ሁለት ቱሪስቶች በአልጄሪያ የባሕር ዳርቻ ፖሊስ ተገደሉ

የባህር ላይ ሞተር ሳይክል

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

የአልጄሪያ የባሕር ዳርቻ ጠባቂ ፖሊሶች ሁለት ቱሪስቶችን ተኩሰው ገደሉ።

ቱሪስቶቹ ባሕር ላይ በጀት ስኪ እየተጓዙ ሳለ ከጠባቂዎቹ በተተኮሰ ጥይት ተገድለዋል።

ለጉብኝት ወደ አልጄሪያ የሄዱት ቱሪስቶች የፈንሳይ እና ሞሮኮ ዜግነት ያላቸው ናቸው።

በሞሮኮ ባሕር ዳርቻ ከሚገኝ መዝናኛ ሳይዳ ከተባለ ስፍራ ተነስተው በጀት ስኪ (በሞተር ኃይል የሚሄደው የባሕር ላይ ሞተር) እየተጓዙ ነበር።

አብሯቸው የነበረ ሌላ ሦስተኛ ጎብኚ በአልጄሪያ የባሕር ጠባቂ ፖሊሶቹ ተይዟል።

ፖሊሶቹ ተኩስ መክፈታቸው በሞሮኮ ቁጣ ቀስቅሷል። የተኩሱን ቪድዮ የለቀቀው ዓሣ አስጋሪ ነው።

የቱሪስቶቹ አስክሬን ባሕር ላይ ሲንሳፈፍ ይታያል።

በአልጄሪያ እና ሞሮኮ መካከል ያለው ድንበር የተዘጋው እአአ በ1994 ሲሆን አልጄሪያ ሞሮኮ ትንኮሳ ፈጽማለች ስትል ብትከስም ሞሮኮ ግን አስተባብላለች።

አራት ሆነው እየተጓዙ ከነበሩት ጎብኚዎች መካከል ወደ ሞሮኮ መመለስ የቻለው መሐመድ ኪሲ ሲሆን፣ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደገለጸው እሱና ጓደኞቹ ባሕር ላይ የሚጓዙበት አቅጣጫ ጠፍቷቸው ነዳጅም አልቆባቸው ነበር።

“የት እንዳለን ጠፍቶን ነበር። አልጄሪያ እስክንደርስ ድረስ ጉዞ ቀጠልን” ብሏል። ከሞቱን መካከል አንደኛው የሆነው ቢላል ወንድሙ ነው።

“አልጄሪያ እንደገባን ያወቅነው የአልጄሪያ ጀልባ ወደኛ እየመጣ ስናይ ነው። ከዚያም ከጀልባው ላይ ወደእኛ ይተኩስ ጀመር” ሲል ገልጿል።

“እኔስ ፈጣሪ ይመስገን ተረፍኩ ወንድሜና ጓደኛዬን ግን አጥቻለሁ” ሲልም መሐመድ አክሏል።

ሌላኛው ጓደኛውን ፖሊሶቹ እንዳሰሩትም ተናግሯል።

“ወንድሜ በአምስት ጥይት ነው የተመታው። ጓደኛዬ ደግሞ በአንድ ጥይት።”

የሞሮኮ ፖሊሶች አግኝተውት ወደ ሳይዳ የባሕር ዳርቻ እንደወሰዱትም ጠቅሷል።

ከሞቱት አንደኛው አብደላሊ ሜርሆር ይባላል። የታሰረው ደግሞ ስማሊ ስናቤ ይባላል።

የሞሮኮ መንግሥት ቃል አቀባይ በሕግ የተያዘ ጉዳይ ነው ብሎ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።

በአልጄሪያ በኩልም የተባለ ነገር የለም።

ሁለቱ አገራት በምዕራባዊ ሰሃራ ምክንያት ለዓመታት ፍጥጫ ውስጥ ቆይተዋል። ወደ 2,000 ኪሎ ሜትር ድንበር ይጋራሉ። ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ከወጡ በኋላ በድንበር ጉዳይ መጋጨት ቀጥለዋል።

በሞሮኮ፣ ማራኬሽ ሆቴል ላይ በኢስላማዊ ታጣቂዎች ከደረሰ ጥቃት በኋላ ድንበሩ በደኅንነት ስጋት በ1994 ተዘግቷል።