አስከፊ የጎርፍ አደጋ በተከሰተባት ስፔን የሟቾች ቁጥር ወደ 95 ከፍ አለ

የፎቶው ባለመብት, AP
ለአስርት ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ አስከፊ የጎርፍ አደጋ በተከሰተባት ስፔን የሟቾች ቁጥር 95 ደረሰ።
በምስራቃዊዋ ቫሌንሽያ ግዛት እና አካባቢው የጣለው ከፍተኛ ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ መጥለቅለቅ ምክንያት ቁጥራቸው የማይታወቅ ሰዎች ደብዛቸው ጠፍቷል።
ጎርፉ ድልድዮችን እና ህንጻዎችን እየደረማመሰ ጠራርጎ የወሰዳቸው ሲሆን በርካቶች ጣራ ላይ ወይም ዛፎች ላይ ተንጠልጥለው ህይወታቸውን ለማትረፍ ሲሞክሩ ታይተዋል።
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ የሶስት ቀናት ብሔራዊ ሃዘን ያወጁ ሲሆን ባለው አስከፊ የአየር ሁኔታ ምክንያት አንዳንድ የነፍስ አድን ጥረቶች መስተጓጎላቸው ተነግሯል።
“በርካታ ደብዛቸው የጠፉ ሰዎች በመኖራቸው የሟቾች ቁጥር ሊያሻቅብ ይችላል” ሲል የአገሪቱ መንግሥት አስታውቋል።
ጎርፉ በከፋ የመታት ቫለንሺያ ግዛት 92 ሞቶች የተመዘገባት ሲሆን ካስቲላ ላ ማንቻ በምትባለው ግዛት ደግሞ ሁለት ሰዎች ህይወታቸው ማለፋቸው ተዘግቧል።
ጎርፉ በሃገሪቱ በአውሮፓውያኑ 1973 ከተከሰተው እና የ150 ሰዎችን ህይወት ከቀጠፈው አደጋ በኋላ የከፋው እንደሆነ ተገልጿል።
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ረቡዕ ዕለት ባደረጉት ብሄራዊ ንግግራቸው ዜጎች ሁኔታዎችን ነቅተው እንዲጠብቁ አሳስበው ለተጎጂዎች “መላው ስፔን ከእናንተ ጋር እያለቀሰ ነው። ብቻችሁን አንተዋችሁም” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በቫሌንሲያ አቅራቢያ በጎርፉ ከተጎዱት የመጀመሪያ ከተሞች አንዷ በሆነችው ቺቫ በዚህ ሳምንት ማክሰኞ በስምንት ሰዓታት ውስጥ የአንድ ዓመት የዝናብ መጠን መመዝገቡን የአገሪቱ ብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ፣ አሜት አስታውቋል።
የሰዎችን ህይወት ለመታደግ ከድንገተኛ ሰራተኞች በተጨማሪ የስፔን ጦር ተሰማርቷል።
በርካቶችን ከመኖሪያ ቤቶቻቸው ሰገነቶች እንዲሁም ከመኪና ጣሪያዎቻቸውን ላይ ለማውረድ ሲሞክሩም ታይተዋል። ድንገተኛው የጎርፍ አደጋ ጎዳናዎችን እና መንገዶችን ወደ ወንዞች የቀየረ ሲሆን ሁኔታው ለበርካታ አሽከርካሪዎችም ያልጠበቁት ዱብ ዕዳ ሆኖባቸዋል።
በወቅቱ መንገድ ላይ የነበረው የ21 ዓመቱ ጊለርሞ ሰርናኖ ፔሬዝ ውሃው በከፍተኛ ፍጥነት እንደ ማዕበል ሲያጥለቀልቃቸው እሱ እና ወላጆቹ መኪናቸውን ጥለው ህይወታቸውን ለማትረፍ ወደ አንድ ድልድይ እንዲወጡ መገደዳቸውን ተናግሯል።












