የእስራኤል የደኅንነት ካቢኔ ጋዛን 'ለመቆጣጠር' የቀረበውን ዕቅድ ማጽደቁ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የእስራኤል ደኅንነት ካቢኔ የአገሪቱ ሠራዊት ጋዛን "መቆጣጠርን" ጨምሮ ሐማስ ላይ የሚያካሄደውን የጥቃት ዘመቻ ለማስፋት የወጣውን ዕቅድ ማጽደቁን አንድ የእስራኤል ባለሥልጣን አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ዕቅዱ ሐማስን ለመደምሰስ እና የቀሩትን ታጋቾች ለማስመለስ የሚያስችል በመሆኑ "ጥሩ ዕቅድ" መሆኑን መናገራቸውን ባለሥልጣኑ ጠቅሰዋል።
ካቢኔው በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት ከባድ የምግብ ዕጥረት አስከትሏል ያለው በጋዛ ላይ ለሁለት ወራት የተጣለውን ዕቀባ ለማብቃት የግል ድርጅቶች ወደ ጋዛ እርዳታ እንዲያስገቡ እና እንዲያከፋፍሉ የቀረበውን ዕቅድ በመርኅ ደረጃ አጽድቋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት እና ሌሎች የእርዳታ ተቋማት የቀረበው ዕቅድ መሠረታዊ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መርሆችን የሚጥስ ነው በማለት እንደማይተባበሩ አስታውቀዋል።
ሐማስ በበኩሉ በእስራኤል በቀኩል የቀረበው ሐሳብ "ፖለቲካዊ ማስፈራራት" ነው ብሎታል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ የደኅንነት ካቢኔ ለሁለት ወራት የቆየውን የተኩስ አቁም ማብቃት ተከትሎ በጋዛ ውስጥ የሚካሄደውን ወታደራዊ ዘመቻ በተመለከተ የተወያየበትን ስብሰባ ያደረገው ትናንት እሁድ ምሽት ነው።
አንድ የእስራኤል ባለሥልጣን ዛሬ ሰኞ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ገለጻ፣ የካቢኔ ሚኒስትሮቹ በአገሪቱ ጦር ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሌ/ጄነራል ኢያል ዛሚር የቀረበውን "በጋዛ ውስጥ ሐማስን በመደምሰስ ታጋቾችን የማስለቀቅ" ዕቅድ በሙሉ ድምጽ አጽድቀውታል።
"ዕቅዱ ከያዛቸው ተግባራት መካከል ጋዛ ሰርጥን በመቆጣጠር ይዞታን ማስፋት፣ የጋዛ ነዋሪዎችን ለመከላከያነት ወደ ደቡብ መዘዋወር፣ የሐማስን እርዳታ የማሠራጨት አቅምን ማዳከም እና በቡድኑ ላይ ከባድ ጥቃት መፈጸምን የሚያካትት ነው" ብለዋል ባለሥልጣኑ።
የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ዕቅዱ ወራትን የሚፈጅ እና በመጀመሪያው ደረጃ ተጨማሪ የጋዛ አካባቢዎችን መቆጣጠር እንዲሁም በጋዛ ድንበር አካባቢ ያሉትን የእስራኤል "የመከላከያ ቀጠናዎችን" ማስፋትን ይጨምራል።
ይህ እስራኤል ከሐማስ ጋር በምታካሂደው አዲስ የተኩስ አቁም ድርድር ላይ ተጨማሪ አቅም የሚሰጣት ይሆናል ተብሏል።
የእስራኤል የደኅንነት ካቢኔ አባል የሆኑት ዚቭ ኤልኪን እንደተናገሩት ትራምፕ ከሳምንት በኋላ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚያደርጉት ጉብኝት ከማብቃቱ በፊት "ሐማስ ማምረራችንን ከተረዳ" ታጋቾች የሚለቀቁበት "ዕድል" አለ ብለዋል።
እሁድ ዕለት አንድ የባሕር ኃይል ሰፈርን የጎበኙት ሌ/ጄነራል ዛሚር ለልዩ ኃይሎቻቸው ባደረጉት ንግግር "በጋዛ ውስጥ የሚካሄደውን ዘመቻ ለማጠናከር እና ለመስፋት" በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የተጠባባቂ ጦር አባላት መጠራታቸውን ገልጸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቺዎቹ የተኩስ አቁሙ ማብቃቱን ተከትሎ በቅርቡ በተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ታጣቂዎቹን ለማስለቀቅ አለመቻላቸውን በመግለጽ፣ ኔታንያሁ በዚህ ግጭት ዓላማቸው ምንድን ነው የሚለው ጥያቄ ውስጥ ወድቋል ብለዋል።
በዕቅዱ መሠረት ወታደሮቹ በአዲስ አካባቢ ተሰማርተው በምድር እና ከምድር በታች የሚገኙ የሐማስ "ሁሉንም መሠረተ ልማቶች ያወድማሉ።"
የካቢኔ አባላቱ ለበርካታ ወራት ቀስ በቀስ የሚደረግ የምድር ላይ ዘመቻን ዕቅድ ያለምንም ተቃውሞ ማጽደቃቸውን የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስራኤል ከሃማስ ጋር የምታደርግ ዓለም አቀፍ ድርድር አዲስ የተኩስ አቁም ላይ ለመድረስ እና በሃማስ ቁጥጥር ስር የሚገኙትን 59 እስራኤላውያን፣ 24ቱ በሕይወት አሉ ተብሎ ይታመናል፣ ማስለቀቅ ሳይችል ቀርቷል።
