ከሠራተኞች ኅብረት መሪነት ወደ የናጠጠ ሃብታምነት የተሸጋገረው የፕሬዝዳንት ራማፎሳ ጉዞ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ደቡብ አፍሪካን እየመሩ ያሉት ሲሪል ራማፎሳ በራስ መተማመን እና ግርማ ሞገስን የተላበሱ ናቸው።
ለአስር ዓመታት ያህል በፖለቲካው መድረክ የቆዩት ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያንን ከሰው በታች ያወረደው የነጮች አገዛዝ የሆነውን የአፓርታይድ እንቅስቃሴም በመታገል ጉልህ ሚና ያላቸው ናቸው።
ራማፎሳ በአገሪቱ ለዘመናት ከተጫወቱት ፖለቲካዊ ሚና አንጻር ደቡብ አፍሪካ በቅርቡ በምታደርገው ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ በፕሬዝዳንትነት ይመረጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ነገር ግን በቅርቡ በተሰበሰቡ የሕዝብ አስተያየቶች የአፍሪካ ብሐሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) መሪ ራማፎሳ ከ30 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ50 በመቶ ያነሰ ድምጽ ሊያገኙ እንደሚችሉ ተንብየዋል።
የ71 ዓመቱ ራማፎሳ የአስተዳደር ዘመን ተስፋ አስቆራጭ በሆነ የሥራ እጦት፣ የምጣኔ ሀብት እኩልነት አለመስፈን፣ በከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እና በሙስና እየተፈተነ ይገኛል።
በተለይም የአፓርታይድ ሥርዓት መገርሰስን ተከትሎ ኤኤንሲ በአውሮፓውያኑ 1994 ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ የፕሬዝዳንትነቱን ሚና ይሹ ነበር ለሚባሉት ራማፎሳ መሬት ላይ ካለው እውነታ የራቁ አድርጓቸዋል።
ራማፎሳ የተወለዱት በአውሮፓውያኑ 1952 ማዕከላዊ ጆሃንስበርግ አቅራቢያ ነው። ልጅነታቸውም ሆነ ወጣትነታቸውን ያሳለፉት በዘረኛው የአፓርታይድ ሥርዓት ውስጥ ነው። ጭቆናንንም ሆነ ኢ-ፍትሃዊነትንን የሚያውቁት ገና በልጅነታቸው ነው።
ልጅ እያሉም ቤተሰቦቻቸው በግዳጅ ወደ ሶዌቶ መንደር ተወሰዱ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደቡብ አፍሪካውያን በወቅቱ በነበሩ ነጭ ባለሥልጣናት ሶዌቶን ጨምሮ በምጣኔ ሀብታቸው ምድረበዳ ወደ ሆኑ ቦታዎች በግዳጅ እንዲሰፍሩ ተደርገዋል።
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ መምህራኖቻቸውን በዕውቀት በመፈተን የቤት ሥራ ከሚሰጡ ጎበዝ ተማሪዎች መካከል እንደነበሩ የሕይወት ታሪካቸውን የጻፉት ፕሮፌሰር አንቶኒ በትለር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በከፍተኛ ሁኔታ በራስ መተማመን ያለው እና ተወዳጅ ነበር” ሲሉ ፕሮፌሰሩ ስለ ራማፎሳ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።
ራማፎሳ በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው በጥቁር እንቅስቃሴዎች ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ ነበራቸው። በዚህም ተሳትፏቸው ምህረት ያልነበረው አገዛዙ ለሁለት ወራት ያህል በእስር ቤት ብቻቸውን እንዲታሰሩ አድርጓቸዋል።
