ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ እና አውስትራሊያ ለፍልስጤም የአገርነት ዕውቅና ሰጡ

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር

ዩናይትድ ኪንግደም፣ካናዳ እና አውስትራሊያ በይፋ ለፍልስጤም የአገርነት እውቅናን መስጠታቸውን አስታወቁ።

ለሁለት ዓመታት እስራኤል በጋዛ ላይ እያካሄደችው ያለው ወታደራዊ ዘመቻን ተከትሎ በርካታ አገራት ለፍልስጤም የአገርነት ዕውቅናን እየሰጡ ነው።

እስራኤል ይህ በተለይ በምዕራባውያን አገራት እየተወሰደ ያለው እርምጃ ሐማስ ለፈጸመባት ጥቃት እንደ ሽልማት ነው በማለት በጽኑ እያወገዘችው ነው።

ከዩናይትድ ኪንግደምን ቀደም ብላ ውሳኔዋን ያሳወቀቸው ከዩኬ ጋር ጥብቅ ትስስር ያላት ካናዳ ስትሆን አውስትራሊያም ዕውቅናውን በመስጠት ተከትላለች።

ምዕራባውያኑ በተለይ አሜሪካ የምትገኝበት የቡድን ሰባት የበለጸጉት አገራት አባላት ለፍልስጤም ዕውቅናውን ለመስጠት የተለያዩ ምክንያቶች እያቀረቡ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቆይተዋል።

ከዚህ ስብስብ ውስጥ ለፍልስጤም ዕውቅና በመስጠት የመጀመሪያዋ አገር ካናዳ ሆናለች። በመከተል ደግሞ አስትራሊያ ውሳኔዋን ስታሳውቅ፣ ዕውቅናውን ለመስጠት እንደተዘጋጀች ስትገልጽ የነበረችው ዩናይትድ ኪንግደምም ውሳኔዋን በጠቅላይ ሚኒስትሯ ይፋ አድርጋለች።

አውስትራሊያ ይህ የእውቅና የመስጠት ውሳኔዋ "ለእስራኤል እና ፍልስጤም የሁለት አገር መመሥረት የዓለም አቀፍ መፍትሄ አካል ነው" ብላለች።

የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር በበኩላቸው የአገራቸው ውሳኔ ያስፈለገው "የሁለት አገራት መመሥረት እና የሰላም ተስፋ እንዲያንሰራራ" ለማድረግ መሆኑን አመልክተዋል።

ይህ ውሳኔ ሐማስ ምንም የወደፊት ተስፋ የሌለው ቡድን በመሆኑ "ለሐማስ የተበረከተ ሽልማት አይደለም" ሲሉ አጥብቀው ተናግረዋል።

ስታርመር ጨምረውም ጋዛ ውስጥ በሐማስ ጠይዘው ያሉ ሁሉም እስራኤላውያን ታጋቾች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ እና እስራኤል በጋዛ ድንበር ላይ የጣለችውን ክልከላ በማንሳት ተጨማሪ እርዳታ እንዲገባ እንድትፈቅድ ጥሪ አቅርበዋል።

ካናዳን ተከትላ ለፍልስጤም የሉዓላዊ አገርነት ዕውቅናን የሰጠችው የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ ባስተላለፉት መልዕክት ውሳኔው "የሁለት አገራት መፍትሄ" ተግባራዊ እንዲሆን የሚደረገው ዓለም አቀፍ ጥረት አካል ነው ብለዋል።

ካናዳ እና አውስትራሊያ ከወራት በፊት በመጪዎቹ ቀናት ኒው ዮርክ ውስጥ በሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለፍልስጤም ዕውቅና እንደሚሰጡ ሲያሳውቁ መቆየታቸው ይታወሳል።