አሜሪካ እና ኢራን የኒውክለር ስምምነት ላይ ለመድረስ መቃረባቸውን ትራምፕ ተናገሩ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር በኒውክለር ፕሮግራሞቿ ላይ በቀረቡት መደራደርያዎች ለመስማማት "መቃረቧን" ተናገሩ።

ትራምፕ በሁለቱ አገራት መካከል እሁድ ዕለት የተጠናቀቀውን ንግግር በተመለከተ ሲገልፁ "ለረዥም ጊዜ ሰላም" በሚል " በጣም ጠንከር ያለ ድርድር" መደረጉን ተናግረዋል።

ቀድም ብሎ የኢራን ጠቅላይ መሪ አማካሪ የሆኑ ግለሰብ ለኤንቢሲ ኒውስ ኢራን ማዕቀቦች የሚነሱ ከሆነ በኒውክለር ፕሮግራሞቿ ላይ ከስምምነት ለመድረስ ዝግጁ ናት ብለዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ኢራን የኒውክሌር የጦር መሣርያ ማምረት እንዳትችል ለማድረግ የምታበለጽገውን ዩራኒየም እንድትተው ትፈልጋለች።

ኢራን በየጊዜው የኒውክለር ፕሮግራሞቿ በአጠቃላይ ለሠላማዊ ተግባራት የሚውሉ መሆናቸውን ትግለጻለች።

በባሕረ ሰላጤው አገራት ጉብኝት እያደጉ የሚገኙት ዶናልድ ትራምፕ ሐሙስ ዕለት በኳታር እንደተናገሩት፣ በኢራን ኒውክለር ፕሮግራም ዙርያ የሚደረገው ድርድር ወደ ስምምነት እየተቃረበ በመሆኑ፣ በቴህራን ኒውክለር ፕሮግራሞች ላይ የሚፈጸመው ወታደራዊ ጥቃት ሊወገድ ይችላል ብለዋል።

በዶሃ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ "በኢራን ውስጥ ምንም ዓይነት የኒውክለር አቧራ አናስነሳም" ብለዋል።

"ይህንን ማድረግ ሳያስፈልገን ስምምነት ለመድረስ እየተቃረብን ያለን ይመስለኛል። ዛሬ ስለ ኢራን ያለውን ዜና አንብባችሁ ይሆናል። ባቀረብናቸው መደራደርያዎች ሳይስማሙ አልቀሩም።"

ፕሬዝዳንቱ የትኛውን አስተየየት በግልጽ እንደጠቀሱ ያሉት ነገር የለም።

ነገር ግን የኢራን የጠቅላይ መሪ አያቶላ አሊ ካሜኒ አማካሪ የሆኑት አሊ ሻምካኒ፣ ከአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ላይ ቴህራን በኒውክሌር ፕሮግራሟ ላይ የቀረቡ እገዳዎችን ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኗን ተናግረዋል።

ሻምካኒ ለኤቢሲ ኒውስ እንዳሉት ከሆነ ኢራን በከፍተኛ ደረጃ የበለፀጉ እና የተከማቹ ዩራኒየሞችን አሜሪካ የጣለችውን ማዕቀብ የምታነሳ ከሆነ ለመተው ዝግጁ ናት።

በቴህራን የኒውክለር ፕሮግራም ላይ የመጨረሻው ድርድር የተካሄደው እሁድ ዕለት ሲሆን ሁለቱም ወገኖች ዳግም ለመገናኘት ከስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።

የአሜረካ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ ውይይቱ አበረታች ነበር ሲሉ የኢራን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋህቺ ደግሞ "አስቸጋሪ ነገር ግን ጠቃሚ" እንደነበር ገልጸዋል።

ትራምፕ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2018 ኢራን ከሌሎች ኃያላን አገራት ጋር ከገባችው ስምምነት መውጣታቸው ይታወሳል።

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በሚያዝያ ወር የተጀመረው እና በኢራን የኒውክለር ፕሮግራሞች ላይ እየተካሄደ ያለው ውይይት የማይሳካ ከሆነ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ዝተው ነበር።

አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣን ለመጨረሻ ጊዜ የተካሄደው ድርድር የፈጀው ሦስት ሰዓት ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አክለውም "እየተደረጉ ያሉ ንግግሮችን ወደፊት ለመቀጠል እና ቴክኒካል ጉዳዮች ላይ እየሰሩ ለመቆየት ከስምምነት ተደርሷል። ዛሬ በሰማነው ነገር ደስተኞች ነን፤ እንዲሁም በቅርቡ የሚካሄደውን ቀጣይ ስብሰባችንን በተስፋ እንጠብቃለን" ብለዋል።