በነጮች የማዕድን ፋብሪካ ኃላፊዎች ላይ የተነሳውን የማዕድን ሠራተኞች ብሔራዊ ኅብረትን ከመሩት አንዱ ናቸው ራማፎሳ።
በቆዳ ቀለማቸው የተሻለ ክፍያ የማያገኙበትን መድሎን ጨምሮ በጥቁሩ ሠራተኞች ላይ የተጫኑ ኢፍትሃዊ አሠራሮችን ለማስወገድ በደቡብ አፍሪካ ታሪክ ውስጥ ከታዩ ታላላቅ አድማዎችን አዘጋጅቷል ኅብረቱ።
አፓርታይድን በማስወገድ ከፍተኛ ሚና የተጫወተውን የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስን (ኤኤንሲ) በመቀላቀል የጭቆናው አገዛዝ እንዲያበቃ በነበረው ትግል፤ እንዲሁም በኋላ በነበረው ድርድር ከኔልሰን ማንዴላ ጋር በቅርበት ሠርተዋል።
ከነጻነት በኋላ ማንዴላ የደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዝዳንት ሲሆኑ ራማፎሳ ምክትላቸው የመሆን ምኞት ነበራቸው። ሆኖም ይህ ምኞታቸው አልተሳካም፤ የኃላፊነቱ ቦታ ለታቦ ምቤኪ ተሰጠ።
ራማፎሳ በሁኔታው ደስተኛ ባይሆኑም የፓርላማ አባል በመሆን በዓለማችን ላይ ተራማጅ ከሚባሉት አንዱ የሆነውን አዲሱን የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥት በማርቀቅ እና በማጽደቁ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ ይነገርላቸዋል።
ሆኖም በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፉት ራማፎሳ፣ በርካቶችን ባስገረመ መልኩ ከፖለቲካው መድረክ ራቅ ብለው የቢዝነሱን ዓለም ተቀላቀሉ።
“በማንዴላ እና በሌሎቹ ተማምኖ ነበር ወደ ሌላ አቅጣጫ ያማተረው። በወቅቱ እሱ በአንጻራዊነት ወጣት ነበር” ይላሉ ፕሮፌሰር በትለተር።
በአገሪቱ በጥቂት ነጮች በተያዘው የንግድ እና የቢዝነስ ዓለም ራማፎሳ በተለያዩ ዘርፎች ተሰማሩ። በቴሌኮም፣ መገናኛ ብዙኃን፣ በለስላሳ መጠጦች፣ እንዲሁም የአሜሪካው ፈጣን ምግብ ማክዶናልድስ የደቡብ አፍሪካው ሰንሰለትም የሳቸው ነው።
ከዚህም በተጨማሪ በማዕድን ማውጣት ድርሻ ኖራቸው። ንግዶቻቸው በጣም ትርፋማ የሆኑላቸው ራማፎሳ፣ በአውሮፓውያኑ 2015 ወደ 450 ሚሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት በመያዝ ከደቡብ አፍሪካ ሃብታም ፖለቲከኞች አንዱ ሆኑ።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ነገር ግን በአውሮፓውያኑ 2012 በማሪካና ፕላቲኒየም ማዕድን ማውጫ ፖሊስ 34 ሠራተኞችን በመግደሉ የራማፎሳ ስም ጠለሸ። የጨቋኙ የነጮች አገዛዝ ካበቃ በኋላ የከፋ የፖሊስ እርምጃ እና በርካታ ግድያዎች የተስተናገዱበት ነው ማሪካና።
በማሪካና ግድያዎቹ ሲፈጸሙ ራማፎሳ የማዕድን ማውጫው ባለቤት የሆነው ዓለም አቀፉ ድርጅት ሎንሚን ዳይሬክተር ነበሩ።
በአንድ ወቅት ሲታገሉለት የነበሩትን ሠራተኞች ከድተዋል በሚል ተወቀሱ። ይህንን ያስባለው ዋነኛ ጉዳይ ደግሞ ሠራተኞቹ አድማ ማስነሳታቸውን በመጥቀስ “የወንጀል ድርጊቶችን ለማስቆም” እርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ መስጠታቸውን የሚያሳዩ የኢሜይል መልዕክቶች መውጣታቸውን ተከትሎ ነው።
በዳኛ የሚመራ አጣሪ ቡድን በግድያው ውስጥ አላቸው ከተባለው ተሳትፎ ነጻ ቢያደርጋቸውም የጠለሸ ስማቸውን ግን ሊያጸዳው አልቻለም።
በአንድ ወቅት ለሠራተኞች መብት ይታገሉ የነበሩት እና በኋላ ቱጃር የሆኑት ራማፎሳ፣ ወደ ፖለቲካው የተመለሱት የኤኤንሲ ምክትል ሆነው ከተመረጡ በኋላ ነው።
