ለዓመት የሚያገለግሉ የባህላዊ መድኃኒት ዕጽዋትን በአንድ ቀን የሚሰበስበው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ

የፎቶው ባለመብት, Hilena Tafesse
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኘው የም ዞን በየዓመቱ ጥቅምት 17 “ልዩ ቀን” ነው።
የም ዞን በአዲሱ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዞን ሆኖ ከመደራጀቱ በፊት ልዩ ወረዳ ነበር። በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክፍል የሚገኘው ዞኑ ዋና ከተማው ሳጆ ይባላል።
እንደ አብዛኞቹ አጎራባች ሕዝቦች የየም ማኅበረሰብ ለበርካታ ዘመናት ከዕጽዋቶች መድኃኒትን በመቀመም ልምድ ያካበተ እንደሆነ ይነገርለታል።
ሕዝቡ በዓመት አንድ ቀን በነቂስ ወጥቶ ለመድኃኒትነት የሚውሉ ዕጽዋትን ለመልቀም ወደ ተራራ ይወጣል፤ ወደ ቦር ተራራ (በአካባቢው አጠራት ቦሪ ተራራ)።
ተራራው ከባሕር ጠለል በላይ 2939 ሜትር ከፍታ አለው። በየዓመቱ ጥቅምት 17 ጆንያ፣ ኬሻ እና ከረጢት ያነገቡ ሰዎች ለሰው እና ለእንስሳት የሚሆኑ መድኃኒቶችን ከዕጽዋቶች (ቅጠል፣ ሥራሥር፣ ቅርፊት እና ግንድ) ለመልቀም ወደ ተራራው ያቀናሉ።
በተራራው ከሚገኙ ዕጽዋቶች ተሰብስቦ የሚቀመመው ባህላዊ መድኃኒት “ሳሞ ኤታ” ወይም “የከርሞ መድኃኒት” ይባላል።
በዚህ ተራራራ መርዛማ ናቸው ተብለው ከተለዩ አራት ዕጽዋቶች ውጪ ሁሉም ዕጽዋት ዋጋ አላቸው።
መድኃኒቱ በተራራው ከሚገኙ 110 የሚሆኑ ዕጽዋቶች ተለቅሞ የሚዘጋጅ እንደሆነ የዞኑ ባህል እና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ሞጋ ቢቢሲ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Hilena Tafesse
መድኃኒቱ ለአንድ ዓመት የሚያገለግል እና ጥቅምት 17 ብቻ የሚለቀም ሲሆን፤ ከአንድ ዓመት በኋላ የመጠቀሚያ ጊዜው የሚያበቃ እንደሆነ ይነገራል።
አቶ ጌታቸው ኃ/ማሪያም በየም ዞን የባህላዊ ህክምና ባለሞያ ናቸው። ከልጅነታቸው ጀምሮ የተሰማሩበት ሙያ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ጌታቸው፤ ባህላዊ መድኃኒት ለየም ሕዝቦች ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ ዛሬ ላይ የደረሰ ነው ይላሉ።
እሳቸው 15ተኛ ትውልድ የባህላዊ መድኃኒት ቀማሚ እንደሆኑም ይናገራሉ።
“አባቴ ሲናገሩ እንደሰማሁት ከአጼዎቹ በፊት ቀድሞ የነበረ የባህል መድኃኒት ቅመማ ነው ያሉኝ። ‘እኔ 14ተኛ ትውልድ ነኝ፤ አንተ ደግሞ 15ተኛ ነህ’ ብለው ነው የነገሩኝ። ከትውልድ ትውልድ እተሸጋገረ የመጣ ነው። እኔ አንተን ተክቻለሁ ነው ያሉኝ” በማለት ሳሞ ኤታ ለዘመናት የቆየ ሥርዓት መሆኑን ያብራራሉ።
የመድኃኒት ዝግጅቱ መቼ እንደተጀመረ በውል ባይታወቅም፤ “የየም ሕዝብ በምዕራብ ኢትዮጵያ ሰፍሮ መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ. . .” ሳይሆን እንደማይቀር አቶ መስፍን ይጠቁማሉ።
ሕዝቡ በሽታዎችን ለመቋቋም ከተፈጥሮ ጋር በጀመረው ትግል ወደ መድኃኒት ግኝቱ እንዳመራው የሚያነሱ ሲሆን፤ አካባቢውም “የፈውስ ምድር” ተብሎ እንደሚጠራ ይገልጻሉ።
