ኢትዮጵያውያን በደቡብ አፍሪካው ምርጫ ማን እንዲመረጥ ይፈልጋሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከደቡብ አፍሪካ አጠቃላይ ሕዝብ መካከል 3 በመቶ የሚሆነው (2.4 ሚሊዮኖቹ) ስደተኞች ናቸው። ከእነዚህ ስደተኞች መካከል ደግሞ በርካታ ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል።
በተለይም በንግድ ሥራ ላይ ለተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ዋነኛ መዳረሻ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ በሆነችው ደቡብ አፍሪካ ዛሬ ግንቦት 21/ 2016 ዓ. ም. ዜጎች ድምጽ መስጠት ጀምረዋል።
በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ስደተኞች ቁጥራቸው ውስን ቢሆንም ከአገሬው ሥራ በመቀማት እና ለወንጀል መበራከት አስተዋጽኦ በማበርከት እንደሚተቹ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።
በተለይ ደግሞ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ሌሎችም ስደተኞች ላይ የሚፈጸሙ መጤ ጠል የሆኑ ጥቃቶች ቁጥራቸው ጨምሯል።
የመብት ተሟጋቹ ሂውማን ራይትስ ዋች በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት እንዳለው፣ የውጭ አገር ዜጎች በፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ ቅስቀሳ እንደ ሰበብ እየዋሉ መሆኑ የሚደርስባቸውን መጤ ጠል ጥቃት እያባባሰው ይገኛል።
ድብደባ፣ የሀብት ዘረፋ እና ሌሎችም እንግልቶች ኢትዮጵያውያን ላይ መድረሳቸው በተደጋጋሚ ተዘግቧል።
ከዘንድሮው ምርጫ ኢትዮጵያውያን ምን ይጠብቃሉ? ማን ቢመረጥስ የተሻለ መብታቸውን ያስከብራል? ስንል ለዓመታት በደቡብ አፍሪካ የኖሩ ኢትዮጵያውያንን አነጋግረናል።
“ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከሕዝቡ እኩል ውጤት የሚጠብቅበት ነው”
በደቡብ አፍሪካ ለ23 ዓመት የኖረውና የማኅበረሰብ መሪዎች አባል የሆነው ዳዊት ተወልደመድኅን እንደሚለው፣ አዲስ የሚያሸነፍ ፓርቲ ቢኖር ምን ሊፈጥር እንደሚችል ስለማይታወቅ ኢትዮጵያውያን የአፍሪካውያን ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ቢያሸንፍ እንደሚመርጡ ያምናል።
በደቡብ አፍሪካ ለ20 ዓመታት የኖረችው ነጋዴ መዓዛ ተስፋዬ እንደምትናገረው፣ ኤኤንሲ ሊያሸንፍ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ቢሆንም የትኛውም ፓርቲ ወደ ሥልጣን ቢመጣ ለስደተኞች ለውጥ አይኖርም።
ዛሬ በምርጫው ዕለት እሷ የምትነግድበትን አካባቢ ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎችም ሱቆች ተዘግተው በሰላም ድምጽ እየተሰጠ እንደሆነ ታክላለች።
በደቡብ አፍሪካ ለ16 ዓመታት የኖረው እና በአገሪቱ የፍትሕ ቢሮ የሚሠራው እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን የማማከር አግልግሎት የሚሰጥ ቢሮ ያቋቋመው ኮስሞስ ገብረሚካኤል በበኩሉ፣ የዘንድሮው ምርጫ በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠበቀ ያለ እንደሆነ ይናገራል።
“ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከሕዝቡ እኩል ውጤቱን የሚጠብቅበት ነው” ሲል ይገልጻል።
የዘንድሮው የደቡብ አፍሪካ ምርጫ ከባድ ፉክክር እንደሚኖረው ይጠበቃል።
ሥራ አጥነት፣ ከፍተኛ የወንጀል መስፋፋት፣ የስደተኞች ጉዳይ፣ የምጣኔ ሃብት መዳከም እና የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ዋነኛ የትኩረት አጀንዳዎች ናቸው።