ከሁለት ዓመት በኋላ በከፍተኛ ቅሌት ሲከሰሱ ለነበሩት ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ምክትል ሆኑ።
ነገር ግን የዙማ የኤኤንሲ የሁለት ጊዜ የመሪነት ገደብ ሲቃረብ ራማፎሳ በፀረ ዙማነት ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው መጡ።
በዋናነትም ይዘውት የመጡት በዙማ አስተዳደር ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ የተንሰራፋውን ሙስና ለመቀልበስ ቃል በመግባት ነው።
ራማፎሳ ቀጣዩ የኤኤንሲ ፕሬዝዳንት የመሆን ውድድራቸው መጀመሪያ ቀለል ያለ መስሎ ቢታይም፤ ነገር ግን ፕሬዝዳንት ዙማ ያለ የሌለ ድጋፋቸውን ለቀድሞ ባለቤታቸው እና ለቀድሞዋ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ኃላፊ ንኮሳዛና ድላሚኒ ማድረጋቸው ሁኔታዎችን ቀየረ።
በሁለቱ ፖለቲከኞች መካከል ከተደረገው ከፍተኛ ፉክክር በኋላ ንኮሳዛና ድላሚን አሸንፈው ራማፎሳ በአውሮፓውያኑ 2017 የኤንኤንሲ መሪ ሆኑ።
ዙማ እስከ አውሮፓውያኑ 2019 አጠቃላይ ምርጫ ድረስ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ለመቆየት አስበው ነበር። ነገር ግን ራማፎሳን ጨምሮ የኤንኤንሲ አመራሮች ባደረጉት ከፍተኛ ግፊት ውዝግብ ውስጥ የገቡት ፕሬዝዳንት ዙማ ሥልጣን ለመልቀቅ ተገደዱ።
ከ25 ዓመታት ምኞት በኋላ የራማፎሳ የረዥም ጊዜ ህልም እውን ሆነ። ራማፎሳ ዙማን በመተካት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው እንደሚሾሙ በፓርላማ ሲታወጅ የምክር ቤቱ አባላት በዘፈን እና በሆይታ ነበር ደስታቸውን የገለጹት።
አዲሱ መሪ በመጀመሪያ ንግግራቸውም ሙስናን በጽኑ እታገላለሁ ቢሉም፤ ነገር ግን ብዙም ሳይቆዩ ራሳቸውም በተለያዩ ቅሌቶች ተዘፍቀዋል በሚል ስማቸው መነሳት ጀመረ።
ራማፎሳ ለኤኤንሲ ፕሬዝዳንትነት ያደርጉት በነበረው የምረጡኝ ዘመቻ ቅስቀሳ ወቅት አወዛጋቢ ከተባለ የአገር ውስጥ ኩባንያ ለዘመቻው የልገሳ ገንዘብ እንዳልተቀበሉ በአውሮፓውያኑ 2018 ለፓርላማው ተናግረው ነበር።
በኋላ ግን ለፓርላማው ምላሽ በሰጡበት ወቅት የተሳሳተ መረጃ ይዘው እንደነበር በመግለጽ ይቅርታ ጠይቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ማመናቸው የፀረ ሙስና ዘመቻቸው ላይ ውሃ የቸለሰበት ጉዳይ ሆኗል። ሆኖም ከዓመታት በኋላ ፕሬዝዳንቱ ሆን ብለው ፓርላማውን አሳስተዋል የሚለውን ሃሳብ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ውድቅ አድርጎታል።
ፕሬዝዳንት ዙማ ሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ከመንግሥት ካዝና በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር መዘረፉን ከሁለት ዓመታት በፊት የወጣ ምርመራ ይፋ አድርጓል። በዚህ ወቅት ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት ዙማ የሥርዓቱን መበስበስ እና ዘረፋዎችን ለማስቆም ምንም አላደረጉም በሚልም በዚህ ሪፖርት ላይ ተጠቅሰዋል።
በዚህ ብቻ አላበቃም ይህ ሪፖርት ከወጣ ጥቂት ወራት በኋላ ፕሬዝዳንቱ በሌላ የሙስና ቅሌት ስማቸው ይነሳ ጀመር።
