ዜሌንስኪ ከፑቲን ጋር የሚካሄደው ቀጥተኛ ንግግር እንዲሳካ "ማንኛውንም ነገር ለማድረግ" ቃል ገቡ

የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን እና የዩክሬኑ ቮሎድሞር ዜሌንስኪ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የቱርኩን ፕሬዝዳንት ረሲብ ጠይብ ኤርዶዋንን ለማግኘት አስቀድመው ወደ አንካራ እንደሚሄዱ አስታውቀው፣ ከሩሲያው አቻቸው ጋር ሐሙስ ዕለት በሚያደርጉት ቀጥተኛ ንግግር ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

"ስብሰባው እንዲካሄድ ማንኛውንም ነገር እናደርጋለን" ሲሉ በኪየቭ ለተሰበሰቡ ጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ሩሲያ እስካሁን ድረስ በአንካራ በሚካሄደው ቀጥተኛ ንግግር ላይ ማን እንደሚሳተፍ አላሳወቀችም።

ፑቲን እና ዜሌንስኪ እንደ አውሮፓውያኑ ታሕሳስ 2019 ወዲህ ፊት ለፊት ተገናኝተው አያውቁም።

በሁለቱ አገራት መካከል ቀጥተኛ ውይይት የተካሄደው ሩሲያ ወረራውን በፈጸመች ጥቂት ጊዜያት ውስጥ እ.አ.አ በ2022 መጋቢት ወር ላይ ነበር።

በቱርክ "ያለምንም ቅድመ ሁኔታ" የሚደረገውን ቀጥተኛ ውይይት የጠሩት የሩሲያው ፕሬዝደንት ሲሆኑ፣ ያንን ተከትሎ ዜሌንስኪ ራሳቸው ወደ አንካራ እንደሚሄዱ አስታውቀው ፑቲንም ተመሳሳዩን አንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

አሜሪካም ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ወደ ስፍራው ትልካለች ተብሎም ይጠበቃል።

ዜሌንስኪ ማክሰኞ ዕለት ወደ ቱርክ እንደሚሄዱ በተናገሩበት ወቅት ሩሲያ በድርድሩ ላይ የሚሳተፉትን አካላት እንድታሳውቅ ጫና መፍጠር መፈለጋቸው በግልጽ ያስታውቅ ነበር።

ክሬምሊን ከዚህ በፊት ጫና ለመፍጠር መሞከር "ረብ የለሽ ነው" ስትል ያስጠነቀቀች ሲሆን፣ ለሚቀመጡ መስፈርቶች ምላሽ እንደማትሰጥ ተናግራለች።

ሩሲያ ጦርነቱን "ከመሰረቱ" ለመፍታት በ2022 ወረራውን ከመፈጸሟ በፊት አስቀምጣቸው የነበሩ እና በኪየቭ በተደጋጋሚ ውድቅ የተደረጉት ጠንካራ ቅድመ-ሁኔታዎች ላይ ማተኮር ትፈልጋለች።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ከፑቲን ጋር በኢስታንቡል ለመገናኘት በዝግጅት ላይ እያሉ ቅድሚያ የሚሰጡት የ30 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነትን ማረጋገጥ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም በሁሉም የዩክሬን አጋር አገራት፣ አሜሪካን ጨምሮ ከስምምነት የተደረሰበት ጉዳይ ነው።

ዜሌንስኪ ፑቲን እሁድ ምሽት በቱርክ ቀጥታ ንግግር እንዲደረግ ያቀረቡት ግብዣ ኪየቭን ቅርቃር ውስጥ ለመክተት ያለመ ነበር ብለዋል።

በባህረ ሰላጤው አገራት በጉብኝት ላይ ያሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "ነገሮች በታቀደላቸው መንገድ የሚሄዱ ከሆነ" ወደ ኢስታንቡል ሊሄዱ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኞች ስቲቭ ዊትኮፍ እና ኪት ኬሎግ በዕለቱ ወደ ኢንስታንቡል እንደሚያመሩ የተገለፀ ሲሆን እስካሁን ድረስ ትራምፕ ወደ ስፍራው የመሄዳቸው ነገር አልታወቀም።

ክሬምሊን በበኩሏ ፑቲን ራሳቸው በቀጥተኛ ንግግሩ ላይ ይሳተፋሉ የሚለውን መላምት አጣጥላለች።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲምትሪ ፔስኮቭ "ሩሲያ ሐሙስ ዕለት ለሚካሄደው ድርድር ዝግጅት ማድረጓን ቀጥላለች። አሁን ማለት የምንችለው ይህንን ብቻ ነው" ብለዋል።

ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ሪያብኮቭ ማክሰኞ ዕለት ከ2022 ጀምሮ በከፊል በሩሲያ የተያዙትን አራት የዩክሬን ደቡብ ምሥራቅ ግዛቶችን ጠቅሰው፣ ሞስኮ "በመሬት ላይ ያለውን እውነታ" ከግምት ውስጥ በማስገባት "በኃላፊነት" ንግግሮችን ለማካሄድ ተዘጋጅታለች ብለዋል።

በተጨማሪም ሞስኮን ወረራ ከመፈጸሟ በፊት ያቀረበችውን ጥያቄ በመድገም ዩክሬን እና ምዕራባውያን አጋሮቿ ይህንን እንደ ቅድመ ሁኔታ ያዩታል ብለዋል።

ሪያብኮቭ ዩክሬን ስምምነቱን አክብራ ትቆያለች የሚለው ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ገልጸዋል።

የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ካጃ ካላስ፣ ዜሌንስኪ እና ፑቲን ፊት ለፊት ቢነጋገሩ ጥሩ እርምጃ ነው ካሉ በኋላ "ፑቲን የሚደፍር አይመስለኝም" ብለዋል።

ዜለንስኪም ፑቲን ፊት ለፊት ለመገናኘት "ፈርቷል" ሲሉ ተናግረዋል።

የፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አንድሪይ ያርማክ የሩስያ ፕሬዝዳንት ወደ ኢስታንቡል የማይሄዱ ከሆነ ጦርነቱን ማቆም እንደማይፈልጉ "የመጨረሻ ምልክት" ይሆናል ብለዋል።

የዩክሬን ዋና አጋር መሪዎች እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ፖላንድ እና ፈረንሳይ ሩሲያ የ30 ቀን የተኩስ አቁም ስምምነት ካልተቀበለች አፋጣኝ ተጨማሪ ማዕቀቦች እንደሚጣል ለማስጠንቀቅ ቅዳሜ እና እሁድ ወደ ኪየቭ ተጉዘው ነበር።