እአአ ከ1994 ጀምሮ እስካሁን ሥልጣን ላይ ያለው ገዢው ፓርቲ አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ከፍተኛ ፉክክር የሚገጥመው በዘንድሮው ምርጫ እንደሆነ ተገልጿል።
ከኤኤንሲ በተባረረው ጁልየስ ማሌማ የተመሠረተው ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ (ኢኤፍኤፍ) ፓርቲ በተለይም ለጥቁር ድሃ ደቡብ አፍሪካውያን በሚያሳየው መቆርቆር በዘንድሮው ምርጫ ትኩረት ከሳቡት መካከል ነው።

“አዲስ የሚያሸነፍ ፓርቲ ቢኖር ምን ሊፈጥር እንደሚችል አናውቅም”
ዳዊት እንደሚለው፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለደቡብ አፍሪካ ምጣኔ ሀብት መውደቅ እና ለመብራት መቆራረጥ ተጠያቂ የሚያደርጉት ኤኤንሲን ነው።
“ምጣኔ ሀብቱ ወድቋል። የአመራር ጉድለት ይመስለኛል። ተቃዋሚዎች ለዚህ ተጠያቂ የሚያደርጉት ኤኤንሲን ነው” ይላል።
ኤኤንሲ ተቃውሞው ቢበረታበትም የማሸነፍ ዕድሉ እንደሚሰፋ በመግለጽ፣ የኢትዮጵያውያን ምርጫም ኤኤንሲ እንደሆነ ያስረዳል።
“አዲስ የሚያሸነፍ ፓርቲ ቢኖር ምን ሊፈጥር እንደሚችል አናውቅም። እዚህ እንደሚኖር ኢትዮጵያዊ ኤኤንሲ ቢያሸነፍ ነው የምመርጠው። ባለንበትም መኖር ቀላል አይደለም” ሲል ነገሮች ባሉብት ቢቀጥሉ ለስደተኞች የተሻለ እንደሆነ ያስረዳል።
“ስደተኛው እስካሁን የኖረው በኤኤንሲ ነው። ሌሎቹ ቢያሸንፉ ስደተኛውን ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ አይታወቅም” ሲል ዳዊት ያስረዳል።
ኮስሞስ በበኩሉ ከፍተኛ ፉክክር እያደረገ ያለው ዴሞክራቲክ አሊያንስ (ዲኤ) ከ30 በመቶ በላይ ድምጽ እንደሚያገኝ ይገምታል።
ኤኤንሲ 40 በመቶ ድምጽ እንደሚያገኝና ቀሪውን ድምጽ ኢኤፍኤፍ፣ ኢንካታ ፍሪደም ፓርቲ (አይኤፍፒ) አክሽን ኤስኤ እና የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጄኮብ ዙማ ፓርቲ የሆነው ኤምኬ ያገኛሉ ብሎ ይገምታል።
ጥምረት በመፍጠር ደረጃ የተሻለ ድምጽ ሊያገኙ የሚችሉት አይኤፍፒ፣ ኢኤፍኤፍ እና ዲኤ እንደሆኑም ያምናል።
ዲኤ (ዴሞክራቲክ አሊያንስ) ለስደተኞች አደገኛ እንደሆነ የሚናገረው ዳዊት፣ የጁልየስ ማሌማ ፓርቲ ከሆነው ከኢኤፍኤፍ ውጪ ያሉት ፓርቲዎች “ስደተኞችን አይቀበሉም” ሲል ያስረዳል።
መዓዛ በበኩሏ በየአምስት ዓመቱ ምርጫ ሲደረግ “ስደተኞችን እናስወጣለን” በማለት ዜጎች ድምጽ እንዲሰጡ ቅስቀሳ እንደሚደረግ ትናገራለች።
“ንግድ ላይ የእኛን ያህል ብዙ ደቡብ አፍሪካውያን ስለማይሰማሩ፣ ስደተኞችን አስወጥተን ሥራውን ለእናንተ እንሰጣለን ብለው ይቀሰቅሳሉ” ትላለች።
ሆኖም ግን ባለፉት ዓመታት ባየቻቸው ምርጫዎች “ምንም የተቀየረ ነገር የለም” በማለት ዘንድሮም ይቀየራል ብላ የምትጠብቀው ነገር እንደሌለ ታስረዳለች።
ኮስሞስ ዋነኛ ስጋቱ ‘ዘ ዋይት ፔፐር’ የተባለው ለስደተኞች አስጊ የሆነው እና በደቡብ አፍሪካ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የፀደቀው መርኅ ነው።
ይህ መርኅ የስደተኞችን መብት የሚነፍግ እና ደቡብ አፍሪካ ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ስምምነት እንድትወጣ ፍኖተ ካርታ ያዘጋጀ እንደሆነ ይናገራል።
ከሌሎች አገራት በተሻለ ስደተኞችን የሚቀበል አሠራር በነበራት እና በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ከየትኛውም አገር በተሻለ ሀብት ንብረት ማፍራት ይችሉባት በነበረችውን ደቡብ አፍሪካ ያለውን የስደተኞች አቀባበል ሥርዓት የሚለውጥ መርኅ ነው።