ራማፎሳ እንስሳትን በማዳቀል ከሚታወቀው ፋላ ፋላ ከተሰኘው የእርሻ ቦታቸው 4 ሚሊዮን ዶላር ጥሬ ገንዘብ ወስደው ደብቀዋል በሚል ተከሰው ነበር። ፕሬዚዳንቱ ምንም አይነት ጥፋት እንዳልፈጸመው አስተባብለው በሶፋ ውስጥ የተደበቀው ገንዘብ በአውሮፓውያኑ 2020 የተወሰደ መሆኑን አምነዋል።
ገንዘቡ 4 ሚሊዮን ዶላር ሳይሆን 580 ሺህ ዶላር መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ጎሽ በመሸጥ ያገኘሁት ነው ብለዋል። በቀድሞ የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኃላፊ የሚመራ የሕግ ባለሙያዎች ቡድን ባደረገው ማጣራት ፕሬዝዳንቱ ተፈጽሟል የሚሉት ሽያጭ ስለመፈጸሙ “ጥርጣሬ አለኝ” ብሏል።
ይህንንም ተከትሎ በኤኤንሲ እንዲሁም ከፓርቲው ውጪ ያሉ ተቃዋሚዎቻቸው ሥልጣን እንዲለቁ ጠይቀዋቸው ነበር። ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ የፓርቲያቸውን ድጋፍ በማግኘታቸው የመሪነት ስፍራቸውን ይዘው እንዲቀጥሉ ሆነ።

የፎቶው ባለመብት, ANC
ከዚህ ቅሌት በተጨማሪ አገሪቱ በውሃ እጦት ቀውስ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት እና በሥራ አጥነት እየተፈተነች ባለበት ወቅት ነው ፕሬዝዳንቱ ለሁለተኛ ጊዜ ምረጡኝ እያሉ ያሉት።
በእነዚህ ተግዳሮቶች ምክንያት የኤኤንሲ ተቀባይነት ያሽቆለቆለ ቢሆንም፤ የፖለቲካ ተንታኙ ሪቻርድ ካላላንድ ራማፎሳ ከቀድሞ የደቡብ አፍሪካ መንግሥታት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን ቢወርሱም “የማይበገሩ እና አስደናቂ” ፕሬዝዳንት ናቸው ይላቸዋል።
“በምጣኔ ሀብት ማገገሚያ ዙሪያ እና በመሳሰሉት በርካታ መለኪያዎች አገሪቱ ያላት ገጽታ አሉታዊ ቢሆኑም፣ እሳቸውም ድክመቶች ቢታዩባቸውም አገሪቱ የምትፈልጋቸው ጥሩ መሪ ነበር ብዬ አስባለሁ” ይላሉ ተንታኙ።
የኤኤንሲም የ2024 ማኒፌስቶ ይህንን የተንታኙን አመለካከት ያስተጋባ ነው።
ፓርቲው በፕሬዝዳንቱ ከተወሰዱ አዎንታዊ እርምጃዎች መካከል ደቡብ አፍሪካ እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት እየፈጸመች ነው በሚል ለተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ፍርድ ቤት መክሰሷን አጉልቷል። ለወራት በዘለቀው የጋዛ ጦርነት ራማፎሳ እና መንግሥታቸው ከፍልስጤማውያን ጎን በመቆም የእስራኤል ባለሥልጣናትን አጥብቀው በመቃወም ላይ ናቸው።
ፕሬዝዳንቱ በአውሮፓውያኑ 2019 በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሚኒስትሮቻቸው ግማሹን ሴቶች በማድረግ አዲስ ካቢኔ በማዋቀራቸው እንዲሁ አድናቆት ተችሯቸዋል።
የማዕድን ማውጫ ሠራተኞችን ኅብረት ከመምራት እስከ የአፍሪካ ትልቁ ምጣኔ ሀብት ባለቤት የሆነችውን አገር መምራት የቻሉት ራማፎሳ የፖለቲካ ሕይወት በተቃርኖ የተሞላ ነው።
ፕሬዝዳንቱ አሁን በያዙት የምርጫ ዘመቻ ላይ ኤኤንሲ በአፓርታይድ ወቅት የፈጸማቸውን ተጋድሎዎች በማስታወስ ላይ ናቸው።
“የሰላሳ ዓመታት ነጻነት እና ዲሞክራሲን በምናከበርበት ወቅት በደቡብ አፍሪካዊነታችን እንኩራ፤ ባገኘናቸው ስኬቶች እንደሰት። ያሳካናቸው ስኬቶች ከተግዳሮቶቻችን ይልቃሉ” ሲሉ ምሥራቃዊ ኬፕን በጎበኙበት ወቅት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።













