን ተራሮች በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ60 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።