ኢራናዊው ክብደት አንሺ ከእስራኤላዊ ተወዳዳሪ ጋር ፎቶ በመነሳቱ ዕግድ ተጣለበት

ኢራናዊው ክብደት አንሺ ከእስራኤላዊው ተወዳዳሪ ጋር

የፎቶው ባለመብት, IMWA

ፖላንድ በተካሄደ የዓለም ማስተርስ ሻምፒዮና ላይ ከእስራኤላዊ ክብደት የማንሳት ተወዳዳሪ ጋር እጅ ሲጨባበጥ እና ሲነጋገር ፎቶ የተነሳው ኢራናዊ ክብደት አንሺ በአገሩ ባለሥልጣናት እግድ ተጣለበት።

የኢራን ክብደት የማንሳት ፌዴሬሽን በክብደት አንሺው ሙስጣፋ ራጃይ ላይ ከዚህ በኋላ በማንኛውም ውድድር እንዳይሳተፍም ነው የእድሜ ልክ እግድ ያስተላለፈበት።

በውድድሩ ላይ ብር ለአገሩ ማምጣት የቻለው ሙስጠፋ ካሸነፈም በኋላ ከእስራኤላዊው የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ተወዳዳሪ ጋር መድረክ ላይ ቆሞም ታይቷል።

ይህንንም ተከትሎ ፌዴሬሽኑ በአገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ሁሉም የስፖርት ማዘውተሪያዎች ዝር እንዳይልም ነው ክልከላ ያስተላለፈበት።

ኢራናዊ አትሌቶች በማንኛውም ስፖርታዊ ውድድሮች ከእስራኤላውያን ጋር እንዳይወዳደሩም በአገሪቱ ባለሥልጣናት ተከልክለዋል።

በዚህም ምክንያት የኢራን ስፖርተኞች ከውድድሮች ራሳቸውን በማግለል፣ እንደተጎዱ በማስመሰል እና ሌሎችንም ዘዴዎችንም በመጠቀም ከእስራኤላውያን ተፎካካሪዎች ጋር አይሳተፉም።

የ40 ዓመቱ ሙስጠፋ ቅዳሜ ዕለት በፖላንዷ ዌሊዝካ ግዛት ከነበረው ውድድር በኋላም ከእስራኤላዊው አትሌት ማክሲም ስቪርስኪ አጠገብ በቆመበት ወቅት የአገሩን ሰንደቅ ዓላማ ለብሶ ነው።

ሙስጠፋ ከዚህ ቀደም ኢራንን ወክሎ በጎሮጎሳውያኑ 2015 በታይላንድ በተካሄደ የእስያ ክብደት የማንሳት ሻምፒዮና ላይ ተሳትፏል።

ክብደት አንሺው የቀድሞ የኢራን ብሔራዊ ቡድንም አባል ነው።

ኢርና የተሰኘው የኢራን መንግሥት የዜና ወኪል ክብደት አንሺው “የእስላሚክ ሪፐብሊክን ቀይ መስመሮችን ተላልፏል” ሲል ዘግቧል።

በዚህ ክስተት ምክንያት ፌዴሬሽኑ ከሙስጠፋ በተጨማሪም የቡድኑ መሪ ሃሚድ ሳሌሂኒያን ከሥራ አሰናብቷል።

የኢራን ልዕለ መሪ አያቶላህ አሊ ኾሜይኒ ኢራናውያን አትሌቶች ሜዳሊያ ለማግኘት ሲሉ ከእስራኤላውያን ተፎካካሪዎች ጋር መጨባባጥ እንደሌለባቸው ከሁለት ዓመት በፊት አሳስበው ነበር።

በዕገዳው ምክንያት አንዳንድ አትሌቶችም አገራቸውን ጥለው ለግዞት ተዳርገዋል።

ከነዚህም መካከል የቼዝ ጨዋታ ተወዳዳሪው አሊሬዛ ፊሮጃ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከእስራኤላዊ ጋር እንዳይወዳደር በሚል እግድ በመጣሉም ምክንያት አገሩን ለቆ ለስደት ተዳርጓል።