ሩሲያ እና ዩክሬን ዛሬ የሰላም ንግግር ይጀምራሉ፣ ፕሬዝዳንት ፑቲን አይሳተፉም

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዛሬ ቱርክ ኢስታምቡል ውስጥ በሚካሄደው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትን የተመለከተ የሰላም ንግግር ላይ እንደማይገኙ ተገለጸ።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በንግግሩ ላይ መሪዎች እንዲገኙ ጥያቄ ቢያርቡም ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ የሩሲያ ልዑክ የሚመራው በፑቲን ረዳት ቭላድሚር ሜዲኒስኪ መሆኑን አመለክቷል።

ቀደም ሲል ቭላድሚር ፑቲን በሰላም ንግግሩ ላይ የሚገኙ ከሆነ ዜሌንስኪ እራሳቸው እንደሚሳተፉ እና ከፑቲን ጋር ለሚደረግ የፊት ለፊት ንግግር ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀው ነበር።

ፕሬዝዳንት ፑቲን ኢስታምቡል የሚገኙ ከሆነ የአሜሪካው ፕሬዝዳንትም ሊገኙ እንደሚችሉ ፍንጭ ተስጥቶ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ትራምፕ በንግሩ ላይ እንደማይሳተፉ ተገልጿል።

ነገር ግን የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዛሬ ሐሙስ በቱርክ ዋና ከተማ አንካራ ውስጥ ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይብ ኤርዶዋን ጋር ይገናኛሉ ተብሏል።

ፑቲን በንግገሩ ላይ የሚሳተፉ ከሆነ ዜሌንስኪም በቀጥታ እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።

ፑቲን እና ዜሌንስኪ ከታኅሣሥ 2019 ወዲህ በአካል ተገናኝተው አያውቁም። ሩሲያ እና ዩክሬን የመጨረሻውን ቀጥተኛ ድርድር ያደረጉት ሞስኮ መጠነ ሰፊ ጥቃትን በዩክሬን ላይ ከከፈተች ከአጭር ጊዜ በኋላ ቱርክ ውስጥ ነበር።

ሁለት ዓመት ባለፈው የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ሩሲያ በምሥራቃዊ ዩክሬን ያሉ ግዛቶችን ቀስ በቀስ በማስፋፋት ተቆጣጥራለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ባለፈው እሁድ ፕሬዝዳንት ፑቲን በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ቀጥተኛ ንግግር በቱርክ ትልቋ ከተማ ኢስታምቡል ውስጥ "ያለምንም ቅድመ ሁኔታ" እንዲካሄድ ጥሪ አቅርበዋል። ለዚህምምላሽ ፕሬዝዳንት ዜኔንስኪ ፑቲን የሚሳተፉ ከሆነ እራሳቸው በቀጥታ እንደሚገኙ አሳውቀው ነበር።

የፑቲን የኢስታምቡል ንግግር ሃሳብ የመጣው የአውሮፓ መሪዎች ቅዳሜ ዕለት በዩክሬን ዋና ከተማ ኪየቭ ከተገናኙ በኋላ ለአንድ ወር የሚቆይ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ ካቀረቡ በኋላ ነው።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ዩክሬን የንግግር ጥሪውን እንድትቀበል መጠየቃቸውን ተከትሎ ዜሌንስኪ እራሳቸው በንግግሩ ላይ በቀጥታ እንደሚሳተፉ ገልጸው ነበር።

ዛሬ በሚደረገው ንግግር ላይ ፑቲን የሚገኙ ከሆነ ትራምፕም ሊገኙ የሚችሉበት ዕድል እንደሚኖር ትናንት ረቡዕ አሳውቀው ነበር።

ኳታር የሚገኙት ትራምፕ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት በንግግሩ ላይ ፕሬዝዳንት ፑቲን ስለመገኘታቸው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል።

ነገር ግን አሜሪካ በከፍተኛ ባለሥልጣን የሚመራ ልዑክ በንግግሩ ላይ እንዲሳተፍ እንደምትልክ ይጠበቃል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ማርኮ ሩቢዮ ዛሬ ሐሙድ ከኔቶ አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ለመወያየት ረቡዕ ዕለት ቱርክ መግባታቸው ተነግሯል።

ከሩሲያ እና ዩክሬን ንግግር በፊት ከሩቢዮ ጋር የተገናኙት የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪ ሳይቢያህ አሜሪካ ሰላም ለማውረድ ለማታደርገው ጥረት አገራቸው ቁርጠኛ መሆኗን እና ሩሲያ "ገንቢ እርምጃ በመውሰድ" ምላሽ እንድትሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።

ወደ ሥልጣን እንደተመለሱ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሩሲያ እና የዩክሬንን ጦርነት እንሚያስቆሙ የተናገሩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተኩስ እንዲቆም ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ከጦርነቱ መጀመር በኋላ በፑቲን ላይ ምዕራባውያን እየወሰዱት የነበረውን የማግለል እርምጃ በማብቃት ትራምፕ ፑቲንን በስልክ ከማናገር አልፈው ልዩ መልዕክተኛቸውን ወደ ሞስኮው ልከዋል።