እስራኤል በጋዛ የተጠለሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ፍልስጤማውያን ለቅቀው እንዲወጡ አዘዘች

በጋዛ በወደመ ህንጻ ፊት ለፊት በፈረስ በሚጎተት ጋሪ ላይ ተጭነው የሚሄዱ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, EPA

እስራኤል፤ ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ ባልታየ መልኩ በጋዛ የሚገኙ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ፍልስጤማውያን ነዋሪዎች አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላለፈች።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት፤ አብዛኛው ክፍሉ ቀድሞውንም በፈንጂዎች የወደመውን የጋዛ ከተማ ደኅንነቱ ያልተጠበቀ ብሎ የበየነ ሲሆን፣ ከተማዋ ተጠልለው የሚገኙ ነዋሪዎችም ሊፈጸም ከታቀደው "ከፍተኛ ጥቃት" በፊት ለራሳቸውን ደኅንነት አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ ተናግሯል።

በእስራኤል ከተለዩት ህንጻዎች መካከል እስላሚክ ዩኒቨርሲቲ፣ አል ሺፋ ሆስፒታል እና ሦስት የቀድሞ ትምህርት ቤቶች ይገኙበታል።

እስራኤል፤ ሐማስ እነዚህን ህንጻዎች "ማዘዣ እና መቆጣጠሪያ" ማዕከላት አድርጎ እየተጠቀመባቸው እንደሆነ በመጥቀስ ትከስሳለች። የአካባቢው ባለሥልጣናት እና የእርዳታ ድርጅቶች በበኩላቸው እነዚህ ስፍራዎች ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን መጠለላቸውን ተናግረዋል።

ሰዎች ከእነዚህ ቦታዎች እንዲለቅቁ ለማድረግ ጊዜ እንደሚያስፈልግም የገለጹ ሲሆን፣ ውሳኔው ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ሰዎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል።

ይህ እርምጃ እስራኤል በጋዛ ወታደራዊ ዘመቻዋን በከፍተኛ መጠን እንደምታስፋፋ የሚያመለክት አስጊ ምልክት ነው።

የቀድሞው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሁድ ኦልሜርት በጋዛ ወታደራዊ ዘመቻን የማስፋት ሃሳብን ከተቃወሙ ጥቂት ስመ ጥር እስራኤላውያን መካከል ናቸው።

ኦልሜርት ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ፤ "አብዛኞዎቹ እስራኤላውያን እየሆነ ያለው ነገር ተቃዋሚ ናቸው። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው [የሠራዊቱ] አዛዦች ወታደራዊ ዘመቻን ማስፋፋትን ይቃወማሉ፤ ጦርነቱ አሁን እንዲያበቃም ይፈልጋሉ" ብለዋል።

በእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔትያናሁ ላይ ተደጋጋሚ እና እየጨመረ የመጣውን የሰላ ትችታቸውን የሚያቀርቡት ኦልሜርት፤ ምልከታቸው 20 ወራት የዘለቀው ጦርነት በሀገሪቱ የሞራል፣ የኢኮኖሚ እና ዓለምአቀፍ አቋም ላይ ያለውን ተጽእኖ በተመለከተ እየተፈጠረ ያለውን ስጋት የሚያንጸባርቅ ነው።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ጦርነቱ በጋዛ ነዋሪዎች ላይ ስላስከተለው ተጽዕኖ በመናገርም ይታወቃሉ።

የእስራኤል መንግሥትን በሚደግፉ መገናኛ ብዙኃን "ለፍልስጤማውያን በመወትወት" የሚከሰሱት ኦልሜርት፤ "ይህ በጭራሽ የማንታገሰው፣ ተቀባይነት የሌላው እና ይቅር የማይባል ነው። አሁኑኑ መቆም አለበት" ብለዋል።

አክለውም፤ "ሕዝቡ የሚያስፈልገውን ሰብአዊ ድጋፍ በሙሉ ማቅረብ አለብን። በጋዛ ረሃብ መከሰቱን ህሊናችን ሊቀበለው አይችልም" በማለት ተናግረዋል።

ይህ ዓይነቱ ሃሳብ በእስራኤል መገናኛ ብዙኃን እና በሚሰበሰቡ የሕዝብ ድምጾች ላይ የሚንጸባረቀው እምብዛም ቢሆንም በተባበሩት መንግሥታት፣ በእርዳታ ድርጅቶች እና በእስራኤል የውጭ አጋሮች የተደረጉ ስሜት የተሞላባቸው ንግግሮች ይህንን አስተጋብተዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኤማኑኤል ማክሮን እስራኤል በጋዛ የፈጸመችውን ድርጊት "አሳፋሪ" ሲሉ ጠርተውታል። ኔታያናሁ ደግሞ የፈረንሳዩን ፕሬዝዳንት "ከሐማስ ጋር በመቆም" ከስሰዋል።