“የወጣው ሕግ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ አደጋ ነው የሆነው። ምንም ዓይነት አዲስ ስደተኞች የማይቀበሉት አሠራር ነው” ይላል ኮስሞስ።
በከፍተኛው ፍርድ ቤት ያልተፈቀደ የስደተኞች ጥያቄ ተቀባይነት እንዳያገኝ እንደሚያደርግ እና ይህ ማለት ደግሞ ስደተኞች ፈቃድ እስከሚያገኙ ረዥም ጊዜ እንዲቆዩና ከፍተኛ ወጪ እንዲያወጡ የሚያደርግ እንደሆነ ያስረዳል።
“ስደተኞች መንገድ ላይ በፖሊስ ቢታሰሩ ወይም ሌባ በጩቤ ቢወጋቸው ሕገ ወጥ ስለሆኑ ፖሊስ ጣቢያ ሄደው መክሰስ አይችሉም” ሲል ስጋቱን ይገልጻል።
ከምርጫው በኋላ በዚህ መርኅ ላይ የሚለወጥ ነገር ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለም።
“ለስደተኞች ብዙም የሚለወጥ ነገር አይኖርም”
ዛሬ ድምጽ የመስጠት ሂደቱ በሰላማዊ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሆነ የሚናገረው ዳዊት፣ ዲኤ ፓርቲ ለስደተኞች ከፍተኛ አደጋ የጋረጠ እንደሆነ ያስረዳል።
መዓዛ በበኩሏ፣ ኤኤንሲ ማሸነፉ ባይቀርም ኢኤፍኤፍ ለስደተኞች የተሻለ እንደሆነ ትናገራለች።
“ማሌማ እስካሁን ተመርጦ ባናየውም ‘አፍሪካ፣ አፍሪካ ነው። አንድ ነን’ በማለት ለስደተኞች ጠንከር ብሎ የቆመ ነው” ትላለች።
ኮስሞስ በበኩሉ፣ ኢኤፍኤፍን “በግል ልደግፈው ብችልም እንደ አገር ስኬታማ ፓርቲ ይሆናል የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው” ይላል።
“ዲኤ ለእኛ መጥፎ ሊሆን ይችላል” የሚለው ኮስሞስ በሚኖርበት ኩዋዙሉ ናታል ፓርቲው በከፍተኛ ሁኔታ ተቀባይነት እንዳለው ያክላል።
ዋናው የሕዝብ ጥያቄ የምጣኔ ሀብት መሻሻል እንዲመጣ፣ የቤት አቅርቦት እንዲሻሻል እና የመብራት መቆራረጥ እንዲቆም እንደሆነ ኢትዮጵያውያኑ ይስማሙበታል።
መዓዛ፣ ካለፉት ዓመታት ተሞክሮዋ ተነስታ እንደምትለው የስደተኞችን ጉዳይ ለምርጫ ቅስቀሳነት ከማዋል ባለፈ እምብዛም ለስደተኞች የሚለወጥ ነገር ይሆራል ብላ አትጠብቅም።
“ለኢትዮጽያውያን ይሄ ይሻላል የምንለው ፓርቲ ያለ አይመስለኝም” ትላለች መዓዛ።
ኮስሞስ፣ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ደቡብ አፍሪካ እንደ አገር እንድትቀጥል እና ምጣኔ ሀብቱም እንዲያድግ በማድረግ የተሻለ የሆነው ፓርቲ የሕዝቡ ምርጫ ይሆናል ብሎ ያምናል።
ዳዊት፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ወቀሳ የበዛበት ኤኤንሲ አሁን አብላጫ ድምጽ እንደሚያገኝ ይጠብቃል።
ከሥራ አጥነት እና የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በተጨማሪ የዘንድሮው ምርጫ ማጠንጠኛ የሆነው ጉዳይ የወንጀል መጨመር ነው።
ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ባለፉት ዓመታት ዝርፊያ፣ መድፈር እና ግድያ በከፍተኛ ደረጃ ተንሰራፍተዋል።
ባለፉት ሦስት ወራት በአገሪቱ በየ20 ደቂቃው አንድ ሰው ሲገደ፣ በየቀኑ ከ130 በላይ ሴቶች እንደሚደፈሩ ተዘግቧል።
ደቡብ አፍሪካ ሌላው ራስ ምታቷ ፍትሐዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል ነው።
ሀብታሞቹ 20 በመቶ ደቡብ አፍሪካውያን የአገሪቱን 70 በመቶ ገቢ ሲቆጣጠሩ፣ ድሃዎቹ 40 በመቶ ደቡብ አፍሪካውያን የአገሪቱን 7 በመቶ ገቢ ብቻ ነው የሚያገኙት።
በጥቂት ነጮች ይመራ የነበረው የዘር መድልዎ ሥርዓትን (አፓርታይድ) ታግሎ የጣለው ኤኤንሲ በአሁኑ ምርጫ የሚያገኘው ድምጽ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ 50 በመቶ ዝቅ ሊል እንደሚችል የዳሰሳ ጥናቶች ይጠቁማሉ።
