እስራኤል ለሁለት ወር የዘለቀው የተኩስ አቁም አብቅቶ እአአ መጋቢት 18 ዳግመኛ የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረች ወዲህ አንድም እስራኤላዊ ታጋች ማስለቀቅ አልቻለችም።
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስራኤል የጋዛ በርካታ ስፍራዎችን በቁጥጥሯ ስር ያዋለች ሲሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በጋዛ ሰርጥ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን ከቤት ንብረታቸው በተደጋጋሚ አፈናቅላለች።
እስራኤል በጋዛ የምታካሄደውን ወታደራዊ ዘመቻ እንዲሁም ከሁለት ወር በላይ ማንኛውም እርዳታ እንዳይገባ ማገዷን በሐማስ ላይ ጫና ለማድረግ ያለመ ነው ስትል ትገልጻለች።
በጋዛ ከፍተኛ የሆነ የምግብ፣ የውሃ እና የመድሃኒት እጥረት መፈጠሩን የሚገልጹ የእርዳታ ድርጅቶች የእስራኤል እርምጃ ፍልስጤማውያንን የማስራብ ፖሊሲ ሲሆን ከጦር ወንጀል ጋር ይስተካከላል ይላሉ።
እስራኤል ይህንን ውንጀላ አትቀበልም።
እስራኤል ከሃማስ ጋር ጦርነት ከጀመረች ጊዜ ጀምሮ በተደጋጋሚ ለግዳጅ የተጠሩት ተጠባባቂ ኃይሎች ላይ አሁን ያቀደችው የሰፋ የማጥቃት እቅድ የበለጠ መሰላቸት ይፈጥራል።
የታጋች ቤተሰቦች መንግሥት በሕይወት ያሉ እስራኤላውያን ለማስለቀቅ ከሃማስ ጋር እንዲደራደር እየየጠቁ ነው።
ይህ የአሁኑ ዕቅድ ኔታንያሁ በዚህ ጦርነት ውስጥ ያላቸው ዓላማ ምንድን ነው የሚለው ላይ ዳግም ጥያቄ አስነስቷል።
ኔታንያሁ በተደጋጋሚ በታጋች ቤተሰቦች እና በተቃዋሚዎቻቸው ለፖለቲካ ሲሉ የተኩስ አቁም ስምምነቶችን ያስተጓጉላል፤ ጦርነቱን ያራዝማሉ የሚል ነቀፌታ ቢቀርብባቸውም በተደጋጋሚ አስተባብለዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አገራቸው በጋዛ ጦርነት ከጀመረች 19 ወር ቢሆንም ከጦርነት የመውጫ እቅድ አቅርበው አያውቁም።
አርብ ዕለት መከላከያ ኃይሉ ለኔታንያሁ በጋዛ ለማካሄድ ላሰበው ማጥቃት ዕቅዱን ማቅረቡን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተጠባባቂ ኃይሎች ፊርማ በማሰባሰብ የኔታንያሁ መንግሥት ውግያውን እንዲያቆም እና ትኩረቱን ታጋቾቹን ለማስለቀቅ ድርድር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ቅዳሜ ምሽት ጦርነቱ እንዲያበቃ የሚጠይቅ ሠላማዊ ሰልፍ በእስራኤል የተለያዩ ከተሞች ተካሂዷል።
በሰልፉ ላይ የተገኘች በጋዛ አሁንም ልጇ ታግቶ የሚገኝ እናት "አላስፈላጊ ጦርነት" ስትል ተናግራለች።
የእስራኤል ጦር እሁድ ዕለት ሁለት ተጨማሪ ወታደሮች በጋዛ መገደላቸውን ይፋ አድርጓል።
እሁድ ዕለት ማለዳ ላይ በኢራን የሚደገፉት የየመን አማፂያን በእስራኤል ዋና አየር ማረፊያ ቤን ጉራዮን ሚሳዔል አስወንጭፈው በተርሚናሉ አቅራቢያ አርፏል።
ኔተንያሁ ታጣቂዎቹን ለመበቀል ዝተዋል።
ሁቲዎች እስራኤል በጋዛ ለመፈጸም ያሰበችውን አዲስ ዕቅድ በተመለከተ በሰጡት ምላሽ በተደጋጋሚ አየር ማረፊያዎቿን ዒላማ በማድረግ "የአየር ማዕቀብ" እንደሚያደርጉባት አስጠንቅቀዋል።
በጋዛ በሃማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር እሁድ ዕለት በ24 ሰዓት ውስጥ 40 ሰዎች ሲገደሉ 125 መቁሰላቸውን አስታውቋል።
እስራኤል ሐማስ ላይ የሚደረግ ወታደራዊ ጫና በቁጥጥሩ ስር የሚገኙ 59 ታጋቾች ለማስለቀቅ ያግዛል ትላለች።
ሐማስ በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7/2023 በእስራኤል ላይ ጥቃት ፈጽሞ 1200 ሰዎችን በመግደል 251 አግቶ ከወሰደ በኋላ ነው እስራኤል በጋዛ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሔድ የጀመረችው።
በጋዛ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከ 52,535 በላይ ፍልስጤማውያን መሞታቸውን የግዛቲቱ ጤና ሚኒስቴር ይናገራል።
ከእነዚህ መካከል 2,436 የተገደሉት እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን ጥቃት ዳግም ከቀጠለች በኋላ መሆኑን የጋዛ ጤና ሚኒስትር አስታውቋል።












