ኡስማን ደምበሌ እና አይታና ቦንማቲ የባለንደኦር አሸናፊ ሆኑ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፓሪስ ሳንት ዠርማኑ ኡስማን ደምበሌ ለመጀመሪያ ጊዜ የባለንደኦር አሸኛፊ ሆኗል። ሶስት ዋንጫዎች ያነሳው ክለቡ ደግሞ የተለያዩ ሽልማቶች አግኝቷል።
የ28 ዓመቱ ፈረንሳዊ አጥቂ ባለፈው የውድድር ዘመን በ53 ጨዋታዎች 35 ጎሎች ሲያስቆጥር 14 ኳሶች አመቻችቶ አቀብሏል።
ደምበሌ ከፒኤስጂ ጋር የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ፣ የፈረንሳይ ሊግ 1 እና የፍሬንች ካፕ ባለድል መሆን ችሏል።
በሊግ 1 በ21 ጎሎች ጥምር ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሲሆን የሊጉ እና የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ኮከብ ተብሎ ተመርጧል።
ኒው ጀርዚ በተካሄደው የዓለም ክለቦች ዋንጫ ላይም እስከፍፃሜው ድረስ መዝለቅ ችሏል።
የባርሴሎናውን ታዳጊ ላሚን ያማል በመርታት የባለንደኦር አሸናፊ የሆው ደምበሌ ፓሪስ በተካሄደው ሥነ-ሥርዓት ላይ በእንባ ተሞልቶ ንግግር ሲያደርግ ታይቷል።
"ይህ እጅግ ልዩ ነገር ነው። የምገልበት ቃላት የለኝም። ከፒኤስጂ ጋር የሆነው የሚደንቅ ነው" ብሏል። በስሜት ተሞልቶ ንግግር ሲያደርግ የነበረው ደምበሌን እናቱ መድረክ ላይ ተቀላቅላዋለች።
"ትንሽ ጨንቆኛል። ምክንያቱም ይህን ሽልማት ማግኘት ቀላል አይደለም። በዚያ ላይ ሽልማቱን ከሮናልዲንሆ እጅ መቀበል እጅግ ልዩ ነው።"
"በ2023 የተቀበሉኝን ፒኤስጂ ማመስገን እሻለሁ። የሚደንቅ ቤተሰብ ነው። ፕሬዝደንቱ ለኔ ልክ እንደ አባት ናቸው" ያለው ደምበሌ የቡድን አጋሮቹን፣ አሰልጣኙን እና የክለቡን ሠራተኞች አመስግኗል።
ምርጥ አሰልጣኝ ተብለው የተሸለሙት ሉዊስ ኤንሪኪ፤ ደምበሌን ከክንፍ መስመር ተጫዋችነት ወደ አጥቂነት በማምጣታቸው ምስጋና ተችሯቸዋል።
በሴቶች የባለንደኦር ሽልማት የስፔን እና የባርሴሎና አማካይ የሆነችው አይታና ቦንማቲ ለሶስተኛ ተከታታይ ጊዜ ሽልማቱን በማንሳት ታሪክ ፅፋለች።
የ27 ዓመቷ ቦንማቲ የአርሰናሏን የክንፍ መስመር ተጫዋች ማሪዮና ካልዴንቴን በመቅደም አንደኛ ወጥታለች።
"ለሶስተኛ ተከታታይ ጊዜ እያነሳሁት እንኳ ማመን ያቅተኛል። ይህን ሽልማት ማጋራት ሚቻል ቢሆን ምንኛ ደስ ባለኝ" ያለችው ቦንማቲ የክለብ አጋሮቿኝን አመስግናለች።
የአርሰናሉ አጥቂ ቪክተር ጊዮኬሬሽ በ2024-25 የውድድር ዘመን በርካታ ጎሎች በማስቆጠር የገርድ ሙለር ሽልማት አሸናፊ ሆኗል።
የ27 ዓቱ ስዊዲናዊ አጥቂ ለፖርቹጋሉ ስፖርቲንግ እና ለሀገሩ በ52 ጨዋታዎች 54 ጎሎች አስቆጥሯል። ጊዮኬሬሽ በክረምቱ የዝውውር መስኮት በ64 ሚሊዮን ፓውንድ አርሰናልን ተቀላቅሏል።
በሌላ በኩል የባርሴሎናው ላሚን ያማል ከ21 ዓመት በታች ለሆኑ ተጫዋቾች የሚሰጠውን ኮፓ ሽልማት ለሁለተኛ ጊዜ አግኝቷል።
ምንም እንኳ ሽልማቱ ከአውሮፓውያኑ 2018 ቢጀምርም ላሚን ያማል ሁለት ጊዜ በመሸለም የመጀመሪያው ሆኗል።
በ55 ጨዋታዎች 18 ጎሎች አስቆጥሮ 21 አመቻችቶ ያቀበለው ያማል ከባርሴሎና ጋር የላ ሊጋ እና የኮፓ ዴል ሬይ ዋንጫን አግኝቷል።
የፒኤስጂው አሰልጣኝ ሉዊስ ኤንሪኬ የዓመቱ ምርጥ ተብለው ሲሸለሙ ከፈረንሳይ ክለብ ጋር ተለያይቶ ማንቸስተር ሲቲን የተቀላቀለው ዶናሩማ ምርጥ ግብ ጠባቂ ተብሏል።