እስራኤል ወደ ፍልስጤማውያን ግዛቶች ምንም ምግብ፣ መድኃኒት እና ነዳጅ እንዳይገባ የጣለችውን 10 ሳምንታትን የቀዘለ እገዳ ተከትሎ በመላው ጋዛ ስቃይ እየጨመረ መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎች እየወጡ ነው።

ምግብ የሚቀበሉ ፍልስጤማውያን እየተጋፉ እና እያለቀሱ

የፎቶው ባለመብት, EPA / Shutterstock

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የተባበሩት መንግሥታት ድጋፍ ያደረገለት አንድ የዳሰሳ ጥናት፤ 2.1 ሚሊዮን ገደማ የሚሆነው የጋዛ ሕዝብ "ከፍተኛ" የረሃብ "ስጋት" እንዲሁም "ከፍተኛ ደረጃ ያለው የምግብ ደኅንነት እጦት" እንደተጋረጠበት አሳይቷል።

የዓለም የጤና ድርጅት በበኩሉ ያለ በቂ ተመጣጣኝ ምግብ፣ ንጹህ ውሃ እና የጤና አገልግሎት፤ መላው ትውልድ ዘላቂ ጉዳት እንደሚደርስበት ተናግሯል።

የእስራኤል መንግሥት ቃል አቀባይ ዴቪድ ሜንሰር ግን "በእርግጠኝነት እስራኤል ጋዛን እያስራበች አይደለም" በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ጋዛ ውስጥ ረሃብ የመኖሩን ጉዳይ እየተቃወምኩ አይደለም፤ ነገር ግን ረሃቡ የተፈጠረው በሐማስ ነው። የእኛ መረጃ ጋዛ ውስጥ ምግብ እንዳለ ነው። ቸነፈር ግን የለም" ብለዋል።

እስራኤል መጋቢት ላይ ጋዛ ላይ የምትፈጽመውን የአየር ድብደባ በድጋሚ አስጀምራለች። በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር ረቡዕ ዕለት የተገደሉትን 80 ሰዎች ጨምሮ እስካሁንም 2,799 ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል።

የተሻሻለው እና በአሜሪካ የተዘጋጀው የተኩስ አቁም ስምምነት በእስራኤል እና ሐማስ ተቀባይነት ያገኛል የሚለው ተስፋ የሳሳ ሆኗል። በዚህ ስምምነት እስራኤል ላልተወሰነ ጊዜ የምታደርሰውን ጥቃት እንድታቆም፤ ሐማስ ደግሞ በምላሹ የቀሩትን የተወሰኑ ታጋቾች እንዲለቅቅ እንደሚደረግ ተገልጿል።

ነገር ግን ኔታያናሁ እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን ወታደራዊ ጥቃት እንደምታጠናክር እና ምንም ነገር ጦርነቱን እንደማያስቆም ተናግረዋል። ሐማስም፤ እስራኤል ቋሚ ተኩስ አቁም ለማድረግ እና ጋዛን ለቅቃ ለመውጣት ካልተስማማች ታጋቾችን እንደማይለቅ አሳውቋል።

ረቡዕ ዕለት ምሽት 67 የቀድሞ ታጋቾች ኔታያናሁ በሐማስ የተያዙ ታጋቾችን በሙሉ ለማስለቀቅ "ሁሉን አቀፍ ስምምነት" ላይ እንዲደርሱ የሚጠይቅ ደብዳቤ ላይ ፊርማቸው አኑረዋል።

ደብዳቤው፤ "አብዛኛው የእስራኤል ኅብረተሰብ ወታደራዊ ዘመቻዎች ተቋርጠውም ቢሆን ታጋቾች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ይፈልጋል" ይላል።

የእስራኤሉ ቻናል 12 ሚያዝያ ላይ ያሰባሰበው የሕዝብ አስተያየት እንደሚያመላክተው ጥያቄ የቀረበላቸው 68 በመቶ የሚሆኑ መላሾች ጦርነቱ ተቋርጦም ቢሆን ከሐማስ ጋር ታጋቾችን የማስመለስ ስምምነት እንዲፈጸም ይፈልጋሉ። በጋዛ ጦርነት እንዲቀጥል የሚፈልጉት 22 በመቶ የሚሆኑት መላሾች ናቸው።