አቶ መስፍን ለመድኃኒትነት የሚውሉ እጸዋትን ለአብነት ሲያነሱ “ለምሳሌ ጣሴታ [የዕጽዋት ሥር] ቁርጠት የታመመ ሰው ስሩን ካኘከ እና ፈሳሹን ከዋጠ ወዲያው ነው ቁርጠቱ የሚቆመው” ይላሉ።
ጥቅምት 17 በቦር ተራራ ላይ የሚበቅሉ እጸዋቶች እና አበቦች ሙሉ የሚሆኑበት፣ ጥንካሬያቸውን የሚያገኙበት “አጋማሽ ወር” በመሆኑ እና ከዚህ ወቅት ካለፉ ደግሞ የሚደርቁ በመሆናቸው ዕለቱ እንደተመረጠ ያነሳሉ።
በዕለቱ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ልጅ አዋቂ ሳይባል እንዲሁም ሳይጠራራ ወደ ቦር ተራራ ይተማል።
“እህል አይቀመስም። ባዶ አፍ ነው የሚኬደው። በባዶ ሆድ ሄደን እዚያው መድኃኒቱን ሰብስበን ከጨረስን ከ6 እና ከ7 ሰዓት በኋላ እዚያው ቁርስ በልተን በእግር እና በአህያ ቁልቁለቱን ወርደን 10 ወይም 11 ሰዓት አካባቢ ነው ወደ ቤታችን የምንመለሰው” ይላሉ።
የባህል መድኃኒት አዋቂ የሆኑትን አቶ ጌታቸውን ቢቢሲ በስልክ ሲያገኛቸው ባለፈው እሁድ ጥቅምት 17 የለቀሙትን ቅጠላ ቅጠል “በዓይነት በዓይነቱ” እየመረጡ ነበር።
“ከላይ [ከተራራው] ስንሰበስበው በአንድ ላይ ነው የምንሰበስበው። ሰብስበን አምጥተን በዓይነት በዓይነታቸው እንለያላን” የሚሉት አቶ ጌታቸው፤ የመለየቱ ሥራ ብቻ አራት ቀን እንደሚፈጅባቸው ይናገራሉ።
ከዚያም እንደ በሽታው ዓይነት እየመረጡ እና እየቀላቀሉ እንደሚያዘጋጁ ጠቁመው፤ መድኃኒቱን በማድረቅ እና በመውቀጥ የመቀመም ሥራቸውን እስከ ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም. ድረስ እንደሚያከናውኑ ይገልጻሉ።
መድኃኒቶቹ በዱቄት እና በፈሳሽ መልክ ሚዘጋጁ ሲሆን እንዳይበላሹ በሸክላ እና በቅል ውስጥ ተደርገው ይቀመጣሉ።
የባህል መድኃኒቶች አዋቂው አቶ ጌታቸው ጨምረውም “ካንሰርን ጨምሮ ለ258 ዓይነት በሽታዎች መድኃኒቶችን እንደሚቀምሙ” ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ዘመናዊ መድኃኒት ተስፋፍቷል በሚባልበት ወቅት ባህላዊ መድኃኒት ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነ አቶ ጌታቸው ያነሳሉ።
ለእርሳቸው ባህላዊ መድኃኒት በዘመናዊ መድኃኒት እና ህክምና ፈውስ ላልተገኘላቸውን በሽታዎችም ፍቱን መፍትሄ ነው። ለዚህም አስረጂ ምሳሌ ከማንሳት ባለፈ ደንበኞቻቸው በሰጧቸው ግብረ መልስ ፈዋሽነቱ ከፍተኛ ነው ይላሉ።
ባህላዊ መድኃኒቱ “በቀላሉ” እና “ነጻ” በሚባል ደረጃ መገኘቱ፣ በዚህ ዘመንም ቢሆን ተፈላጊ ያደርገዋል የሚሉት አቶ መስፍን፤ “የጎንዮሽ ጉዳት” የሌለበት መሆኑንም በማንሳት ሕዝቡ በሰፊው ይጠቀመዋል ይላሉ።
በዘንድሮው የየም ባህላዊ የመድኃኒት ለቀማ ሥነ ሥርዓት ላይ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሆኑት ዶ/ር ደረጄ ዱጉማን ጨምሮ ከፍተኛ መንግሥት ሹማምንት ተገኝተዋል።
የዞኑ አስተዳደር ሳሞ ኤታን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ከሦስት ዓመት በፊት ጥያቄ አቅርቧል።
“አካባቢው ጥበቃ ተደርጎለት ተገቢውን አገልግሎት ለዚህ አካባቢ ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም፤ ለዓለምም ተደራሽ እንዲሆን እየተሠራን ነው” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, YEM ZONE COMM.












